በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመልአከ ገብርኤል ጸሎት ከተሰበሰቡት ምዕመናን መካከል በክፊል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመልአከ ገብርኤል ጸሎት ከተሰበሰቡት ምዕመናን መካከል በክፊል  (Vatican Media)

ሁለቱ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት በደስታ ይጠባበቃሉ ተባለ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሁለት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች፣ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገራቱ ሕዝቦች መካከል በከፍተኛ ናፍቆት እየተጠበቀ መሆኑ ተነግሯል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከመጭው መስከረም 2 - 5/2014 ዓ. ም ድረስ በሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የስሎቫኪያው ፕሬዚደንት ክብርት ሱዛና ካፑቶቫ በደስታ የተቀበሉት መሆኑን አስታውቀዋል። ክብርት ፕሬዚደንቷ በመልዕክታቸው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አገሪቱ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በምትገኝበት ባሁኑ ወቅት የዕርቅ እና የተስፋ መልዕክትን የሚያስተላልፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሰኔ 27/2013 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሚቀጥለው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በሁለት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች እንደሚሆን እነርሱም ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህን መልካም ዜና ባበሰሩበት ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት የተሰበሰቡት የስሎቫኪያ ምዕመናን ደስታቸውን በጭብጨባ ሲገልጹ ታይተዋል።    

የቫቲካን ዜና አገልግሎት የምሥራቅ አውሮፓ ዘጋቢ ስቴፋን ቦስ በዘገባው ቅዱስነታቸው በስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የሕዝቡን ደስታ እጥፍ ያደረገው መሆኑን ገልጾ፣ የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤም ዜናውን በታላቅ ደስታ የተቀበለው መሆኑን አስታውቋል።

የስሎቫኪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኢቫን ኮርኮክ በበኩላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ስሎቫኪያ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ታላቅ ክብር የተሰማችው መሆኑን ገልጸዋል። የቫቲካን ዜና አገልግሎት የምሥራቅ አውሮፓ ዘጋቢ ስቴፋን ቦስ በዘገባው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ወደ ሁለቱ አገራት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገራቱ ሕዝቦች ብርታትን እና መጽናናትን የሚሰጥ ነው በማለት ገልጾታል። 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን የሚመሩ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በመልካም እንዲጠናቀቅ ምዕመናን በጸሎት እንዲያግዟቸው ጠይቀው ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ስኬታማነት ዝግጅት እና የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙት የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።

06 July 2021, 15:24