እህት ትሪኒዳድ የቤተክርስቲያን ሥራ ማኅበር መስራች እህት ትሪኒዳድ የቤተክርስቲያን ሥራ ማኅበር መስራች 

እህት ትሪኒዳድ፣ ለቤተክርስቲያን ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው

በሮም ከተማ ውስጥ ሐምሌ 21/2013 ዓ. ም ያረፉት እህት ትሪኒዳድ፣ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማኅበር መሥራች የነበሩ እና ጥልቅ የቤተክርስቲያን ፍቅር የነበራቸው መሆኑ ታውቋል። እህት ትሪኒዳድ፣ በሕይወት ዘመናቸው በዓይን የተመለከቷቸውን እና የተረዱትን የቅድስት ሥላሴን ምስጢራት ጽፈው በማስቀመጥ ለመጭው ትውልድ አስረክበዋል። በጣሊያን የቶሪኖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኖሲሊያ፣ በእህት ትሪኒዳድ ጸሎተ ፍትሃት ዕለት ባሰሙት ስብከት “እህት ትሪኒዳድ ለተከታዮቻቸው ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው ናቸው” በማለት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እህት ትሪኒዳድ የመሠረቱት የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማኅበር አባላት በጣሊያን፣ በስፔን፣ በላቲን አሜሪካ እና አፍሪካ ውስጥ በአንዳንድ አገሮች እንደሚገኙ ታውቋል። እህት ትሪኒዳድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጉብኝት ሥራ ምሳሌ በመከተል በስፔን-ማድሪድ ከተማ ጎዳናዎች የሚገኙ ዕርዳታ ፈላጊዎችን ለመጎብኘት የሚያግዝ አንድ ጥንድ ጫማ መጠቀማቸው ከአገልግሎታቸው መካከል በተጨባጭ የሚጠቀስ መሆኑን በእህት ትሪኒዳድ ጸሎተ-ፍትሃት ዕለት ስብከታቸውን ያቀረቡት የቶሪኖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቸዛሬ ኖሲሊያ ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ቸዛሬ በስብከታቸው፣ እህት ትሪኒዳድ በሙሉ ፈቃድ ለቤተክርስቲያን እንዲታዘዙ ያደረጋቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር መሆኑን አስረድተዋል። በስፔን ዶስ ሄርማናስ (ሲቪሊያ) ከተማ ከካቶሊካዊ ቤተሰብ እ. አ. አ የካቲት 10/1929 ዓ. ም የተወለዱት እህት ትሪኒዳድ፣ በቤተሰባቸው የልብስ መሸጫ መደብር ውስጥ ይሠሩ እንደነበር አባ በርተሎሜዎስ ቫልቡዌና ግራሲያ ገልጸዋል። እህት ትሪኒዳድ በዚህ ሥራ ላይ እያሉ በ17 ዓመት ዕድሜያቸው የሕይወት አቅጣጫን እንዲቀይሩ ያደረጋቸውን ጥሪ መቀበላቸውን አባ በርተሎሜዎስ አስረድተዋል። እህት ትሪኒዳድም በመጽሐፋቸው “የእኔ ጥሪ ቤተክርስቲያን መሆንና እያንዳንዱን ሰው ቤተክርስቲያን ማድረግ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ከር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተቀሉት ቡራኬ

የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጅ የሆነች እህት ትሪኒዳድ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማኅበርን በማድሪድ ሀገረ ስብከት የመሠረቱት እ. አ. አ በ1967 ዓ. ም ሲሆን ወደ ጣሊያን ይዘው የመጡት በታኅሳስ 20/1997 ዓ. ም መሆኑ ይታወሳል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማኅበር ከቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት መካከል አንዱ በማድረግ የማኅበሩን ደንብ ፈርመው ማጽደቃቸው ይታወሳል። ይህ ከመሆኑ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘውን እና በቤተክርስቲያን አገልግሎት ማኅበር የሚመራውን የቫልሜ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ቁምስናን እ. አ. አ በታኅሳስ 15/1996 ዓ. ም መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የቤተክርስቲያን አገልግሎት የካኅናት ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ ፍራንችስኮስ ሳቨሪዮ ቪቼንቴ የእህት ትሪኒዳድ ጥልቅ ሥነ-መለኮታዊ የቤተክርስቲያን ፍቅር ሲገልጹ፥ እህት ትሪኒዳድ በ17 ዓመት ዕድሜያቸው፣ ከጽንሰታ ለማርያም ክብረ በዓል አንድ ቀን አስቀድሞ ከእግዚአብሔር ጥሪ መቀበላቸውን አስታውሰዋል። የእህት ትሪኒዳድ ጥሪ ልዩ እንደ ነበር የገለጹት አባ ፍራንችስኮስ ሳቨሪዮ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት “የማያልቅ ፍቅር ማግኘት ከፈለግሽ፣ ደስታንም ማግኘት ከፈለግሽ፣ የማያልቅ ፍቅር እና ደስታ እኔ ነኝ” የሚል መልስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተቀበሉ መናገራቸውን አባ ፍራንችስኮስ ሳቨሪዮ አስታውሰዋል። እህት ትሪኒዳድም በበኩላችው “እኔ ሙሉ በሙሉ፣ ሁል ጊዜ ያንተ ነኝ” በማለት ለጥሪው ምላሽ መስጠታቸውንም አስታውሰዋል። እህት ትሪኒዳድ ከእግዚአብሔር ዘንድ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ራስን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት በማቅረብ ዕርዳታቸውን ለማቅረብ የተነሳሱበት፣ ቤተክርስቲያን እንድትታደስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥያቄ የቀረበበት እና ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የተካሄደበት ወቅት መሆኑን አባ ፍራንችስኮስ ሳቨሪዮ አስታውሰዋል።

እህት ትሪኒዳድ ይህን መልዕክት እንዴት ተቀበለች?

ከስፔን ደቡባዊ ክፍለ ሀገር የተገኙት እህት ትሪኒዳድ የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብለው ለአገልግሎት በተሰማሩበት ወቅት ምንም ዓይነት ድጋፍ ያልተደረገላቸው ሲሆን ነገር ግን በማድሪድ የሚገኙ የንስሐ አባታቸው የዘወትር እንቅስቃሴያቸውን ይከታተሉ እንደ ነበር ታውቁል። እ. አ. አ በ1963 ዓ. ም እህት ትሪኒዳድ ለቤተክርስቲያን ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ያለ እንደሆነ በተጠየቁ ጊዜ ካህናትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማዊያትን፣ ተዕኮዋቸውን የሚደግፉ ሰዎችን ማፈላለግ ጀመሩ። እህት ትሪኒዳድ ለዚህ ጥሪ ምላሽ ለማግኘት ብለው ከባድ ችግሮችን  እና መከራዎችን ከተሻገሩ በኋላ እ. አ. አ በ1993 ዓ. ም ወደ ሮም መጡ፤ መልካም አቀባበልም ተደረገላቸው።

እህት ትሪኒዳድ ወደ ሮም ከመጡ በኋላ ከቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር በነበራቸው መንፈሳዊ ግንኙነት ወቅት ከ15-20 ገጾች ያሏቸውን 55 ደብዳቤዎችን መጻፋቸውን እና በእነዚህ ደብዳቤዎች አማካይነት ቤተክርስቲያኗን ለመርዳት ከእግዚአብሔር የተቀበሉት የአገልግሎት ጥሪ ያለባቸው መሆኑን መግለጻቸውን አባ ፍራንችስኮስ ሳቨሪዮ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊም የዚህ አጭር ታሪክ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል።

ማኅበራቸው ከእህት ትሪኒዳድ የወረሷቸው የአገልግሎት ድርሻዎች ሰፊ መሆናቸውን የገለጹት አባ ፍራንችስኮስ ሳቨሪዮ፣ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት እንደሚቻል የሚገልጹ፣ በቤተክርስቲያን ምስጢራት ውስጥ ስላለው እምነተ-አንቀጽ ጥልቅ ዕውቀት የሚናገሩ ከ60 በላይ የስነ-መለኮት መጽሐፍት ጽፈው ማስረከባቸውን፣ በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና ጳጳሳትን በአገልግሎታቸው ለማገዝ የሚረዱ ከአንድ ሺህ በላይ የተመዘገቡ ንግግሮችን አዘጋጅተው ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

11 August 2021, 17:33