የእስያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊነት ሂደት አህጉራዊ ምዕራፍ የእስያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊነት ሂደት አህጉራዊ ምዕራፍ 

የእስያ አህጉር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊነት ጎዳናን ለመራመድ መዘጋጀቷን ገለጸች

በእስያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአህጉራዊ ምዕራፍ ባካሄዱት የሲኖዶሳዊነት ስብሰባ ያገኟቸውን የእስያ ጥንታዊ ባሕል እና ልማድ መሠረት ያደረጉ መልሶችን በሰነድ ይፋ አድርገዋል። ሰነዱ የእስያ ቤተ ክርስቲያናት የሲኖዶሳዊነት ጎዳናን ለመራመድ መዘጋጀታቸውንም ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእስያ አህጉር የጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን፣ በሲኖዶሳዊነት ላይ መጋቢት 7/2015 ዓ. ም. ያደረጉት የአህጉራዊ ምዕራፍ ስብሰባ የመጨረሻ ሠነድን ይፋ አድርጓል። ሠነዱ በአህጉሪቱ የሚገኙ የ17 ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ የሁለት ምሥራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶሶች፣ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዝዳንቶች እና ልዑካን በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ውስጥ ከየካቲት 17-19/2015 ዓ. ም. ባካሄዱት አህጉራዊ የሲኖዶሳዊነት ጉባኤ ላይ የሰጡት ምላሾች ውህደት ፍሬ እንደሆነ ተነግሯል።

እስያ ለአህጉራዊ ሰነድ የሰጠችው ምላሽ

የእስያ አህጉር ወደ 4.6 ቢሊዮን ሰዎች የሚገኙባት እና አብዛኛው የዓለማችን ቢሊየነሮች የሚኖሩባት ስትሆን፣ ከእነዚህም 150 ሚሊዮን ወይም ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል 3.31% የሚገመት ካቶሊክ ምዕመናን የሚኖሩባት አህጉር ናት። የአህጉራዊ ምዕራፍ ጉባኤ የመጨረሻ ሰነዱ፣ በአህጉሪቱ የሚገኙ ካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር አናሳ ቢሆኑም፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ፣ በማኅበራዊ ደኅንነት እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ድሆችን እና የተገለሉ ቡድኖችን በመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦን እንደምታበረክት በመግቢያው ላይ ገልጿል።

በእስያ አህጉር ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሲኖዶሳዊነት ሂደት፣ በጥቅምት ወር 2015 ዓ. ም. ከተካሄደው የእስያ አህጉር የጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን 50ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጋር የተገጣጠመ እንደሆነ ተመልክቷል። አንዳንድ አገሮች ከተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎች የተውጣጡ በርካታ ምዕመናንን ማሳተፍ የቻሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ጥቂት ምዕመናንን ማሳተፍ መቻላቸውን የመጨረሻ ሰነዱ አስታውቋል። የአህጉራዊ ምዕራፍ ሰነድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የተገደበበት አንዱ መንገድ “በእስያ አህጉር በሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች ተተርጉሞ አለመቅረቡ ነው” ተብሏል። በሲኖዶሳዊነት አህጉራዊ ምዕራፍ ሰነድ ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን ያለው ጥልቅ ፍቅር፣ እንደ ደስታ፣ ሐዘን፣ ተጋላጭነት እና መቁሰል የመሳሰሉ የተለያዩ ስሜቶች በቀዳሚነት ተገልጸዋል።

በእስያ የተካሄደው የሲኖዶሳዊነት ሂደት በአህጉሪቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የበለጸጉ ባህሎቻቸውን በይፋ እንዲያሳዩ ያገዘ ሲሆን፣ እንዲሁም በእስያ የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች እምነታቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት የሚሰነዘሩባቸው የተለያዩ ዛቻዎች እውነታ የበለጠ እንዲታወቅላቸው አስችሏቸዋል።

በእስያ አህጉር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከሚታዩ ቁስሎች መካከል ጥቂቶቹ፥ “ከገንዘብ፣ ከሥልጣን፣ ከሕሊና እና ከጾታ ጋር የተያያዙ በደሎች፤ ሴት ምዕመናንን በአስተዳደር እና በውሳኔ ሰጭነት ቦታ ላይ በበቂ ሁኔታ ማካተት አለመቻል፤ በቂ ሐዋርያዊ አገልግሎት ማቅረብ አለመቻል እና የግንዛቤ ማነስ” የሚሉት ይገኙበታል። ለምዕመናን የሚሰጥ በቂ ሐዋርያዊ አገልግሎት አለመኖር እና መልካም አቀባበል አለመደረግ፣ እንደ ግለኝነት፣ ስግብግብነት እና ፍቅረ ንዋይን የመሳሰሉ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች ሰርገው መግባት እና የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ የሚያፍኑ ጨቋኝ መንግሥታት መኖራቸውን ሰነዱ ጠቅሷል።

አዲስ ጎዳና ላይ መጓዝ

እነዚህ ቁስሎች ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ወደ አዲስ ራዕይ እንድትሸጋገር ዕድሎችን እንደሚያመቻቹላት የገለጸው የአህጉራዊ ምዕራፍ ሰነዱ መልዕክቱን በመቀጠል፣ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ሰው በመቀበል የአንድነት እና የኅብረት መንፈስ እንዲኖር ማድረግ መጀመር እንዳለባት አሳስቦ፣ እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ማንም ሊገለል እንደማይገባ፣ አቅመ ደካሞች ቢሆኑም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማካተት ለሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን የግድ እንደሆነ ሰነዱ አስገንዝቧል።

በእስያ አህጉር የሚታዩ የጋራ ውጥረቶች

የእስያን ቤተ ክርስቲያን ከመሠረቱት ልዩ ልዩ እውነታዎች መካከል ትክክለኛ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በሚያደርግ የምስጢረ ጥምቀት ጥሪ እንዳይኖሩ የሚከለክሉ የአመራር ዘይቤዎች መኖራቸውን የገለጸው የአህጉራዊ ምዕራፍ የመጨረሻ ሰነዱ፣ በአህጉሩ ሕዝቦች መካከል መከፋፈል እንዳለ ገልጿል።

ይህን ማሸነፍ የሚቻለው ለምዕመናን ወገን የአገልግሎት ቦታዎችን በማስፋት፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረግ፣ በስልጣን አጠቃቀም ተጠያቂነት እና ግልጽነት እንዲኖር ማድረግ፣ የክህነት ጥሪ ማነስ እና በቤተ ክርስትያን ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎ ማነስን የመሳሰሉ ክስተቶችን እንደገና መገምገም እንደሚያስፈልግ እና የተለያዩ የድህነት ዓይነቶች የሚያጋጥሟቸው ሰዎችን በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ማካተት እንደሚያስፈልግ፣ ሌሎችን ውጥረቶች እና ከሃይማኖታዊ ግጭቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የአህጉራዊ ምዕራፍ ጉባኤ መመልከቱን የመጨረሻ ሰነዱ ገልጿል። 

28 March 2023, 16:57