ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት   (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ክርስቲያን መሆን ማለት እስከ መስቀል ድረስ የኢየሱስን መንገድ መከተል ማለት ነው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቄሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመና በተገኙበት በየካቲት 12/2012 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ክርስቲያን መሆን ማለት  እኛን ለማዳን ኢየሱስ የተጓዘበትን መንገድ መከተል ማለት ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ማነኛውም ክርስቲያን ምዕመን፣ ጳጳስ፣ ካህን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሳይቀር ይህንን ኢየሱስ የተጓዘበትን መንገድ የማይከተሉ ከሆነ መንገድ ስተዋል ማለት ይቻላል ምክንያቱም ክርስቲያን መሆን ማለት እስከ መስቀል ድረስ የኢየሱስን መንገድ መቀበል እና መከተል ማለት ስለሆነ ነው ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት አክለው እንደ ገለጹት ከክርስትና ሐይማኖት ጋር የተጣጣመ ሕይወት መኖር እንችል ዘንድ እና እንዲያው ክርስቲያን ነኝ ብለን ለይስሙላ እንዳንኩራራ ይረዳን ዘንድ ጸጋውን ልንጠይቅ የገባል ብለዋል።

“ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?”፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” እነዚህ ዛሬ በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማርቆስ 8፡27-9፡1) የሚገኙት ጥያቄዎች ናቸው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በወቅቱ እርሳቸው ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ያጠነጠነው በእነዚህ ሁለት ኢየሱስ ባቀረባቸው ጥያቄዎች ላይ መስረቱን ያደርገ እንደ ነበረም ተገልጹዋል። ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ማን እንደ ሆነ ሐዋርያቱ በሚገባ ይገነዘቡ ዘንድ ሦስት ደረጃዎችን ይጠቁማል፣ እነዚህም እግዚኣብሔርን ማወቅ፣ እርሱን መመስከር እና እግዚኣብሔር ለኢየሱስ የመረጠውን መንገድ መቀበል የሚሉት እንደ ሆኑ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ኢየሱስን መመስከር ይገባል

ኢየሱስን ማወቅ ማለት አሉ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ቅዱስ ወንጌል ይዘን፣ ኢየሱስ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ስለእርሱ የተጻፉትን ማንበብ፣ ሕጻናትን ወደ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በምንወስደበት ጊዜ እና እንዲሁም መስዋዕተ ቅዳሴ በምንሳተፍበት ወቅት እነዚህን እና እነዚህን በመሳሰሉ ሁኔታዎች እኛ ኢየሱስን  ለማወቅ እንሞክራለን ነገር ግን ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ብለዋል።

ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ በኢየሱስ መመስከር የሚለው ሲሆን ይህንን እኛ ብቻችን ሆነን ልንፈጽመው የማንችለው ጉዳይ ነው፣ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ለጴጥሮስ “ይህንን የገለጸልህ አባቴ ነው እንጂ አንተ አይደለህም” ብሎት ነበር በእዚህም መሰረት በኢየሱስ ማመን እና ኢየሱስን መመስከር የምንችለው በእግዚኣብሔር ኃይል እና በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ጭምር ነው፣  ስለሆነም የክርስቲያን ማህበረሰብ ኢየሱስ እርሱ እግዚአብሔር ነው ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ለመናገር ሁል ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ማግኘት ይኖርበታል ብለዋል።

እስከ መስቀል ድረስ የኢየሱስን መንገድ መከተል

ነገር ግን የኢየሱስ ሕይወት ዓላማ ምንድ ነው ፣ ለምንስ መጣ? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እሱን ለማወቅ በማሰብ መጓዝ ሦስተኛውን እርምጃ መውሰድ ማለት ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ኢየሱስ መሰቃየት ፣ መገደል እና እንደገና ከሙታን መነሳት እንዳለበት ለሐዋርያቱ ማስተማሩን አስታውሰዋል።

      ኢየሱስን መመስከር ማለት የእርሱን ሞቱን፣ የእሱን ትንሣኤ፣ መመስከር ማለት ነው እንጂ እንዲያው ለይስሙላ “አንተ እግዚአብሔር ነህ” ማለት በራሱ በቂ አይደለም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “አንተ ወደ እዚህ ምድር ለእኛ ስትል መጥተኃል፣ ለእኔ ሞተኃል። ከሙታን ተነስተኃል፣ ሕይወት ተሰጥቶናል፣ በሕይወት ጉዞ የመራን ዘንድ መንፈስ ቅዱስህን እንደ ምትልክልን ቃል ገብተሃል፣ በማለት ልናምን እና ልንመሰክር እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን ኢየሱስን መመስከር ማለት አብ ለኢየሱስ የመረጠውን የውርደት መንገድ መቀበል ማለት ነው ብለዋል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ "እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ” ብሎ እንደ ገለጸው እኛም ይህንን የኢየሱስን መንገድ እና ለቤዛነት የመረጠውን የውርደት መንገድ ካልተቀበልን እኛ በሙሉ ልባችን ክርስቲያኖች ነን ብለን ለመናገር አንችልም ብለዋል።

የውርደት መንገድ የማይከተል ክርስቲያን አይደለም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሰይጣን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በደንብ እንደሚያውቅ ጠቁመው ነገር ግን ጴጥሮስ ኢየሱስ የመረጠውን መንገድ በመቃወሙ የተነሳ ጴጥሮስን ከእኔ ወዲያ ራቅ በማለት እንደ ገሰጸው ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። በእርግጥ “ኢየሱስን ማመን እና መመስከር” ማለት ኢየሱስ የመረጠውን የትህትና እና የውርደት መንገድ መከተል ማለት ነው ያሉ ሲሆን ቤተክርስቲያን በእዚህ መንገድ ካልተመራች መንገዷን ትስታለች፣ ዓለማዊ ትሆናለች ብለዋል።

ብዙ መልካም እና በጎ የሆነ ፈቃድ እና ምኞት ያላቸውን ጥሩ የሆኑ ክርስቲያኖችን ስንመለከት፣ እምነት አለኝ በማለት ስለእምነታቸውን ይናገራሉ፣ ይመሰክራሉም፣ ነገር ግን ይህንን የሚያደርጉት እውነተኛውን ሐይማኖት በተከተለ መልኩ ሳይሆን ማኅበራዊ በሆነ መልኩ ነው፣ የእዚህ ዓይነት መንገድ ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች ግራ የተጋቡ ክርስቲያኖች ናቸው፣ ጌታ ሆይ ይላሉ ነገር ግን በተቃራኒው ዓለማዊ የሆነ የክብር ስፍራን የፈልጋሉ። በእዚህም መሰረት እንዲህ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች በስም ብቻ ክርስቲያኖች የሆኑ ሰዎች ናቸው፣ ምክንያቱም ኢየሱስ በተጓዝበት መንገድ ላይ እየተጓዙ አይደለምና፣ የሚፈልጉት የኢየሱስን መንገድ ሳይሆን የራሳቸውን የክብር መንገድ ነው፣ ትክክለኛው የኢየሱስ መንገድ የወርደት እና የትህትና መንገድ ነው ብለዋል።

በእዚህም መሰረት “ክርስቲያን ነኝ” በማለት ስንናገር እና ስንመሰክር ከእዚህ ታላቅ ከሆነ የክርስትና ስም ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ኑሮ እና ሕይወት ሊኖረን ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው በእዚህ እውነተኛ እና ኢየሱስ ባሳየን የትህትና መንገድ ላይ መጓዝ እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን ልንማጸነው የገባል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

20 February 2020, 15:17
ሁሉንም ያንብቡ >