የሜጁጎሪ እመቤታችን ቤተመቅደስ የሜጁጎሪ እመቤታችን ቤተመቅደስ  

በሜጁጎሪ የሚገኝ የእመቤታችን ቤተመቅደስ ከ40 ዓመታት በኋላ

ከባልካን አገሮች መካከል አንዱ በሚባለው ቦስኒያ ሄርዞጊቪና ውስጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለወጣቶች የተገለጸችበት ሜጁጎሪ በዓመት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ መንፈሳዊ ነጋዲያን የሚሄዱበት ሥፍራ መሆኑ ሲነገር የዚህ መንፈሳዊ ሥፍራ ታሪክ የሚጀምረው ከሰኔ 17/1973 ዓ. ም. ጀምሮ ነው። የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዓለም ዙሪያ እንዲወገድ በማለት በዚህ ሥፍራ በሚያዝያ ወር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎት ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዛሬ ቦስኒያ ሄርዞጊቪና በሚባል አገር ቢጃኮቪች በተባለች መንደር የሚኖሩ ጥቂት ወጣቶች የሴት መልክ ያላት፣ በብርሃን የተሞላች ሰው ፊት ስለተገለጠላቸው ይህ መልክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት እንደሆነ አመኑ። ይህ የሆነው ሰኔ 17/1973 ዓ. ም ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለአርባ ዓመታ በኮሚኒስት ሥርዓት ስትተዳር በነበረች ድሃ አገር የሜጂጎሪ እመቤታችን ታሪክ ሲወራ ቆይቷል። በሜጁጎሪ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተገለጠችላቸው ሰባቱ ወጣቶች ቅድስት ድንግል ማርያም ራሷን “የሰላም ንግሥት” በማለት መናገሯን ይመሰክራሉ። ይህ የእመቤታችን መልዕክት በዓለም ውስጥ እርቅን እና የሕይወት ለውጥን ለማምጣ እጅግ ወሳኝ መልዕክት ነበር።

ሜጁጎሪ የተባለች የገጠር መንደር ከረጅም ዓመታት ወዲህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለጸሎት የሚሄዱባት አካባቢ ሆናለች። የሜጁጎሪ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ብዙ ሰዎች ምስጢረ ንስሐን የሚገቡት እና የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎትን የሚካፈሉበት መንፈሳዊ ቦታ ነው። ታዋቂ ስፖርተኞች እና የቴያትር ባለሞያዎች የሕይወት ለውጥ ያገኙበት ሥፍራ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ ሜጁጎሪ ብዙ ሰዎች የእምነት ብርታት ያገኙበት፣ ወደ ቅዱሳት ምስጢራት የቀረቡበት፣ ብዙዎች በእምነታቸው በርትተው መልካም ፍሬን ያሳዩበት ስፍራ ነው።

መርማሪ ኮሚሽን መሰየም
በሜጁጎሪ እመቤታችን ቅድስት ማርያም በእርግጥም ለወጣቶች መገለጧን የሚያረጋግጥ መርማሪ ቡድን በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ በሚመለከት ማኅበር ውስጥ ካርዲናሎችን፣ ብጹዓን ጳጳሳትን፣ የሰነ-መለኮት ሊቃውንትን እና ጠበብትን የቀፈ አሥራ ሰባት አባላት የሚገኝበት ዓለም አቀፍ መርማሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረጋቸው ይታወሳል። ኮሚሽኑ ያካሄደውን የአራት ዓመት የምርምር ውጤት ይፋ ከማድረግ አስቀድሞ ወድ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዘንድ ማቅረቡ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በሚያዝያ ወር 2017 ዓ. ም በፖርቱጋል የሚገኝ የፋጢማ እመቤታችን መቅደስ ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ጉብኝተው ሲመለሱ ባደረጉት ንግግር

ሁሉም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግልጸቶች የግል ምስክርነቶች እንጂ የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ አካል አለመሆናቸውን አስረድተው ኮሚሽኑ ሦስት ጉዳዮችን እንዲያጣራ ሥራ የተሰጠው መሆኑን ገልጸው የመጀመሪያው በሜጁጎሪ ታይታለች የተባለውን የእመቤታችን የመጀመሪያ ግልጸት የመሠከሩት በልጅነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች በመሆናቸው ምክንያት ተጨማሪ የምርምር ጊዜ እንዲሰጥ መወሰኑን አስታውሰዋል። ቀጥሎ የታየው ሁለተኛው ግልጸት ጥርጣሬ የለበት ሲሆን ሦስተኛው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግለጸት ወደ ሜጁጎሪ የሚሄዱ በቁጥር በርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት ሕይወታቸውን የቀየሩ በመሆኑ እውነተኛነቱ የተረጋገጠ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።

ለመንፈሳዊ ነጋዲያን የሚደረግ እንክብካቤ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነጋዲያን የሚሄዱባትን የሜጁጎሪ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስን በየጊዜው እንዲጎበኙ በማለት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄንሪክ ሆሰርን በ2010 ዓ. ም መሰየማቸው ይታወሳል። ስያሜው በቅድስት መንበር የተወሰነ የልዩ ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል መሆኑ ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄንሪክ ሆሰርን በሜጁጎሪ ቁምስና ያላቸውን ሃላፊነት አስመልክቶ የቫቲካን መግለጫ ክፍል እንደገለጸው፣ የቁምስናውን ምዕመናን እና ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያንን መንፈሳዊ እንክብካቤን መስጠት እና ቀጣይነት ያለውን ክትትል ማድረግ እንደሆነ አስታውቋል። ከ2011 ዓ. ም ጀምሮ ከተለያዩ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች መንፈሳዊ ጉዞን ማስተባበር እንዲቻል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ፍቃድ መስጠታቸው ታውቋል።

የጸሎት እና የትውውቅ መድረክን ማመቻቸት
ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ በሜጁጎሪ የወጣቶች መንፈሳዊ ስብሰባ ሲካሄድ መቆየቱን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ሥፍራዉ የሚጓዙት ወጣቶች በሚያቀርቡት ጸሎት አማክይነት አዲስ የሕይወት ልምድን የሚቀስሙበት በመሆኑን እንዲጎበኙት በማለት ግብዣቸውን አቅርበዋል። ወጣቶች ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ የሕይወትን እውነተኛ ትርጉም ለይተው ያውቃሉ ብለዋል። የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዓለም ዙሪያ እንዲወገድ በማለት ያለፈው ሚያዚያ ወር በቦስኒያ ሄርዞጎቪና በሚገኙ ሰላሳ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስናዎች ጸሎት ሲደረግ የቆየ ሲሆን፣ በግንቦት 7/2013 ዓ. ም. በሚጁጎሪ በሚገኝ ቅዱስ ያዕቆብ ቅምስና ውስጥ ስደተኞችን በማታወስ ልዩ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዶ ማለፉ ይታወሳል።
 

28 June 2021, 20:49