ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት   (Vatican Media)

ሁላችንም ሟቾች እንደ ሆንን በማሰብ ሕይወታችንን መኖር ያስፈልጋል!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ለተገኙ ቄሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመና በኅዳር 19/2012 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት ከሉቃስ ወንጌል 21፡29-33 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “ሰማይ እና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም” በሚለው የምጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ዙሪያ ላይ መስረቱን ያደረገ ስብከት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ሁላችንም ሟቾች እንደ ሆንን በማሰብ ሕይወታችንን መኖር ያስፈልጋል ብለዋል።

የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት -ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በእለቱ ያደረጉት ስብከት እያንዳንዳችን በመጨረሻው ቀን ስለሚያጋጥመን ፍርድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን እኛን አንድ በሚያደርገን እና የማይቀር በሆነው በሞታችን ቀን ጌታን ለማግኘት በመተማመን ለእዚህ ጥሪ ጥሩ ምላሽ እንድንሰጥ እርስ በርሳችን አንዱ ለአንዱ ሊጸልይ ይገባል ብለዋል።

በቤተክርስቲያኗ የአምልኮ ስነ-ስረዓት የቀን አቆጣጠር ደንብ መሰረት የላቲን ስረዓተ አምልኮ በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አሁን የምንገኝበት ወቅት የዓመቱ ሥረዓተ አምልኮ የመጨረሻው ሣምንት ላይ መሆናችን የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ ሳምንት በስርዓተ አምልኮ ወቅት የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት በዓለም፣ በቤተክርስቲያን፣ በእያንዳንዳችን መጨረሻ ሕይወታችን ዘመን ላይ የሚከሰቱትን እና የሚንጸባረቁትን አብይት ተግባራት እና ክስተቶች የሚገልጹ ምልእክት ያላቸው ንባባት እንደ ሚነበቡ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት በእለቱ የተነበበው የእግዚኣብሔር ቃል ኢየሱስ “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” በማለት የእርሱ ቃል ዘለዓለማዊ መሆኑን እና የተቀሩ ነገሮች በሙሉ ሀላፊ መሆናቸውን ያስረዳል።

የሰው ልጅ ተጋላጭነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ሁሉም ነገር ያልፋል ነገር ግን “እርሱ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል” ማለታቸው የተገልጸ ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ሁሉም ሰው በመጨረሻው የፍርድ ጊዜ ላይ እንዲያሰላስል ለመጋበዝ ተነሳሽነት እንዲወስዱ ቅዱስነታቸው በትህትና ጥሪ አቅርበው ማናችንም ቀኑ መቼ እንደሚሆን በትክክል የምናውቀው ነገር የለም፣ በእርግጥም ይህንን በተመለከተ ኢየሱስ ራሱ አመልክቷል - ብዙውን ጊዜ ራሳችንን ዘለዓለማዊ አድርገን እናስባለን፣ ነገር ግን ነገሩ እንደዚህ አይደለም፣ ሁላችንም መጨረሻ አለን መጨረሻ የሌለው የእግዚኣብሔር ቃል ብቻ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህንን ሐሳባቸውን ለማጽናት በማሰብ የሚከተለውን ብለዋል . . .

ሁላችንም ይህ የህይወት ድክመት ፣ ይህ ተጋላጭነት አለን። ትናንት በዚህ ላይ እያሰላሰልኩ ነበር፣ አሁን እኛ ሁላችንንም ስለሚያግጥመን ተጋላጭነት የሚያወሳ አንድ ደስ የሚል ጽሑፍ ትላንትና ማታ ሳነብ ነበር።  ሁላችንም ተጋላጭ ነን እናም በተወሰነ ደረጃ ይህ ተጋላጭነት ወደ ሞት ይመራናል። አካላዊ ተጋላጭነቴ ምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንደ ሚገኝ ለማወቅ ካለን ፍላጎት የተነሳ ወደ ሕክምና ባለሙያ እንሄዳለን። ሌሎቹ ደግሞ በስነ-ልቦና ረገድ ያላቸውን ተጋላጭነት ለማወቅ እና ለመፈወስ በማሰብ ወደ ስነ-ልቦና ባለሙያ ይሄዳሉ።

ዘለዓለም እኖራለሁ በሚል ቅዤት ውስጥ መኖር

በእዚህ ረገድ ተጋላጭነት ሁላችንንም አንድ ያደርገናል፣ ምንም ዓይነት ቅዤት ከእዚህ ነጻ ሊያደረግን በፍጹም  አይችልም። “በምድር ላይ” አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሐሳባቸውን በሚገባ ለማስረጽ በማሰብ “ለቤተሰባችን ገንዘብ ለመቆጠብ በማሰብ ገና ሳንሞት ለቀብር ቦታችን የሚሆን ቦታ ለመግዛት እንቸኩላለን። በአንዳንድ የቀብር ስነ-ስረዓት አስፈጻሚዎች አማካይነት የተፈጸመው የማጭበርበር ሁኔታ በይፋ እየተገለጸ መጥቱዋል፣ እኛ ዘለዓለማዊ እንደ ሆንን አድርጎ የሚሰማን የቅዤት ስሜት ከዬት የመጣ ነው? ሞት የማይቀር እዳ መሆኑን እና እርግጠኛ የሆነ ጉዳይ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው። ጌታ ግን ሁል ጊዜ ለእኛ “ከእርሱ ጋር መገናኘት” እና “ተስፋ” ማደርግ እንደ ሚገባን የሚገልጸውን የማጻናኛ ቃል ይናግረናል” ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል . . .

ጌታ ከእርሱ ጋር በምንገናኝበት ወቅት ለምንናግረው ነገር ዝግጁ እንድንሆን ይጠይቀናል፣ ሞት ከእርሱ ጋር የምንገናኝበት ወቅት ነው፣ እርሱም ሊጎበኘን ይመጣል፣ እርሱም እኛን በእጃችን ይዞ ይወስደናል። ይህ ቀለል ያለ የእኔ ስብከት በቅብር ሥፍራ ላይ የሚድረግ ዓይነት ስብከት መስሎዋችሁ እንዲሰማችሁ አልፈልግም! ይህ በቀላሉ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰ ነገር ነው፣ ሕይወት ነው ፣ እሱ በቀላሉ ለእኛ የተሰጠን ማሳሰቢያ ነው፣ ሁላችንም ተጋላጭ ነን፣ ሁላችንም አንድ ቀን ጌታን ለመገናኘት የሚያስችለንን አንድ በር አቋርጠን ማለፋችን አይቀሬ ነው።

 

ለጌታ መምጣት በደንብ ለማዘጋጀት መጸለይ ይገባል!

ስለሆነም የበሩ ደወል በሚጮህበት ጊዜ እና ጌታ በሩን በሚያንኳኳበት ወቅት ለመክፈት ያስልቸን ዘንድ በቅድሚያ በደንብ መዘጋጀት ያስፈልጋል፣ ለሚመጣው ጌታ በልበ ሙሉነት በሩን መክፈት ያስፈልጋል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል . . .

ካከማቸናቸው፣ ካስቀመጥናቸው፣ ከሰበሰብናቸው መልካም ከሚባሉ ነገሮች መካከል ይዘነው የምንሄደው ምንም ንገር የለም፣ የሚያጋጥመን እና የሚወስደን የጌታ እቅፍ ብቻ ነው። ስለራሳችን የሞት ቀን ማሰብ፣ መቼ ነው የምሞተው? ብለን ጥያቄ ለራሳችን ማቀረብ ወሳኝ ነው። የእኛ የሞት ቀን በቀን መቁጠሪያ ሰሌዳ ላይ የተካተተ አይደለም፣ የሚያውቀው ጌታ ብቻ ነው። እናም ወደ ጌታ ጸልዩ- “ጌታ ሆይ ፣ በጥሩ ሁኔታ ለመሞት በሰላም ለመሞት፣ በተስፋ ለመሞት ልቤን አዘጋጀ” በማለት ልንጸልይ ይገባል። ይህ ቃል ሁል ጊዜ ከሕይወታችን ጋር አብሮ መኖር ያለበት ቃል ነው። እዚህ ቃላት በመጪው ዓለም ከጌታ ጋር ለመኖር ያለንን ተስፋ ያነሳሳልናል፣ አንዱ ለአንዱ ሊጸልይ ይገባል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 November 2019, 14:11
ሁሉንም ያንብቡ >