በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት ክቡር አቶ ዣን ፋብር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት ክቡር አቶ ዣን ፋብር 

እምነትን በማጠንከር ሰላምን መገንባት እንደሚገባ ተነገረ

በጣሊያን ውስጥ አሲሲ ከተማ ከመስከረም 12-14/2015 ዓ. ም. ድረስ ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፣ የምጣኔ ሃብት ሥርዓትን ለማደስ የሚያግዙ ውይይቶች ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ስብሰባውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት ክቡር አቶ ዣን ፋብርም መካፈላቸው ታውቋል። የልማት ዳይሬክተሩ ለስብሰባው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር በሥርዓቱ ላይ ለውጦችን ማካሄድ እንደሚቻል ገልጸዋል። አክለውም ማናቸውንም የልማት ዕቅዶች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል ገልጸው፣ ይህን ለማድረግ ግን ከሁሉ አስቀድሞ እምነት እና ሰላም ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የፊዚክስ ትምህርት እንዳጠኑ የተናገሩት አቶ ዣን ፋብር፣ ቀጥለውም በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው መሥራታቸውን ገልጸው፣ ሆኖም ግን የምርምር ሥራዎቻቸው ለጦር ሠራዊት ይቀርብ እንደ ነበር አስታውሰዋል። “በአንድ ወቅት የሰዎችን ሕይወት ቶሎ ለማጥፋት አለመወለዴን ተገነዘብኩ” ያሉት አቶ ዣን ፋብር፣ የተወለዱትም “ሰብዓዊ ቤተሰብ የበለጠ አንድ እንዲሆን ለመርዳት እንጂ ሕይወትን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት ለመርዳት አልተወለድኩም” በማለት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ማኅበራዊ ምጣኔ ሃብት እና አብሮነትን ​​ለማሳደግ የሚሠራ ቡድን አባል መሆናቸውን ተናግረው፣ እውነታው ከቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት መርሆዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ጥሪ ማቅረባቸውን በሰሙ ጊዜ እና ወጣቶቹን በበላይነት ለመርዳት ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ በተለይም ተነሳሽነቱ አዎንታዊ መሆኑን በማመናቸው እንቅስቃሴውን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ክቡር አቶ ዣን ፋብር፣ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

ለወጥን ማምጣት ይቻላል!

የምጣኔ ሃብት ሥርዓትን እንደገና የማጤን ተልዕኮ በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ተነሳሽነት የተጀመረ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ መሆኑ ይታወቃል። “የዘመኑን የምጣኔ ሃብት ሥርዓት መለወጥ ይኖርብናል” ያሉት ክቡር አቶ ዣን ፋብር፣ ይህን ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ እና እንቅፋት የሚሆኑ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ይህም በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች ያለ ቢሆንም፣ ነገር ግን የሰዎችን መልካም ተነሳሽነት ለማዳበር ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በሁሉም አካባቢዎች በምጣኔ ሃብት ዙሪያ የሚታዩ አስከፊ ገጽታዎችን መለወጥ የሚቻል መሆኑን የገለጹት አቶ ዣን ፋብር፣ በየዕለቱ በሚደረጉ ትክክለኛ ምርጫዎች በመታገዝ መልካም ለውጦችን ማምጣት እንደሚቻል እና አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።   

“ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ይቻላል” ያሉት አቶ ዣን ፋብር፣ እምነት ሊኖረን እንደሚገባ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ያስተማረን መሆኑን ተናግረዋል። ልዩ  ልዩ ሃይማኖቶች ቢኖሩም እውነተኛ እምነት ሊኖር እንደሚገባ፣ በራስ እና በሌሎች ላይ እምነት በማሳደር የፍቅር ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ አክለው ተናግረዋል። የጋራ ሰላም ፣ ፍትህ እና ደህንነት ሊመሠረት የሚችለው እርስ በርሳችን ስንተሳሰብ እንደሆነ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት ክቡር አቶ ዣን ፋብር፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

24 September 2022, 16:47