ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2013 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2013 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት 

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2013 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2013 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን ምእመናንና የቅድስት ማርያምን ፍልሰታ ለሚያከብሩ ሁሉ እንኳን ለ2013 ዓ/ም የፍልሰታ ማርያም ጾም በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የተቀደሰ የተባረከ ጾም እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም በሥጋዋና በነፍሷ ወደ ሰማይ የተወሰደችበት፤ እና ቤተክርስቲያን ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አክብሮት ከምታምንባቸው እና ከምታስተምራቸው የእምነት አንቀጾች (ዶግማዎች) አንዱ ነው። ካቶሊካውያን ምእመናን በየዓመቱ ከነሐሴ 1 እስከ 15 የእመቤታችንን ፍልሰታዋን ለማክበር ያስችላቸው ዘንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ በጾምና በሱባኤ በጸሎትም በመትጋት ያሳልፋሉ፡፡

ዘንድሮ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን እና እስካሁንም ድረስ እያሳለፈች ያለችባቸው እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች ለሁላችንም ግልጽ ነው። በሁሉም አቅጣጫ ብዙ ወገኖቻችን በዘርፈ ብዙ ግጭቶችና ጦርነቶችች እጅግ ክቡር ሕይወታቸው ተቀጥፏል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ይህ ሁኔታ አሁንም መቀጠሉ እጅግ ይሳዝነናል። በመሆኑም ይህንን የጾምና ምህለላ ዘመን እኛ ሁላችንም ሕዝበ እግዚአብሔር በሙሉ ልባችን በጸሎት ወደ አምላካችን ብንጮኽ ፊቱን ወደኛ ዘንባል በማድረግ ከተጋረጠብን ከዚህ ከተፈጥሯዊ እና ከሰው ሠራሽ ችግሮች ሁሉ እንደሚታደገን እንተመማመናለንና መለውን ምዕምናን እና በጎ ፈቃድ ያልሁችሁ ሁሉ ይህንን የፍልሰታ ጾም በተለየ ሁኔታና ትጋት እንድትጾሙ እና ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ስለ ሕዝቦቿ ደህንነትና ሰላም ተንበርክካችሁ እንድትጸልዩ ዘንድ እጥብቄ እለምናችኋለሁ፤ እሳስባችሁማለሁ። ጾማችሁና ሱባኤዎቻችሁ ደግሞ የሚጎሳቆሉ ንጹሐን ዜጎችን በማሰብ እና በሚቻለን ሁሉ መርዳትና መደገፍ እንደሚገባ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም ያዘኑትን፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን እንዲሁም ሕይወታቸውን በከፍተኛ ስጋት የሚመሩትን መርዳት አስፈለጊ እንደሆነ አስተማሪያችን ናት፡፡ እሷ የፍቅር ሥራ አብነት ናት ማለት ይቻላል፡፡ በእርሷ የፍቅር ሥራና ትሕትና የተሞላው ሕይወት ልንማረክ ይገባናል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የወንጌል ደስታ በተሰኘው መልእክታቸው ለድሆች እና በችግር ላይ ለሚገኙ ልዩ እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ እደሆነና ድሆችን ያላማከለ ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም "ኃይለኞችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ ሀብታሞችን ባዶ እጃቸውን ሰዶአቸዋል፤ ትሑታንን ከፍ አድርጎአቸዋል" (ሉቃስ 1፡52) በማለት ለእግዚአብሔር ምሥጋና ማቅረቧ በኑሮ ደረጃ ዝቅ ያሉትን እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለጉዳት የተዳረጉትን በማሰቧ ነው፡፡ ስለዚህ በኅብረተሰብ ሕይወት ለንጹሐን ዜጎች ደህንነት ማሰብ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ከሁሉ በላይ በዚህ በጾም ወቅት በልዩ ሁኔታ ሀገራችን ስላለችባቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ልንጸልይ እና ምሕለላ ልናደርግ ይገባናል።  ካቶሊካውያን ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር በሰላም፣ በመከባበር፣ በመቻቻል አብሮ በመኖር እና እርስ በእርስ በመዋደድ የጾምና የጸሎት መንፈስ ተላብሰው በዚህ የጾም ወቅት በጋራ እና በልዩ ሁኔታ እንዲጸልዩ አሳስባለሁ፡፡

የጾም ወራትን በጾምና በጸሎት በተጋድሎም በማሳለፍ ለበዓለ ፍልሰታዋ በሰላም ለመድረስ ያብቃን፡፡ አምላክ የተቀደስ የተባረከ ጾመ ፍልሰታ ለመላው ካቶሊካዊያን ምእምናን ያድርግልን እያልኩ "የሕያው ወንጌል እናት፤ ለእግዚአብሔር ታናናሾች የደስታ ምንጭ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእኛ ለልጆቿ እና ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ትለምንልን፡፡ አሜን"፡፡ (የወንጌል ደስታ288)

ቸሩ አምላካችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ኢትዮጵያን ይባርካት፡፡

 

 †ካርዲናል ብርሃነየሱስ

  ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

  የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዝደንት

  የኢትዮጵያ የዕርቀ ሰላም ኮሚሺን ሰብሳቢ

 

 

06 August 2021, 20:20