ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ከግብዝነት ነፃ የምንሆነው በእግዚአብሔር ፊት እራሳችንን መውቀስ ስንችል ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 4/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከተ ወንጌል በእግዚአብሔር ፊት እራሳችንን መውቀስ ብንችል ኖሮ ከግብዝነት ሕይወት ነፃ እንወጣ ነበር ብለዋል። ከሉቃ. 11፤ 37-41 በተነበበው የዕለቱ ወንጌል ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው ከግብዝነት ሕይወት ራሳችንን ማላቀቅ እንደሚገባ አሳስበው መንገዱም በእግዚአብሔር ፊት እራስን አቁሞ በመክሰስ በመውቀስ እንደሆነ አስረድተው ይህን ማድረግ የማያውቅ ክርስቲያን ጥሩ ክርስቲያን  አይደለም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት ስብከታቸው የግብዝነት ሕይወትን የተመለከቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚከተለው የወንጌል ጥቅስ ላይ አስተንትነዋል። “ኢየሱስ ንግግሩን እንደ ጨረሰ፣ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምግብ እንዲበላ ጋበዘው፤ እርሱም አብሮት ገብቶ በማእድ ተቀመጠ። ፈሪሳዊውም ኢየሱስ ከምግብ በፊት እጁን እንዳልታጠበ ባየ ጊዜ ተደነቀ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጫዊ ክፍል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በስስትና በክፋት የተሞላ ነው። እናንት ሞኞች፤ የውጪውን የፈጠረ የውስጡንም አልፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል”(ሉቃ. 11: 37-41)።

ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዝነትን የማይቀበል መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው ኢየሱስን ወደ ምሳ የጋበዘው ፈሪሳዊ ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነትን ለመፍጠር ተመኝቶ ሳይሆን በእርሱ ላይ ሊፈርድበት ፈልጎ እንደሆነ ገልጸው ግብዝነት ትክክለኛውን ማንነት የሚጋርድ የማስመሰል ሕይወት ነው ብለዋል።

የግብዝነት ምንጭ ሰይጣን ነው፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ለግብዝነት ቦታን ካለመስጠቱ የተነሳ ፈሪሳዊያንን ግብዞች ብሎ እንደሚጠራቸው የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ማለቱ ሊሰድባቸው ወይም በሃሰት ስማቸውን ለማጥፋት ፈልጎ ሳይሆን እውነቱን ለመናገር ፈልጎ ነው ብለዋል። ግብዞች በውጭ ገጽታቸው የጸዱ፣ ጻድቃንም የሚመስሉ፣ ውስጣቸው ሲታይ ግን ሙሉ በሙሉ የተለዩ ናቸው ብለው ይህን ድብቅ ማንነት የሚቀበሉት ራሱም ውሸታም ከሆነው ከሰይጣን እንደሆነ አስረድተው ሰይጣን ቀዳሚ ግብዝ እንደሆነ እና በመካከላችን የምናያቸው ግብዞችም የእርሱ ወራሾች ናቸው ብለዋል።

ግብዝነት በራሱ የክፉ መንፈስ ባህሪ ነው፤ ይህን የክፉ ሥራ ባሕሪ በልባችን ውስጥ የሚዘራው ሰጣን ነው። ከግብዞች ጋር አብሮ መኖር መልካም ባይሆንም በመካከላች አሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞችን ማጋለጥ እና መውቀስ ይፈልጋል። የግብዝነት ሕይወት ሰዎችን ወደ ሞት እንደሚወስዳቸው በሚገባ ያውቃል። ምክንያቱም ግብዝ ሰው ትክክለኛ በሆነ መንገድ ይጓዝ ወይም አይጓዝ ለይቶ ስለማያውቅ ወደ ፊት መጓዝን ብቻ ያያል። ሥራው ስም ማጥፋት ከሆነ ስምን ማጥፋት፣ ሐሰተኛ ምስክር ማቅረብ ከሆነ ሐሰተኛ ምስክሮችን መፈለግ ነው።               

ግብዝነት ገዳይ መርዝ ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን በመቀጠል አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በመካከላቸው ግብዝነት የለም ብለው ሊከራከሩ እንደሚችሉ ገልጸው እንዲህ ማሰብ በራሱ ትልቅ ስህተት ነው ብለዋል።

የግብዝነት ቋንቋ ትክክል ያልሆነ የዕለተ ዕለት ገጠመኛችን ነው። በውጭ ገጽታ ጥሩ መስሎ መታየት፣ ውስጥ ሲታይ ግን ሌላ ሆኖ መገኘት፣ ለስልጣን መታገል፣ ቅናት እና ምቀኝነት፣ እነዚህ ክፉ ባሕሪያት ሰዎችን የሚገዱ ውስጣዊ የግብዝነት መርዞች ናቸው። የሚዘገይ ቢሆንም ግብዝነት ምሕረት የማያደርግ የሚገድል መርዝ ነው።     

ለግብዝነት መድሐኒቱ እራስን መውቀስ ነው፣

ከግብዝነት ሕይወት መውጣት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ “መውጫ መንገድስ የት አለ”? በማለት ጠይቀዋል። ባቀረቡት መልሳቸው ከግብዝነት ሕይወት መውጣት የሚቻለው እውነተኛ መንገድን በመከተል እና በእግዚአብሔር ፊት ቆመን እራሳችንን መውቀስ ስንችል ነው ብለዋል።

እራሳችንን መውቀስ እና በራሳችን ላይ ክስ ማቅረብ መማር አለብን፤ “ክፉ ሥራን ሰርቻለሁ፣ ክፉ አስቤአለሁ፣ በቅናት እና በምቀኝነት ተነሳስቼአለሁ፣ በዚህ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ አለብኝ” በማለት በውስጥ ያለውን ክፋት በሙሉ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ራስን በመውቀስ መናገር ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ወደ እግዚአብሔር ፊት መቅረብ ያልተለመደ ቢሆንም በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ መለማመድ ያለብን ሕይወት ነው። እራሳችንን መውቀስ፣ በራሳችን ላይ ክስን ማቅረብ፣ እራስን ሃጢአተኛ ማድረግ፣ እራስን ግብዝ ማድረግ፣ ልባችን በደልን ለማድረግ የሚያስብ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ወደ እግዚአብሔር ፊት መቅረብ ያለብን አንደኛው ምክንያት ሰይጣን በልባችን ውስጥ ክፋትን ስለሚዘራ እና በክፉ ሥራችን ተጸጽተን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንዳንቀርብ ስለሚያደርገን ነው። ነገር ግን እኛ ወደ እግዚአብሔር ፊት በትህትና መቅረብን መማር ይኖርብናል።  

ጴጥሮስ ኃጢአተኛ መሆኑን አመነ፣

እራሳችንን መውቀስ መማር ይኖርብናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ምናልባትም ከባድ መስሎ ቢታየንም፥ ይህን ማድረግ በእግዚአብሔር ፊት እራስን አቁሞ መክሰስ እና መውቀስ የማያውቅ ክርስቲያን ጥሩ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም ብለዋል። በግብዝነት ሕይወት በቀላሉ ሊወድቅ ይችላል ብለዋል። ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ “ጌታ ሆይ ሐጢአተኛ ስለሆነኩ ወደ እኔ አትቅረብ” በማለት ያቀረበውን ጸሎት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ “ጌታ ሆይ እራሳችንን መውቀስ እንድንማር እርዳን” በማለት ስብከተ ወንጌላቸውን ፈጽመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 October 2019, 17:49
ሁሉንም ያንብቡ >