ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሰሞኑን በጎንደር የተከሰተውን ግጭት አወገዘች

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት በጎንደር ከተማ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሼህ ኤሊያስ የቀብር ስነ ስርዓት ወቅት ተቀስቅሶ ለበርካቶች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው ግጭት በኢትዮጵያ ሃይማኖቶች መካከል የቆየውን አብሮ የመኖር እና የመቻቻል ባህል ፈጽሞ የሚጻረር ተግባር በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ የምታወግዘው መሆኑን ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተለይ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች የዐብይ እና የረመዳንን ጾም በጋራ በመጾም እና በጸሎት ቆይተው የትንሳኤ ብርሃን በመላው ሃገሪቱ በሚያበራበት እንዲሁም ሙስሊም ወንድሞቻችን ታላቁን የረመዳን ጾም ቀጥለው ባሉበት በዚህ ወቅት ይህ በመፈጠሩ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን እጅግ ያሳዘናት መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም ልጆቻችንን ከመሰል የጥፋት ተግባራት መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን በመግለጽ ወጣቶች የወላጆቻቸውን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን ምክር በመስማት እና እንዲሁም እርስ በእርስም በመደማመጥ ለበለጠ ልማት መሰለፍ እንደሚገባቸው አደራ ጭምር አሳስበዋል።

ብፁዕነታቸው አያይዘው በባህር ዳር ደሴ ካቶሊካዊ ሰበካ ስር በጎንደር የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች በስልክ ያነጋገሩ መሆኑን እና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአካባቢው ያሚኖሩ ማሕበረሰቦች ሁኔታውን በረጋ መንፈስ በማጤን ሰላም እና ዕርቅ የሚሰፍንበትን ሁኔታ በማመቻቸት የደረሱበትን እጅግ በፈጠነ ሁኔታ እንደሚያሳውቁን ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በመጨረሻም በግጭቱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችንም ፈጣሪ በመንግሥቱ እንዲቀበላቸው እና ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲልክላቸው የሚመኙ መሆኑን ገልጸዋል።

29 April 2022, 09:57