ሕገ-ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል በዋናነት ሴቶችን እና ህጻናትን ያጠቃል ሕገ-ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል በዋናነት ሴቶችን እና ህጻናትን ያጠቃል 

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋት ኤኮኖሚን እና የሥራ ዕድልን ማሳደግ ይገባል ተባለ

የካቲት 1/2014 ዓ. ም የተከበረውን ዓለም አቀፍ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀንን ምክንያት በማድረግ የጸሎት እና የአስተንትኖ ሥነ-ሥርዓት በበይነ መረብ አማካይነት መካሄዱን “ታሊታ ኩም” የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት አስታውቋል። ይህን የጸሎት እና የአስተንትኖ ሥነ-ሥርዓት የተሳተፉ በሙሉ፣ በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመውን አስከፊ ገጽታ በጽኑ እንደሚቃወሙት ገልጸዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከአምስቱ አኅጉራት የተመረጡ እና ከባርነት ሕይወት የተላቀቁ ሴቶች ምስክርነት መስጠታቸው ወንጀሉን ለመቃወም እና የአንድነት ባሕልን ለማሳደግ መልካም ምሳሌ መሆኑ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሕገ-ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል "በሰው ልጅ ላይ ጥልቅ የሆነ ቁስልን" በዋናነትም ሴቶችን እና ህጻናትን እንደ ዕቃ እንዲሸጡ የሚያደርግ ነው” በማለት፣ ዓለም አቀፍ የገዳማውያት አለቆች ኅብረት ፕሬዝዳንት፣ እህት ዮላንታ ካፍካ ገልጸዋል። በአውታረ መረብ ላይ የጸሎት እና የአስተንትኖ ሥነ-ሥርዓት መጀመሪያ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት እህት ዮላንታ፣ “የእንክብካቤ ኃይል” የሚለው የዘንድሮ ዓለም አቀፍ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን መሪ ቃል መሆኑን ገልጸው፣ ቅድስት ዮሴፒና ባኪታን በማስታወስ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጸሎት መተባበር እና ይህን አስከፊ ሕይወት ለማስወገድ በኅብረት መቆም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ከዓለም ዙሪያ የቀረቡ ምስክርነቶች

ከስምንት ሰዓት በላይ በዘለቀው የአውታረ መረብ ላይ የጸሎት እና የአስተንትኖ ሥነ-ሥርዓት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የተካፈሉ ሲሆን፣ መላው ዓለም በኅብረት በመቆም ይህን በሰው ልጆች ላይ የሚደርስ አስከፊ ሕይወትን መቃወም እንደሚገባ በቪዲዮ መልዕክታቸው አስገንዝበዋል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሰለባ የሆኑት ቢያንስ 40 ሚሊዮን ሰዎች መኖራቸው ተገልጿል። ከጥቃቱ ያመለጡት ከአምስቱ አህጉራት የተወጣጡ ሴቶች ምስክርነት መስጠታቸው፣ የማኅበሩ በጎ ፈቃደኞች የሚያቀርቡት ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ የጥቃቱ ሰለባ የነበሩ ሰቶች ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ መልካም እና ውጤታማ አገልግሎት መሆኑ ተገልጿል።

ዋና ተዋናዮች መሆን

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መምሪያ ሐላፊ ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ፣ ከጸሎት እና አስተንትኖ ዝግጅት አስተባባሪ ማኅበር “ታሊታ ኩም”፣ ከዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት፣ ከዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ሴቶች ማኅበር፣ ከፎኮላሬ እንቅስቃሴ እና ከኢየሱሳዊያን የሰደተኞች መርጃ ድርጅት ጋር በመተባበር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በኅብረት የሚሠሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ የሰው ልጅ በእጅጉ ከቆሰለው አስከፊ ሕይወት መውጣት እና ማገገም እንደሚቻል ካሰረዱ በኋላ፣ በአደጋ ከማዘን ይልቅ አቅምን በማስተባበር በኅብረት መከላከል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ከአፍሪካ ሴቶች መካከል 8% ብቻ ደሞዝ ይከፈላቸዋል

ጦርነት፣ በሽታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ብልሹ አስተዳደር በሚያሰቃያት አፍሪካ፣ በእያንዳንዱ አገር ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል መጋለጣቸው ታውቋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ሴቶች ለልመና፣ ለሴተኛ አዳሪነት፣ ለአካል ክፍሎች እና ለሕፃናት ሽያጭ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በጉዞ ላይ ገደብ መጣሉ አደጋውን እንዳያመልጡ በማገዱ የተጠቂዎችን ቁጥር እጅግ  ከፍ ማድረጉ ታውቋል። በአህጉሪቱ የሚኖሩ ሴቶች የለውጥ ተስፋዎች መሆናቸው ሲነገር፣ 62 በመቶ የሚሆነውን የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ ምርቶችን ሠርተው የሚያቀርቡት ሴቶች ቢሆኑም ደሞዝ የሚከፈላቸው ግን 8 ከመቶ ብቻ እንደሆኑ፣ በቡርኪናፋሶ ውስጥ የቅባት እና ሽቶ ምርቶችን በማምረት ለሴቶች የሥራ ዕድልን የሚያመቻች አንድ የጣሊያን ኩባንያ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑ ታውቋል።    

የመገናኘት ባሕልን ማሳደግ ያስፈልጋል

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው የጤና ቀውስ ምክንያት ከሥራቸው የተወገዱ 13.5 ሚሊዮን ሰዎች እንዳሉ የተገመተ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በሺዎች እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል። የጋራ መረጃ ማዕከል ባለመኖሩ ምክንያት ትክክለኛ አሃዝን ማወቅ ባይቻልም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2017/2020 ዓ. ም ሪፖርት መሠረት በአሥራዎች የሚቆጠሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸው ተመልክቷል። ከእነዚህ የመብት ጥሰቶች መካከል ጾታዊ የጉልበት ብዝበዛ፣ የባርነት፣ የአካል ክፍሎች እና የሕፃናት ሽያጮች መከናወናቸው ታውቋል።   ሕገ-ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ዓለም አቀፋዊ ችግር እንደሆነ ግልጽ በመሆኑ ይህን ማኅበራዊ ችግር ለማቃለል “ዓለም አቀፍ የጋራ ተግባር” ሊኖር እንደሚገባ ያስታወሱት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱሳዊያን ማኅበር ጠቅላይ አለቃ የሆኑት ክቡር አባ አርቱሮ ሶሳ፣ “የመናቅ እና የማግለል ባሕልን” በማስቀረት በምትኩ “የአንድነት እና እርስ በእርስ የመገናኘት ባሕልን” ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

10 February 2022, 16:23