ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሕግ ታራሚዎችን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 10/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሕግ ታራሚዎችን በጸሎታቸው አስታውሰው ምዕመናንም በመንፈስ እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

በቫቲካን ውስጥ ከሚገኝ የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት በቪዲዮ ምስል በቀጥታ በተሰራቸው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከታቸው በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎችን እና በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ ዛሬ ተከብሮ የዋለውን የቅዱስ ዮሴፍ መታሰቢያ በዓል ማክበር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው ምዕመናንም መንፈሳዊ አንድነታቸውን በያሉበት እንዲያጠናክሩ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 10/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ ደረጉት ንግግር፣ ዕለቱ የመላዋ ቤተክርስቲያን ባልደረባ የሆነው እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረዳት ቅዱስ ዮሴፍ መታሰቢያ እለት መሆኑን አስታውሰው፣ እርሳቸውም መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሐዋርያዊ ስልጣን የተቀበሉበት ሰባተኛ ዓመት መታሰቢያ ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተዛመተ በሚገኝበት ባሁኑ ወቅት በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

"በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በጸሎታችን እናስታውሳቸው፤ የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ውስጥ ሊከሰት በሚችለው ነገር እርግጠኞች ባለመሆናቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውም ጭምር በማሰብ እና በመጨነቅ ላይ ስለሚገኙ በጸሎታችን እናስታውሳቸው"።

ለዕለቱ በተመደበው የማቴ. 1: 16 እና 18-21 እና 24 ላይ በተጻፈው የወንጌል ክፍል በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል ቅዱስ ዮሴፍ ትክክለኛ እና እምነቱን በተግባር የኖረ ሰው መሆኑን እንደሚገልጽ፣ በእግዚአብሔር ምሥጢር ለመሳተፍ ችሎታ ያለው መሆኑን አስረድተው፣ በመሆኑም ክብረ በዓሉን የውዳሴ እና የምስጋና ጸሎትን በማቅረብ ማክበር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው።

የቅዱስ ቤተሰብ ምስል፥ ኢየሱስ፣ ማርያም እና ዮሴፍ አንድ ላይ፤
የቅዱስ ቤተሰብ ምስል፥ ኢየሱስ፣ ማርያም እና ዮሴፍ አንድ ላይ፤

"ቅዱስ ዮሴፍ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ዕብራዊያን በጻፈው መልዕክቱ በምዕ. 11 ላይ፣ እምነታቸውን በተስፋ የኖሩ ናቸው በማለት ከጠቀሷቸው ሰዎች መካከል እንደ አንዱ ሊቆጠር ይችላል። እነ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ እና አብርሃም እምነታቸውን የኖሩት በተስፋ፣ የማይታይ ነገርን መተማመኛቸው በማድረግ ነው።

ቅዱስ ዮሴፍም ትክክለኛ ሰው ሆኖ የተቆጠረው የእምነት ሰው ስለሆነ ነው። ማመን ብቻ ሳይሆን የሚያምነውን በተግባር የኖረ ሰው ነው። ቅዱስ ዮሴፍ ትክክለኛ የእምነት ሰው ስለነበር፣ በእውነትም ሰው እና እግዚአብሔር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያስተምር በእግዚአብሔር ተመረጠ። ይህን ለማድረግ ከዮሴፍ በቀር ሌላ ሰው አልተገኘም። ቅዱስ ዮሴፍ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ መነጋገር የቻለ ሰው ነበር። በእግዚአብሔር ምሥጢር ለመካፈል ችሎታ ያለው ሰው ነው። የሚፈልገውን፣ የሚያስበውን ነገር ለማድረግ በምኞት ብቻ የተገደበ ሰው አልነበረም። በአናጺነት ሞያው ሁሉን በልኩ የሠራ፣ እንዴትስ መሥራት እንዳለበት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከችሎታው በላይ በሆነው በእግዚአብሔር ምስጢር ውስጥ መግባት የቻለ ሰው ነበር። የዮሴፍ ቅድስና የተገልጸውም በዚህ ነው። ቅዱስ ዮሴፍ ሕይወቱን እና የዕለት ተግባሩን ፍትሐዊነት በተሞላ መንገድ መምራት የቻለ ሰው ነው። ቅዱስ ወንጌል ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ሕልሞች ሲናገረን የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር ቅዱስ ዮሴፍ ወደ እግዚአብሔር ምስጢር መግባቱን ነው።

ዛሬ ተከብሮ በዋለው የቅዱስ ዮሴፍ ክብረ በዓል ዕለት ስለ ቤተክርስቲያን አስባለሁ። ምዕመናኖቻችን፣ ብጹዓን ጳጳሶቻችን፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም ቢሆኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ምስጢር የመግባት ችሎታ አላቸውን? ወይስ ይህ ችሎታ እንዳይኖር በሚከለክሏቸው አንዳንድ ነገሮች ላይ ማሰብ ይኖርባቸዋል። ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ምስጢር ውስጥ የመግባት ችሎታ ከሌላት ምስጋናን እና ውዳሴን የማቅረብ ችሎታ ታጣለች። የውዳሴ ጸሎት ሊቀርብ የሚችለው አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ምስጢር ሲገባ ብቻ ነው።                  

በመሆኑም ቤተክርስቲያን በዕለታዊ ሕይወቷ እርግጠኛ እንድትሆን እና በእግዚአብሔር ምስጢር መግባት የምትችልበትን ጸጋ ከእግዚአብሔር እንለምን። ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ምስጢር ውስጥ ያልገባ ከሆነ፣ ሙሉ ቤተክርስቲያን ተብላ ልትቆጠር አትችልም። ለምስጋና እና ለውዳሴ የምትሰበሰብ ሳትሆን በአንዳንድ ሕጎች ብቻ የምትመራ ዓለማዊ ማሕበር ትሆናላች። ወደ እግዚአብሔር ምስጢር መግባት ማለት ደግሞ በምኞት ብቻ መኖር ማለት አይደለም። ወደ እግዚአብሔር ምስጢር መግባት ማለት እርሱን በእውነት ማክበር እና ማወደስ ነው። ወደ እግዚአብሔር ምስጢር መግባት ማለት ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ያቀድነውን ውዳሴ ነገ ሳይሆን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በሚገኝበት በዛሬዋ ዕለት ማቅረብ ማለት ነው። ይህን ማድረግ የምትችልበትን ጸጋ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን ይስጣት”።    

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ከማጠቃለላቸው በፊት ባሰሙት ንግግር በተላላፊው የኮሮና ቫይረስ መዛመት ምክንያት በጣሊያን ቁምስናዎች የሚደረግ የጋራ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መቋረጡን አስታውሰው፣ ቢሆንም በዚህ አስጨናቂ ወቅት ምዕመናን በመንፈስ አንድ በመሆን በጸሎት እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው በማሕበራዊ መገናኛዎች፣ በቴለቪዢን ጣቢያዎች የሚተላለፍ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን እና ሌሎች መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

“ኢየሱስ ሆይ! ራሴን ዞር ብዬ በመመልከት የተሰበረውን ልቤን ይዤ ለንስሐ ወደ እግሮችህ አጠገብ ቀርቤአለሁ። በፍቅር በገለጥካቸው ቅዱሳት ምስጢራት በኩል አክብርሃለሁ፤ በደሳሳ ቤቴ፣ አንተን በልቤ ውስጥ ልቀበልህ እመኛለሁ፤ ከቅዱሳት ምስጢራት ኅብረት የሚገኘውን ደስታ በመጠባበቅ ፣ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እፈልጋለሁ፤ ኢየሱስ ሆይ ፣ ወደ እኔ ና! በሕይወቴ ዘመን እንዲሁም በሞቴ ሁሉ ፍቅርህ ይብዛልኝ፤ እምነቴ እና ተስፋዬ አንተው ነህና እወድሃለሁ፤ አሁንም፣ ዘወትርም ይሁን”።

ብለው ጸሎታቸውን በማቅረብ የዕለቱን ስብከታቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
19 March 2020, 17:01
ሁሉንም ያንብቡ >