ወጣትነት እና ስኬቶቻቸው ወጣትነት እና ስኬቶቻቸው   (ANSA)

ወጣት እና ስኬት

በዚች ዓለም ዉስጥ ስኬታማ ሆኖ ለመኖር ራሱን ማጠናከርም ሆነ ማዳከም የሚፈጠረዉ በአእምሮ አጠቃቀም  ጉድለት ነዉ፡፡ ያለዉን አቅም በአግባቡ የማይጠቀም ሰዉ ደካማ ነዉ ሊባል ይችላል ፡፡ የሚሆነዉንና የሚችለዉን ፈልጎ የማግኘት ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ደካማ ሆኖ የተፈጠረ ሰዉ የለም ፡፡ ወጣቶችም ይህን በዉል መረዳት አለባቸዉ ፡፡ተስፋ መሰነቅ ለወጣቶች ትልቅ ጉልበት ይሆናል ፡፡ጉልበት የሚሆንለት ግን በዕዉቀት ስመራ ነዉ ፡፡አንድ ወጣት ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ራሱን መፈተሽ ይኖርበታል ፡፡ ምንድነዉ የምችለዉ ? ምንድነዉ የማልችለዉ ?ብሎ አቅሙን መለካት አለበት ፡፡

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርኔ

ወጣት ስኬታማ ለመሆን በመጀመርያ የራእይ ሰዉ መሆን አለበት ፡፡ ራእይ የለሽ ሰዉ ካለበትና ከደረሰበት አልፎ ለመሄድ አይፈልግም ፡፡ ይህ የሚሆነዉ ዓይኑ የተተከለዉ በገሃድ በሚታየዉ ብቻ ላይ በመሆኑና በዓይነ- ህልናዉ የሚያየዉ እይታ ስለሌለዉ ነዉ ፡፡ ባለ ራእይ  ሰዉ ባለበት ሳይወሰን ወደ አድስ ነገር ለመግባት ይገሰግሳል ፡፡ ራእይ የለሽ ሰዉ አይነ-ስጋዉ ብቻ የተከፈተና በፊቱ ያለዉን ብቻ እንድያይ  የሚገደድ ሰዉ ነዉ ፡፡ ባለ ራእይ ሰዉ ግን አይነ-ህሊናዉ የተከፈተ በመሆኑ በፊቱ ካሉት በእጁ ከጨበጣቸዉ እዉነታዎች ባሻገር በማየት ያልማል ፡፡

ለወጣቶች ስኬት መሰናክል የሚሆን ነገር ጊዜያዊዉ እና ዘላቂዉ ደስታ ሲጋጩ ነዉ ! አንዳንድ ጊዜ ዛሬ ተጎድተን እስከወዲያኛዉ የሚጠቅመንን መንገድ ከመምረጥ ይልቅ ለሰሞኑ ብቻ የሚጠቅመንንና የሚያስደስተንን ነገር ወደመምረጥ ስንጎተት ራሳችንን እናገኘዋለን ፡፡ አያችሁ ጊዜያዊና ዘላቂዉ ሁል ጊዜ በጦርነት ላይ ናቸዉ ፡፡ ያደላንለት ያሸንፋል ፡፡ ጊዜያዊ መስዋዕት አሁን አርክቶ ኃላ መዘዝ የሚያመጣዉን ለይቶ ማወቅና ያንን ሰዉቶ ወደፊት ዋጋ ባለዉ ነገር ላይ ማተኮር ስኬታማ ያረገናል ፡፡ ይህ ስናገሩት ቀላል፤ ወደ ተግባር ሲመጣ ግን ከባድ ሂደት ነዉ ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ዛሬ ተጠቅመን  ነገ ከምንከፍለዉ  ፤ ዛሬ ከፍለን ፍሬዉን ነገ ብንበላ ይሻለናል ፡፡

በምንም ነገር ከመበልጸግህ በፊት በአመለካከት የመበልጸግን ምስጢር ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ ይህንን ግንዛቤ ለማዳበር የሚረዱ እዉነታዎች እንደሚከተሉት ናቸዉ ፡-

1)     ማነኛዉም ነገር / ሁኔታ ጊዜያዊ መሆኑን ላይ ማትኮር ፡- ሃብት ፣ስልጣን  ፣ ኮኮብነት እና ተደናቅነት ሁሉ ጊዜያዊ ነዉ ፡፡እነዚህ ነገሮች ቀድሞ እንዳልነበሩ እና ከጊዜ በኃላ እንደመጡ ፤ እንደዛዉም ደግሞ ነገ ተመልሰዉ የሚሄዱበት ጊዜ ይመጣል ፡፡ዋናዉ ነገር ሁኔታዎች በእጃችን የመግባታቸዉን ዕድል ተጠቅመን  የሚናከናዉነዉ ነገር ነዉ ፡፡ የሁኔታዎችን ጊዜያዊነት ማወቅ የሚጠቅምህ በአንድ ጎኑ በተሳካልህ ነገር ተደላድለህ “ሃዉልት” ሆነህ እንዳትቀርና ሲሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ በጊዜያዊነት “ሽንፈትህ” ተስፋ ቆርጠህ እንዳትቀር ነዉ ፡፡

2)    ስኬት ገንዘብን ያመጣል እንጂ  ገንዘብ ስኬትን አያመጣም ፡፡ ይህ ማለት ገንዘብ ብቻዉን ስኬት አይደለም ፡፡እዉቀትም እንዲሁ ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ስኬት አንድ ቀን የሚደርስበት ክስተት ሳይሆን ሂደትና የህይወት ዘይቤ በመሆኑ ነዉ ፡፡ ስኬት ማለት በየዕለቱ  የሚንኖረዉ የአመለካከት ልቀት ፣ ዓላማን የማወቅ ብስለት ፣ ማንነትን  የማወቅ መደላደልና ሌለላዉ የመትረፍ እይታ ነዉ ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችን የተረዳ ሰዉ ገንዘብ የማግኘት መንገድን በቀላሉ ያገኛል ፡፡ ስኬት በእጃችን አስገብተን እንዳይጠፋ የምንጠብቀዉ ነገር ሳይሆን በየቀኑ የምንኖረዉ ኑሮ ነዉ ፡፡

3)   የአንዱ ነገር አለመሳካት የሁሉም ነገር አለመሳካት አይደለም ፡፡ ስኬት ዘርፈ ብዙ ነዉ፡፡በዚች ዓለም ላይ ያለዉ ዕድል ብዙ ነዉ ፡፡ ስለዚህ በአንዱ የወደቀ በሁሉም የወደቀ አይደለም ፤ በአንዱ ኃላ የቀረ በሁሉም ኃላ የቀረ አይደለም ፤ አንዱ መንገድ ያልገባዉ ሁሉም መንገድ ያልገባዉ አይደለም ፡፡የአንድን ወይም የተወሰኑ ሰዎችን ሁኔታ አይተን ስኬትን አንተርጉመዉ ፡፡

ወጣት ትኩስ ጉልበት አለዉ ፣ ይቻላል ብሎ ከወጣ ፣ ሁሉን ማድረግ ይችላል ፡፡ ዓለም ሰፊ ናት ፣ ገና ለጋ ዕድሜ ዉስጥ እያለህ የምን ተስፋ መቁረጥ አመጣዉ ፤ ብቻ አመለካከትህ ቀይረዉ !!!

ወጣት ለስኬት ከመጣር ይልቅ ተስፋ በመቁረት የወጣት ጡረተኛ መሆን የለበትም ፡፡ ሰዎች ረጅም እድሜ ከኖሩ ፣ ከተማሩ ፣ ከሰሩና የቻሉትን ያህል ከሮጡ በኃላ እድሜ ስገፋ ወደ ጡረተኝነት ይሸጋገራሉ ፡፡ ይህ የጡረተኝነት ዘመን ምንም እንኳን እንከን የሌለበት ሂደት ቢሆንም  የራሱ የሆነ ጣዕም ቢኖርዉም ፣ ምናልባት የጡረተኝነት ዘመን ትንሽ ጎዶሎ የሚያደርገዉ ጡረተኞቹ ከዚህ በፊት ራሳቸዉን ችለዉ ማድረግ የሚችሉትን ነገር እየቀነሱ የመሄዳቸዉ ጉዳይ ነዉ ፡፡ ይህ የሚሆነዉ ዋናዉ ምክንያት ቀድሞ የነበራቸዉ አቅም አሁን ስለማይኖራቸዉ ነዉ፡፡

እንደዛዉም  አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ወጣቶች ገና በለጋነት እድሜያቸዉ ጡረተኞች ይሆናሉ ፡፡ብዙ መስራት ስትችሉ ቁጭ ብላችዉ ጊዜያችሁን የምታሳልፉ ከሆነ ወጣት ጡረተኛ ናችሁ ፡፡ ስለነገ አላማችሁና ራእያችሁ ከሚታስቡትና ከሚታቅዱት  ይልቅ ቁጭ ብላችሁ ስለትናንትና  ታሪካችሁ ስታስቡና ስትጸጸቱ የምትኖሩ ከሆነ  ወጣት ጡረተኞች ናችሁ ፡፡

አንድን ነገር የማድረግ ፍላጎቱና ምኞት እያላችሁ አቅም  የማጣት ስሜት ከተጫጫናችሁ  ፣ ወጣት ጡረተኞች ናችሁ ፡፡ የመሻሻል አቅሙና ጤናነቱ እያላችሁ በየዕለቱ እየተሻሻላችሁና ራሳችሁን ወደ መቻል እያደጋችሁ ከመሄድ ይልቅ እየደከማችሁና የሰዉ ጥገኛ እየሆናችሁ ከሄዳችሁ ፣ ወጣት ጡረተኛ ናችሁ ፡፡ አንደ ሰዉ ትኩረቱን ፣ ጊዜዉን / አብሮነቱን ስለከለከላችሁ ብቻ መኖር እሰከማትችሉ ድረስ ተስፋ እንደሌላችሁ ከተሰማችሁ ወጣት ጡረተኞች ናችሁ ፡፡

ይህን የወጣትነት ዘመናችሁን በፍጹም እንደገና የማታገኙበት አመታቶች ሩቅ አይደሉምና ተነሱ ! ተንቀሳቀሱ ! አስቡ ! አቅዱ ! ስሩ ! ከማንም ሰዉ ዉጭ መኖር እንደሚትችሉ ራሳችሁን በማሳመን በፈጣርያችሁ ዕርዳታ ራሳችሁን  አሳድጉ እንጂ አትዳከሙ ፡፡ ካሳለፉችሁባችዉ ዓመታቶች ይልቅ ገና ያልኖራችሁባችዉ ዓመታቶች ይበዛሉና ወደፊት እያያችሁ በብርታት ተራመዱ ፡፡

የቤተክርስቲያናችን  ትልቅ ሰዉ ቅዱስ አዉጎስጢኖስ ስናገር “ያለ እኛ ፍቃድ የፈጠረን አምላክ ያለ እኛ ፍቃድ ምንም አያረግም” እንዳለዉ ፤ ወጣቶች ያማረ ህይወት ለመኖር ከፈለጉ ከመሠረቱ ማቃናት አለባቸዉ ፡፡ ህይወት ማለት  “ጀምሮ መጨረስ” ማለት ነዉ ፡፡ ከእናታችን ማህጸን ተወልደን የጀመረዉ ይህ ህይወት በትክክል ኖረነዉም  አልኖርነዉ አንድ ቀን ማብቃቱና  መፈጸሙ አይቀርም ፡፡ በዚህ ህይወት ዘመናችን የሚገኙ ማናቸዉም ነገሮች ለዚህ ሕግ ተገዢዎች ናቸዉ ፡፡ የግል ፣ የቤተሰብ ፣ የጓደኝነት ፣ የት/ት  ፣የፍቅር ፣ የትዳር ፣ ስራ ፣ ንግድ ፣ የተለያዩ የህይወት ዘርፎች ይጀመራሉ ! ይጨረሳሉ !

ይህ አንዴ የተጀምሮ በአደራ መልክ በእጃችን የተሰጠን ሕይወት  ወደፊት የምንመራዉና በተፈጠረለት የጥራት ንድፍ መሠረት የምንጨርሰዉ በየእለቱ በምናደርጋቸዉ ምርጫዎች ነዉ፡፡ እነዚህ ምርጫዎች ጉዞዎችን እንድንጀምር  ያነሳሱናል ፡፡ ቁም ነገሩ ያለዉ አንድን ነገር በመጀመራችን ላይ ብቻ ሳይሆን  በትጋት / በብቃት በመጨረሳችን ላይ ነዉ ፡፡ ስለዚህ ለጅማሬ መናሳሳትን ፣ ለቀጣይነት አቅምን ፣ በብቃት ለመጨረስ ደግሞ ስልትን ማዳበር የግድ ነዉ ፡፡ “የሚከፈልህ ለጀመርከዉ ነገር አይደለም ... ጀምረህ ለጨረስከዉ ነገር ብቻ ነዉ የሚከፈልህ”።

በሰዉ ህይወት ዉስጥ ሁለት የመማርያ መስኮች  አሉ ፤ አንደኛዉ መስክ ት/ት ቤት ያባላል ፤ ሌላኛዉ መስክ ደግሞ ሕይወት ይባላል ፡፡ ት/ት ቤት በመጀመርያ አስተምሮ ከዚያም ይፈትናል ፡፡ ህይወት ግን በመጀመርያ ፈትኖ ከዚያ ያስተምራል ፡፡ ት/ት ቤት ነገ ሊረሳ / ሊለወጥ የሚችል የአእምሮ ዕዉቀት ይሰጣል ፡፡ ህይወት ግን መቼዉንም  ቢሆን የማይረሳና የማይሻር የልምምድ ጥበብ ይሰጣል ፡፡ ስለዚህ ወጣት ሆይ በዛሬዉ ዕለት ብትቸገር / በህይወትህ የምትቀምሰዉ መከር ሁሉ ፤ የማይረሳ ነገር መሆኑንና በጥሩ አስተማር እየተማርክ መሆኑን አትዘንጋ እላለሁ ፡፡

23 July 2021, 14:36