በጣሊያን ፖጆ ፑስቶኔ ክፍለ ሀገር የሚገኝ ፍራንችስካዊ የንግደት ሥፍራ በጣሊያን ፖጆ ፑስቶኔ ክፍለ ሀገር የሚገኝ ፍራንችስካዊ የንግደት ሥፍራ 

ወጣቶች ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር እጅ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ

ከተለያዩ የጣሊያን ከተሞች ተነስተው ወደ አሲዚ ከተማ መንፈሳዊ የእግር ጉዞ ያደረጉት በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር እጅ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጹ። ወጣቶቹ ወደ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የትውልድ ሥፍራ ወደ ሆንው አሲዚ ከተማ ያደረጉት መንፈሳዊ ጉዞ ዋና ዓላማ በአሲዚ ተሰብስበው ምሕረትን በሚለምኑበት ዕለት ዓለምን በማስጨነቅ ላይ ካለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲልክ በጋራ ለመለመን መሆኑ ታውቋል። በጣሊያን ውስጥ በሪኤቲ ሀገረ ስብከት አስተባባሪነት በተዘጋጀው መንፈሳዊ የእግር ጉዞ ላይ የተሳተፉት ፍራንችስካዊ ካህን ክቡር አባ ስቴፋኖ ማርያ ሳሮ “ወደ አሲዚ የተደረገው መንፈሳዊ ጉዞ በእግዚአብሔር ፊት ራስን የሚያቀርቡበት አንዱ መንገድ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኃይለኛ የበጋ ወራት ሙቀት መካከል የእግር ጉዞን ማድረግ ነፍሳቸውን ከሚያስጨንቅ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ራስን ነጻ የሚያደርግ እና ከተፈጥሮ ጋር የተገናኙበት መንገድ መሆኑን ወጣቶቹ ገልጸዋል። ወደ አሲዚ የሚወስደውን መንገድ በመከተል ዳገቱን እና ቁልቁለቱን ወጥተው፣ ተራራን አቋርጠው፣ የእግዚአብሔርን የማያልቅ ምሕረት ለመለመን ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሄደበትን መንገድ መጓዛቸው መንፈሳዊ ልምድ የሚቀስሙበት ጉዞ መሆኑን ገልጸዋል። በጣሊያን ውስጥ በላሲዮ እና በአብሩዞ ክፍለ ሀገራት የሚገኙ ፍራንችስካዊያን ወንድሞች፣ ከሀገረ ስብከቶቹ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ጋር በመተባብር ያዘጋጁትን መንፈሳዊ የእግር ጉዞን የመሩት የሪኤቲ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ፖምፒሊ መሆናቸው ታውቋል።

በሪኤቲ ሀገረ ስብከት የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ፍራንችስካዊ ካኅን ክቡር አባ ስቴፋኖ ማርያ ሳሮ ለቫቲካ የዜና አገልጎሎት እንደገለጹት ቅዱስ ፍራንችስ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖር የወሰነበትን ጥሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበለው በአሲዚ መሆኑን አስታውሰው፣ ወደ አሲዚ የሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኘውን የወንድማማችነት ሕይወት ለማወቅ እና የእርሱን ምሕረት በሙላት ለመቀበል የሚያግዛቸው መሆኑን አስረድተዋል። ወጣቶችም ለዚህ መንፈሳዊ ጉዞ ዋጋን በመስጠት ላለፉት አርባ ዓመታት ሲጓዙ መቆየታቸውን አስታውሰው ወጣቶች ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔርን ከልብ ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት በማስፋት እና የእርሱን ፊት ለማየት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ወጣቶቹ ኑዛዜያቸውን ለጊዜው ከግምት ውስጥ ባያስገቡም ይልቁንም ከመንፈሳዊ ጉዞ በኋላ “ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ተበታትኖ ለሚገኝ ልባቸው ማረፊያን የሚሰጥ አምላክ መሆኑን ይረዱታል ብለዋል። ይህን የፍራንችስካዊያን መንፈሳዊ የእግር ጉዞን ለዓመታት ማካሄዳቸውን የገለጹት ፍራንችስካዊ ካኅን ክቡር አባ ስቴፋኖ ማርያ ሳሮ፣ የመንፈሳዊ ጉዞ አስተባባሪ እንደመሆናቸው ባለፉት ዓመታት ውስጥ አስደናቂ ተአምራትን ፣ ብዙ ወጣቶች ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር እጅ ላይ ያደረጉበትን አጋጣሚ ማየታቸውን ገልጸዋል።

የማያቋርጥ እይታ

አንድ ወጣት የእግዚአብሔርን ምሕረት ማወቅ እንዲችል ምን ማድረግ ይቻላል? ያሉት ካኅን ክቡር አባ ስቴፋኖ ማርያ ሳሮ፣ የራሳችንን መንገድ ትተን እግዚአብሔር ባዘጋጀልን መንገድ መጓዝ ስንጀምር ፍቅር ምን ያህል ቀላል እና ምን ያህል የተወሳሰበ እንደሆነ መረዳት እንችላለን ብለዋል። እይታን እና ልብን በትክክል መምራት አላስፈላጊ እና መሠረታዊ መሆኑን አስረድተው፣ ዓለም ከሚያቀርብልን ነገሮች መካከል መሠረታዊ ወደ ሆነው ዓይኖቻችንን እና አእምሮአችንን መመለስ መቻል ያስፈልጋል ብለዋል። ዓይኖቻችንን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ማለት የእርሱን ፍቅር በነጻ መቀበል ማለት እንደሆነ አስርድተው፣ ፍቅሩን መቀበል ማለት ይቅርታን ከልቡ ወደሚሰጥ እግዚአብሔር ዘንድ ያለመዘናጋት መቅረብ እንደሚያስፈልግ ክቡር አባ ስቴፋኖ ማርያ ሳሮ ተናግረዋል።

03 August 2021, 16:33