የቤተክርስቲያን አንድነት የሚያስረዳ አጭር ትምህርት በአሲሲ ከተማ ተዘጋጅቷል የቤተክርስቲያን አንድነት የሚያስረዳ አጭር ትምህርት በአሲሲ ከተማ ተዘጋጅቷል  

በቤተክርስቲያን አንድነት ላይ የሚወያይ ትምህርታዊ ስብሰባ በአሲሲ ከተማ ይካሄዳል

በጣሊያን፣ አሲሲ ከተማ ከነሐሴ 14-16/2013 ዓ. ም ድረስ በሚቆይ አጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ወቅት፣ የቤተክርስቲያንን አንድነት የሚያስረዳ አጭር ትምህርት የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል። ሦስት ቀናትን የሚወስድ ትምህርታዊ ስብሰባ ዋና ዓላማ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፈለጉት የቤተክርስቲያንን አንድነት የሚያጠናክሩ ባለ ደረጃ ጭብጦችን አዘጋጅቶ እ. አ. አ በ2023 በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ለማቅረብ እንደሆነ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በአንድነት ለመራመድ አንድ ላይ እንሁን” የሚለው መሪ ቃል፣ የቤተክርስቲያንን አንድነት ለማጠናከር የሚያግዝ አዲስ ጥረት ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጀመሩትን የቤተክርስቲያን አንድነት በሚገልጽ መልኩ በማብራራት በተግባር የሚኖሩበትም መሆኑ ታውቋል። በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መርቀው የሚያስጀምሩት እና ከመስከረም 29-30/2014 ዓ. ም የሚቆይ የቅድመ ዝግጅቱ የመጀመሪያ ደረጃ ስብሰባው እ. አ. አ በ2023 በሚካሄድ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወቅት የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል። ከዓመት ወደ ዓመት ፣ ከወር ወደ ወር በየደረጃው የሚደረግ የትምህርት መርሃ ግብሩ እያንዳንዱን የቤተክርስቲያን አባል በማሳተፍ፣ ከተለመደው ሂደት የተለየ እና የዕረፍት ጊዜ ያለው ዝግጅት መሆኑ ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ከመካሄዱ አስቀድሞ በየጊዜው የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች የቤተክርስቲያንን ወቅታዊ እውነታ በማጤን፣ በሀገረ ስብከቶች፣ በቁምስናዎች፣ በገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና በማኅበራት ውስጥ የታቀፉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስሜት የሚገልጽ ነው ተብሏል።

በኮርሱ ላይ ተናጋሪዎች

አሲሲ ከተማ ከነሐሴ 14-16/2013 ዓ. ም ድረስ በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ አጭር ትምህርት፣ ከዚህ በፊት ተቋቁመው የነበሩ ሦስት የዝግጅት ኮሚሽኖች ያሉት፣ የክርስቲያናዊ ከተማ አሲሲ ታሪክን በማካተት ባህላዊነት ያላቸውን ጥናታዊ ትምህርቶችን በማቅረብ አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል። በአሲሲ ከተማ የሚሰጥ የዘንድሮ ኮርስ 79ኛ ዙር ሲሆን መሪ ርዕሡ “በአንድነት ለመራመድ አንድ ላይ እንሁን” የሚል መሆኑ ተገልጿል።

ለሦስት ቀናት በሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ላይ የመግቢያ ንግግር ከሚያደርጉት መካከል የሞደና-ኖናንትሎ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና የካርፒ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤሪዮ ካስተሉቺ፣ ከጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ዋና ጸሐፊ ጋር የቫቲካን ጓዳይ ተመራማሪ ቫንያ ዴ ሉካ፣ የአቤለ እና የሊበራ እንቅስቃሴ መሥራች የሆኑት ሉዊጂ ቾቲ፣ በቱሪን የቫልዴስ ቤተክርስቲያን ፓስተር፣ ማሪያ ቦናፌዴ እና የ “Slow Food” ማኅበር መሥራች አቶ ካርሎ ፔትሪኒ መሆናቸው ታውቋል።

ትምህርቶቹን እንዴት መከታተል ይቻላል?

አሲሲ ከተማ ከነሐሴ 14-16/2013 ዓ. ም ድረስ የሚቆየውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገኝቶ መከታተ የግድ ሲሆን በሚቀጥሉት ጊዜያት የሚደረጉ ውይይቶችን (www.cittadella.org) በሚለው ድረ-ገጽ በኩል የቀጥታ ስርጭትን መከታተል የሚቻል መሆኑ ተነግሯል።   

18 August 2021, 15:37