ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የክርስቲያን ልብ በደስታ የተሞላ ሊሆን ይገባል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥር 19/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ከተገኙት ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ጊዜ የሚሰማቸውን ደስታ አውጥተው እንዲያሳዩ፣ በክርስቲያኖች የደስታ በዓል ላይም መገኘት ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም “ቅዱስ ወንጌል በሚገባ ሊሰበክ የሚችለው ዘወትር ደስተኛ በሆኑ የወንጌል አገልጋዮች ሲታገዝ ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለዕለቱ በተመደበው የመጀመሪያ ንባብ፣ በ2ኛ ሳሙ. 6:12-15 እና 17-19 ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የእስራኤል ሕዝብ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ በጋራ ሆነው ደማቅ በዓል ማክበራቸውን አስታውሰዋል።

የእስራኤል ሕዝብ የተደሰተው እግዚአብሔር አብሮት ስለሆን ነው፣

ተሰውሮ የነበረ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሲመጣ ለእስራኤል ሕዝብ ታላቅ ደስታን እንዳስገኘላቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው የእስራኤል ሕዝብ የተደሰተበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን እግዚአብሔር አጠገቡ ስለተገኘ ነው በማለት አስረድተዋል። ንጉሣቸው ዳዊትም ከፊት ለፊታቸው ሆኖ ሕዝቡን ይመራቸው እንደነበር፣ ከሕዝቡም ጋር ሆኖ ደስታውን ይገልጽ እንደነበር አስታውሰዋል።

ጠፍቶ የቆየው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት መገኘቱ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ትልቅ ደስታን ፈጥሯል። የተደሰቱትም እግዚአብሔር ወደ እነርሱ ስለተመለሰ ነው። ንጉሣቸው ዳዊት፣ እኔ ንጉሣቸው ነኝ በማለት ራሱን ከፍ አላደረገም፤ ኃፍረትም ሳይዘው ከሕዝቡ ጋር እየጨፈረ ደስታውን ገለጸ። ምክንያቱም በዓሉ የተዘጋጀው እግዚአብሔር በመካከላቸው ስለተገኘ እና ደስታቸው መንፈሳዊ ደስታ ስለ ነበር ነው። ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔርን ስለሚወድ፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ስለተገኘ እጅግ ተደሰተ፤ ደስታውንም በዘፈን እና በጭፈራ ገለጸ።     

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ስንገነዘብ እኛም ደስታ ይሰማናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቁምስናዎች እና በአንዳንድ አካባቢዎች ምዕመናን ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች የሚገልጹ መሆኑን አስታውሰዋል። የእስራኤል ሕዝብ የተደሰተበት ሌላ አጋጣሚ መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በነህምያ ዘመን የሕጉ መጽሐፍ በተገኘ ጊዜ ሕዝቡ ደስታውን በልቅሶ መግለጹን አስታውሰዋል።

ለድንገተኛ ደስታ የተደረገ ንቀት፣

በሁለተኛ ትንቢተ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው፣ ከበዓሉ በኋላ ዳዊት ቤተሰቡን ለመባረክ ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ፣ ከሚስቶቹ መካከል አንዷ፣ የሳውል ልጅ ሜልኮል ልትቀበለው በወጣች ጊዜ “የእስራኤል ንጉሥ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ሲጨፍር መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው”! በማለት መናቋን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

ዳዊት ከሚስቱ ሜልኮል በኩል የተሰጠው ንቀት ለትክክለኛ ሃይማኖታዊነት የተሰጠ ንቀት ነው፤  ይህ ንቀት እግዚአብሔርን በማግኘት ለተፈጠረ ድንገተኛ ደስታ የተሰጠ ንቀት ነው። ዳዊትም ሚስቱን እንዲህ አላት፥ “ደስታዬን የገልጽኩበት ምክንያት ተሰውሮ የነበረ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ በመምጣቱ ነው፤ ይህም ለእስራኤል ሕዝብ ታላቅ ደስታን አስገኝቷል”። ሜልኮል ባሏን በዚህ ምክንያት በመናቋ የተነሳ እግዚአብሔር፣ ልጅ እንዳትወልድ፣ ፍሬን እንዳታፈራ ማድረጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን። አንድ ክርስቲያን ደስተኛ ሳይሆን ሲቀር፣ ያ ክርስቲያን ፍሬን ሊያፈራ አይችልም። በልባችን ውስጥ ደስታ የሚጎድል ከሆነ ፍሬን ማፍራት አንችልም።  

 

ወደ ፊት ለመጓዝ ደስተኛ የወንጌል አገልጋዮች ሊኖሩ ይገባል፣

የበዓል ትርጉም መንፈሳዊነቱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን የሚያሳትፍ፣ ከሌሎች ጋር በሕብረት የሚደረግ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነው ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ንጉሥ ዳዊት ከቡራኬ በኋላ ዳቦን ቆርሶ ከወይን ጠጅ ጋር ለሕዝቡ በማዳረስ፣ ሕዝቡም ወደ የቤቱ ሲመለስ እቤት ካሉት ጋር በመካፈል በዓል እንዲያከብር ማድረጉን አስታውሰዋል። ለእግዚአብሔር ተብሎ በሚደረግ በዓል ላይ ደስታን መግለጽ ኃፍረት ሊሆን አይገባም ያሉት ቅዱስነታቸው በእርግጥ መጠንን ያለፈ ደስታ ወደ ሌላ መንገድ በማምራት አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አስረድተው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፣ “ወንጌልን ማብሰር” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ስለ እውነተኛ ደስታ መናገራቸውን አስታውሰዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ጥር 19/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን ስብከት ከማጠቃለላቸው አስቀድመው እንደተናገሩት፣

ቤተክርስቲያን ወደ ፊት መራመድ የምትችለው፣ ቅዱስ ወንጌልም በሚገባ ሊሰበክ የሚችለው ደስተኛ የሆኑ የወንጌል አገልጋዮች ሲኖሩ ነው ብለው፣ ደስታው የሚመጣው የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንደሆነ አስረድተው በክርስትናችን፣ በክርስትና ሕይወታችን ሳናፍር ደስተኞች መሆን ይገባል እንጂ የስም ክርስትናን ብቻ ይዘን መጓዝ አያስፈልግም ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 January 2020, 16:59
ሁሉንም ያንብቡ >