ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የእግዚአብሔር መገለጥ የሚጀምረው ራስን ዝቅ በማድረግ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ ጠዋት በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ለተገኙት ብጹዓን ጳጳሳት፣ ቄሳውስት፣ ደናግል እና ምዕመና የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ ሥርዓት ወቅት ባሰሙት ስብከተ ወንጌል የእግዚአብሔር መገለጥ የሚጀምረው ራስን ዝቅ በማድረግ እንደሆነ ገልጸው እግዚአብሔር ከተገለጠልን በኋላ ራስን ዝግ በማድረግ መቆየት ሳይሆን በእርሱ በመታመን ምስክርነትንም መስጠትን ይጠይቃል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዕለቱ ከትንቢተ ኢሳያይስ ምዕ. 11: 1-10 ተውስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ላይ “በዚያን ቀን፣ የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ መንግሥታት ወደ እርሱ ይመጣሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል” በሚለው ጥቅስ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሁሉም ዝቅተኛ በሆነው ላይ በመውረድ ከፍ እንዲል ያደርገዋል ብለዋል።        

“እግዚአብሔር ለዓለም የሚገለጠው ራሱን ዝቅ በማድረግ እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው ራስን ዝቅ ማድረግ በብዙ መልኩ ሊወሰድ ይችላል ብለው ከሁሉም በላይ ራስን ዝቅ ማድረግ የሚቻለው ትህትናን በማሳየት ነው ብለዋል። የዓለማችን ሕያላን ያላቸውን አቅም የሚገልጹት ሃይላቸውን በማሳየት ነው። ሰይጣን ኢየሱስን በበረሃ በፈተነው ጊዜ ራሱን ከሁሉ በላይ አድርጎ፣ ሁሉን ለማድረግ እንደሚችል በመናገር፣ ሁሉ ነገር እንዳለው በመግለጽ ነው”።

እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጸው ከሁሉ የበታች አድርጎ ነው በማለት ስብከታቸውን ያሰሙት ቅዱስነታቸው ኢየሱስም በወንጌሉ የተናገረው ይህንን ነው ብለዋል።   

“ኢየሱስም ደስታውን በመግለጽ አባቱን ያመሰገነበት ምክንያት ራሱን የገለጸው ለሃያላን ሳይሆን ለዝቅተኛ፣ ለደካሞች እና ለድሆች ስለሆነ ነው። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት የሚያስረዳን እግዚአብሔር ራሱን ለዓለም የገለጠው ሕጻን በመሆን ነው። በክርስቲያን ማሕበረሰብ ውስጥ ምዕመናን፣ ካህናት፣ ጳጳሳት ይህን የበታችነት መንገድ የማይከተሉ ከሆነ ወደ ፊት ያላቸው ዕጣ ፈንታ መበታተን ይሆናል። ይህ ደግሞ ባለፉት ታሪኮች በገሃድ የተመለከትነው ነው። ክርስቲያኖች ገናና መንግሥት ለመሆን ተዋግተዋል፣ ሃይልን ተጠቅመዋል። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት በገናናነት አይመሠረትም። ሁል ጊዜ ራስን ከጥቃቅን ነገር ጋር ያመሳስላል። ከሰንፍጭ ቅንጣት ጋር ያመሳስላል። ነገር ግን የሰናፍጭ ፍሬ ብቻውን ምንም መሆን አይችልም። እንዲበቅል፣ እንዲያድግ እና እንዲጠነክር የሚያደርግ ሌላ አጋዥ ሃይል ያስፈልገዋል። ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ  “የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ መንግሥታት ወደ እርሱ ይመጣሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል” በማለት ተናግሯል”።   

መንፈስ ቅዱስ በራሳቸው በሚመኩ ልቦች ውስጥ አይገባም፣

መንፈስ ቅዱስ ማረፊያ የሚሆንለትን ሥፍራ ይመርጣል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃይለኛ ነኝ በማለት በራሱ በሚመካ ልብ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሊገባ አይችልም ብለው፣ አቅመ ደካማነቱን እና ዝቅተኛነቱን በሚመሰክር ልብ ውስጥ ገብቶ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ማሳየት ይመርጣል ብለዋል። የስነ መለኮት ጠበብትም ቢሆኑ ስለ እግዚአብሔር ያላቸው ዕውቀት ውስን እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ሁሉን እናውቃለን በማለት ራሳቸውን ከፍ የሚፈልጉ ከሆነ ገና ምንም የማያውቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው ራሱን ካህን፣ ጳጳስ፣ ካርዲናል ወይም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ነኝ ብሎ የሚያምን ማንም ራሱን የበታች አድርጎ ትህትናን የሚገልጽ ካልሆነ፣ ሕዝባዊ መሪ ብቻ እንጂ የእግዚአብሔር ሕዝብ እረኛ ሊሆን አይችልም ብለዋል።   

ክርስቲያናዊ የበታችነት የሚያዋርድ አይደለም፣

ክርስቲያናዊ የበታችነትን በተግባር ማሳየት ሊያስፈራ አይገባም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የምናደርግ ከሆነ በፍርሃት በመያዝ ለእግዚአብሔር የምንሰጠውን ምስክርነት እንጎድላለን ብለዋል። ክርስቲያናዊ የበታችነት ታላቅ መሆንን ያመለክታል ያሉት ቅዱስነታቸው ከክርስቲያናዊ የበታችነት ትርፍን እንጂ አንከስርም ብለዋል።

ቅዱስ ቶማስ አስተምህሮቹን በአጭሩ ሲያጠቃልል፣ በግዙፍ ነገሮች አትደናገጡ፣ ቅዱስ ፍራንቸስቾ ዛቬርም ሲናገር ምንም መደናገጥ የለባችሁም፣ በርትታችሁ ወደ ፊት መጓዝን ቀጥሉ፣ ትናንሽ ነገሮችን ሳትንቁ ለመቀበል ትጉ፣ እርሱም መለኮታዊ ሃይል ነው። አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን የሚጀምረው ከትንሽነት ነው። ጸሎታችን አቅመ ደካማነታችንን በመገንዘብ፣ ሃይል እና ድጋፍ እንደሚያስፈልገን በመረዳት የምናቀርብ ከሆነ መልስ እንገኛለን”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በተነበቡት የቅዱሳት መጽሐፍት ላይ ባደርጉት አስተንትኖ፣ ደካማነታችንን እና ትንሽነታችንን ተገንዝበን ለምናቀርበው ጸሎት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጠንን ታላቅነት፣ ሃይል እና ብርታት ለመቀበል ፍርሃት ሊይዘን አይገባም በማለት የዕለቱን አስተምህሮአቸውን አጠቃልለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 December 2019, 16:35
ሁሉንም ያንብቡ >