ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የ “ፖሊኮሮ” ማኅበር ወጣቶች ያቀረቡትን ንግግር ሲያዳምጡ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የ “ፖሊኮሮ” ማኅበር ወጣቶች ያቀረቡትን ንግግር ሲያዳምጡ 

ወጣቶች በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምክር በመታገዝ ወደፊት እንዲጓዙ ጥሪ ቀረበ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጣሊያን ወጣት ካቶሊካዊ ማኅበራት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ለወጣት ማኅበራት ተወካዮች ባቀረቡት መልዕክት ወጣቶች በማኅበረሰባቸው ውስጥ የተስፋ ፍሬ እንዲሆኑ አሳስበዋል። በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የማኅበራዊ ችግሮች አስወጋጅ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ ወጣቶች በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አነሳሽነት በመታገዝ ክርስቲያናዊ እና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ወደ ፊት እንዲገፉ ጥሪ አስተላልፈዋል። ክቡር አባ ብሩኖ አክለውም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ በወጣቱ መካከል የሥራ ፈጠራ ችሎታ የበለጠ እንዲያድግ ማድረጉን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሥራ፣ ተስፋ፣ ሰብዓዊ ክብር እና ጥረት በሚሏቸው ሃሳቦቸው ላይ በመመርኮዝ በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር በሚገኝ “ፖሊኮሮ” በሚባል ማኅበር ውስጥ የታቀፉ አንድ መቶ ወጣቶችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክታቸውን አስተላልፈውላቸዋል። “ፖሊኮሮ” የተባለ ማኅበር የወጣቶችን ሕይወት ለማሻሻል በደቡብ ጣሊያን፣ ፓሌርሞ ከተማ ውስጥ ከ25 ዓመታት በፊት መቋቋሙ ይታወሳል። ማኅበሩ እ. አ. አ በ1995 ዓ. ም ከተመሠረተ በኋላ በሰሜን ጣሊያን የቶሪኖ ከተማ ተወላጅ የሆኑት ክቡር አባ ማርዮ ኦፔራቲ የደቡብ ጣሊያን ወጣቶች ሕይወት በማሻሻል ለቤተክርስቲያናቸው ድጋፍ እንዲሆኑ ማድረጋቸው ታውቋል። ማኅበሩ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በደቡብ ጣሊያን በሚገኙ 130 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለወጣቶች የብድር አገልግሎትን በማመቻቸት እና በማደራጀት በንግድ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ማድረጉ ታውቋል።

ባህል እና ማህበራዊ ኑሮ የሕይወት መመሪያዎች

በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የማኅበራዊ ችግሮች አስወጋጅ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ ወጣቶች ለቅዱስነታቸው መልዕክት የሰጡትን ምላሽ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሥራ፣ ተስፋ፣ ሰብዓዊ ክብር እና ጥረት የሚሉ ርዕሠ ጉዳዮችን በመመልከት መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስታውሰው፣ በተለይ በዚህ አስቸጋሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በርካታ ወጣቶች በማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ መገኘታቸውንም ገልጸዋል። በመሆኑም ወጣቶች ያጋጠማቸውን ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ለማሸነፍ በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክቶች በመታገዝ ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት ያደረባቸው መሆኑን አስረድተዋል። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት ለወጣቶች ተስፋን የሚሰጥ እና በልባቸው ውስጥ በራስ የመተማመን ስሜት የፈጠረ መሆኑን ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ አክለው አስታውቀዋል።

ችግሮችን ለመቋቋም የሚደረግ ጥረት የማኅበራቸው ዋነኛ መመሪያ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ ወጣቶች በአካባቢያቸው የሚከሰቱት የተወሳሰቡ ችግሮችን ቶሎ በመገንዘብ፣ በማኅበራዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ ሕይወትም የሚታዩ ችግሮችን በማጤን፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እንደተናገሩት፣ አንድ የወንጌል መልዕክተኛ ሊያደርግ የሚገባውን ሥራ ተግባራዊ በማድረግ ምላሽ የሚሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።

“በ25 ዓመታት ውስጥ በማኅበራቸው ውስጥ የተወለዱ ሁለት ጽንሰ-ሃሳቦች አገራቸው በወጣቶች ላይ ተስፋን እንዲትጥል አድርጓል” ያሉት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ የመጀመሪያው፣ የሥራ ባሕልን ማሳደግ የሚል መሆኑን አስታውሰው፣ ይህም እያንዳንዱ ወጣት ምን መሥራት እንደሚችል ራሱን እንዲጠይቅ አድርጓል ብለዋል። ሁለተኛው ሃሳብ፣ ማኅበሩ ምን ዓይነት ሥራን ለወጣቶች ቢያስተዋውቅ ሕይወታቸውን ሊያሻሽል ይችላል? የሚል መሆኑን ገልጸዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአገራቸው ሲዛመት ወጣቶች ሥራቸውን እንዲያቆሙ በታዘዝ ተገባራዊ ቢያደርጉም አጋጣሚዎችን በመጠቀም፣ ሁሉ የተመቻቸበት ጊዜን ሳይጠብቁ፣ በአውታረ መረብ አማካይነት ትምህርታቸውን በመከታተል ተስፋን የሚሰጥ ተግባር መፈጸማቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ አስረድተዋል።

07 June 2021, 14:58