የሚያንማር ሰላማዊ ሰልፈኞች የሚያንማር ሰላማዊ ሰልፈኞች  

የሚያንማር ሕዝብ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምስጋናውን አቀረበ

በሚያንማር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች የእምነት ተቋማት በአገሩ ሰላም እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት ምስጋናቸውን እና አድናቆታቸውን ማቅረባችውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ቲን ዊን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ በየካቲት ወር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባት ሚያንማር በከፍተኛ አመጽ እና ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ መቆየቷ ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሚያንማር ሕዝብ ጎን በመሆን በሚችሉን መንገድ ሁሉ ሲረዷቸው እና ሲያጽናኗቸው መቆየታቸውን የተገነዘቡት አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች የእምነት ተቋማት ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምስጋና ማቅረባቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ቲን ዊን ገልጸው፣ በሚያንማር ሕዝብ ላይ የደረሰውን ችግር እና መከራ በማስመልከት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት በሚያስተላልፉበት ወቅት ሁሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ብቻ ሳይሆን የሌሎች እምነቶች ተከታዮችም መጽናናትን እና ብርታትን የሚያገኝ መሆኑን ሊቀ ፓጳስ ብጹዕ አቡነ ማርኮ አስረድተዋል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለመላው የሚያንማር ሕዝብ ብርታትን መመኘት አስፈላጊ መሆኑን የማንዳላይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ አስታውቀዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሚያንማር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በሐዘን ውስጥ ሆነው ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ በአገሪቱ ውስጥ በተቀሰቀሰው አመጽ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈላቅለው በረሃብ መሰቃየታቸውን፣ በዚህ ምክንያት ብዙዎች እየሞቱ መሆኑን አሳስበው፣ ለሕዝቡ ምግብ እና ሌሎች ዕርዳታዎች የሚደርስበት መስመር እንዲመቻች በማለት አሳስበው ከወራት ወዲህ በከፍተኛ መከራ ውስጥ የሚገኘውን የሚያንማር ሕዝብ በጸሎታቸው በማስታወስ ከጎኑ እንደሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል። እ. አ. አ በኅዳር 2015 ዓ. ም በሚያንማር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያካሄዱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአገሪቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደበት ጊዜ አስንቶ አገሪቱን ሲረዱ መቆየታቸው ሲታወስ ወታደራዊ መሪዎችም ለውይይት ቀርበው በአገሪቱ ሰላምን ለማረጋግጥ እንዲተጉ ማሳሰባቸው ይታወሳል። 

መፈናቀል፣ መከራ እና ረሃብ

በሚያንማር የማንዳላይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ፣ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በሙሉ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሰላም ጥሪ መልዕክት እንዲቀበሉ ጠይቀዋል። በሀገረ ስብከታቸው እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በአመጹ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስረድተው፣ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ሕሙማን እና አቅመ ደካማ አረጋዊያን በአመጹ ምክንያት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም የአገሪቱ ወታደራዊ ሠራዊት የዕርዳታ እህል ማቃጠሉ በንጹሐን ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭካኔ ተግባር መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ አስረድተዋል።    

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓርብ ሰኔ 11/2013 ዓ. ም ባሳለፈው ውሳኔ ለሚያንማር የሚቀርብ የጦር መሣሪያ ሽያጭ እንዲቆም፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ እና በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚወሰድ የኃይል እርምጃ እንዲቆም መጠየቁ ይታወሳል። ይህ ውሳኔ በሚያንማር ውስጥ ሰላም እንዲወርድ የሚያግዝ የመጀመሪያ ውሳኔ እንደሆነ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገልጸው፣ በውሳኔው የሚያንማር ሕዝብ የተደሰተ መሆኑንም ገልጸዋል። በሚያንማር የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥ የመሩት ጀኔራል ሚን አውንግ ያለፈው እሑድ ወደ ሩሲያ ያመሩ መሆናቸው ሲነገር የጉዞአቸው ዓላማም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የታለመ ነው ተብሏል።

እራስን መከላከል

በሚያንማር ውስጥ የአገሪቱ ጸጥታ አስከባሪዎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገልጸው፣ ወጣቶች ሕዝቡን ከጥቃት ከመከላከል በስተቀር ሌላ ዓላማ የለውም ብለዋል። በሚያንማር የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም የሰላም መልዕክቶችን በማስተላለፍ እና ደም መፋሰስ እንዲቆም በመጸለይ ላይ መሆኗን አስታውቀዋል። በአገሪቱ ውስጥ ለሰላማዊ ውይይት ፈቃደኛነቱን የገለጸ አካል አለመኖሩን ያስታወቁት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ፣ እግዚአብሔር የሰዎችን ልብ እንዲለውጥ ከመጸለይ በቀር ሌላ ምርጫ የሌላቸው መሆኑን ፊደስ ለተሰኘ የቤተክርስቲያን ዜና ምንጭ ተናግረዋል።   

በሚያንማር በተካሄደው የመንግሥት ግልበጣ በአገሪቱ ሰላም ጠፍቶ መቆየቱ ይታወሳል። በአገሪቱ በተቀሰቀሰው አመጽ ምክንያት ከ800 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል። ለበርካታ ሳምንታት በሚያንማር ትላልቅ ከተሞች መጠነ ሰፊ ሰላማዊ ሰልፎች ሲደረጉ መቆየቱም ይታወሳል። ከሰላማዊ ሰልፈኞች ውስጥ ወጣቶችን ጨምሮ 4,000 የሚጠጉ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ ለሚኖሩ የእስያ አህጉር ተወላጆች ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ ከጥላቻ እና ልዩነት ይልቅ ፍቅርን እና ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በመልካም ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች በመታገዝ ለኢየሱስ ክርስቶስ እውነት ታማኞች መሆን እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

24 June 2021, 16:28