የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት አርማ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት አርማ  

በኢትዮጵያ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምላሽ

መግቢያ

በኢትዮጵያ ሀገራችን በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በየአካባቢው የሰው ሕይወት መቀጠፍ፣ ንብረት መውደም እና የዜጎች መፈናቀል ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ እና የዕለት ተዕለት ዜና እየሆነ መጥቷል። በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ሰዎች በጎርፍ አደጋ፣ በአንበጣ መንጋ እንዲሁም በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ  ምክንያት የሰዎች ሕይወት አልፏል፣ ከፍተኛ የጤና እና ማሕበራዊ ቀውስ ተከስቷል በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ኢትዮጵያውያን ለወትሮው ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ የኑሮ ደረጃ ልዩነቶችን መሰረት ሳያደርጉ በጋራ በመረባረብ የተጎዱትን በማቋቋም በተፈጥሮ አደጋዎች የተከሰቱባቸውን ጉዳቶች በመቀልበስ ወደ መደበኛ የኑሮ ሁኔታ ለመመለስ ጥረት የሚያደርጉ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ታሪኮችን ለማመሳከር መሞከሩ በቂ ነው።

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በተለይ በጎርፍ እና በአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ የተፈጥሮ አደጋዎቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰበካዊ ጽ/ቤቶቿን በማስተባበር እና አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ለተጎጂ ወገኖች አብሮነትዋን አሳይታለች። ከእነዚህም ጥቂቶቹን እንኳን ለመጥቀስ ያህል በባህር ዳር-ደሴ ሀገረስብከት በኩል በደቡብ ወሎ ዞን እና በባቲ ዙሪያ በትሁለ ደሪ፣ በከሚሴ ለሚገኙ በአንበጣ መንጋ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች በተመሳሳይም በደቡብ ጎንደር ዞን፣ በሊቦ ከምከም ወረዳ ዙሪያ በጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የእህል ዘር፣ የዕለት ደራሽ ምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ አድርጋለች።

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከል እና በመግታት ሂደት በጳጳሳት ጉባኤ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በቁጥር CBCE-022-20 በአምልኮ እና በሥራ ቦታዎች የሚተገበሩ የጥንቃቄ መመሪያዎችን አውጥታለች። በመስከረም  2013 ዓ.ም. ይህንኑ መመሪያ አሻሽላ በማውጣት ተግባራዊነቱን በጥብቅ በመከታተል ላይ ትገኛለች። መመሪያዎችን ከማውጣት እና በተግባር ከማዋል በተጨማሪ 40,000,000.00 (አርባ ሚሊዮን ብር) የሚገመት መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ የንጽህና መጠበቂያ፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ፣ የህክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒቶችን በመላው ሀገሪቱ አሰራጭታለች። የጤና ተቋማቶቿም የመከላከል ሥራውን በሰፊው እያከናወኑ ይገኛሉ።

በአሁኑ ጊዜ ግን በሀገራችን በተፈጥሮ ከሚደርሱብን ጉዳቶች እጅግ በከፋ መልኩ በየጊዜው እና በየአካባቢው በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየወደመ እና ዜጎች ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ይገኛሉ። በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች በየጊዜው በሚከሰቱ የእርስ በእርስ ግጭቶች እና ጦርነት ምክንያት የንጹሃን ሰዎች ሕይወት ያለአግባብ ተቀጥፏል፣ ህጻናት እና ሴቶች ተደፍረዋል፣ አካል ጎድሏል፣ ቤተሰብ ተበትኗል፣ አረጋውያን ያለጧሪ፣ ህጻናት ያለአሳዳጊ ቀርተዋል፤ የሰው ልጆች ክብር ተገስሷል፣ ፆታዊ ጥቃት ተፈጽሟል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ መብት ተጥሷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ንብረታቸው ተዘርፎ፣ ቤታቸው ተቃጥሎ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። የማምለኪያ ቦታዎች እና በርካታ መዋዕለ ነዋይ ፈሶባቸው ሕብረተሰቡን በነጻ እንዲያገለግሉ የተቋቋሙ እና ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተቃጽዖ ሲያበረክቱ የቆዩ የሃይማኖት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የልማት ተቋማት ተዘርፈዋል ተቃጥለዋል።

እነዚህ የወንጌልን እንዲሁም የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን እምነት እና አስተምህሮ በግልጽ የሚጻረሩ ተግባራት ናቸው። በመሆኑም ቤተክርስቲያን የተለያዩ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በማክረር ወደግጭት ከመግባታቸው አስቀድሞም ሆነ የግጭት እና የጦርነት ሁኔታዎች ከተከሰቱ በኋላ በሽምግልና እና በዕርቅ ሂደቶች በይፋ በመሳተፍ፣ ግልጽ ጳጳሳዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ፣ በመዋቅሮቿ እና በአገልግሎት ተቋማቶቿ የሰላም እና ዕርቅ ስልጠናዎችን እና አስተምህሮዎችን በማስተላለፍ፣ በቁምስናዎቿና በደብሮቿ የጸሎት እና የምህላ አዋጅ እና መርሃግብራትን በመተግበር፣ በመገናኛ ብዙሃን የሰላም እና ዕርቅ አስተምህሮዎችን በተደጋጋሚ እና በአትኩሮት በማስተላለፍ ለምእመናኖቿ እና በጎ ፈቃድ ላላቸውን በሙሉ የሰላምን አስፈላጊነት ለማስገንዘብ እንዲሁም ሁሉም ወገን የሰላም መሳሪያ እንዲሆን የማነጽ ተግባራትን አከናውናለች።

ሰላም እና ዕርቅን ለማስፈን በተግባር ከምትሳተፍባቸው እንዲሁም ከሕንጸት እና ግንዛቤ ከማስጨበጥ መርሃግቦቿ በተጓዳኝ በጦርነት እና በግጭቶች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በጳጳሳት እና በቤተክርስቲያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሚመሩ የልዑካን ቡድኖችን በማቋቋም፣ ተጎጂዎች የሚገኙበት ቦታ ድረስ በአካል በመጓዝ፣ ሁኔታዎችን በመታዘብ እና ለዜጎች አብሮነትን በመግለጽ የዕለት ደራሽ እና መልሶ የማቋቋም ተግባራትን እና የማጽናናት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በኢትዮጵያ ያከናወነቻቸው ተግባራት

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ አሳሳቢነት ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሑድ ጥቅምት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በብስራተ ገብርኤል ጸሎት ማሳረጊያ ላይ በኢትዮጵያ ያለው የሰላም ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው እና መንግሥት እና በግጭት የተካረሩ ወገኖች በሙሉ ሰላማዊ አቅጣጫዎችን ብቻ በመከተል ልዩነቶቻቸውን በውውይት እንዲፈቱ ይፋዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።1 እንዲሁም ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በቫቲካን የፕሬስ ጽ/ቤት በኩል በድጋሚ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በአንክሮ እየተከታተሉ መሆኑን በመግለጽ በፌዴራል እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የተፈጠረው ግጭት በአፋጣኝ እንዲቆም እና ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ ምእመናንም በመላው ሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በጸሎት እንዲተጉ እና የበኩላቸውን አስተዋጽዖዎች ሁሉ እንዲያበረክቱ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የተከናወነው 49ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ስብሰባውን ያደረገው ሀገራችንን በስጋት ውስጥ በጣሏት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የጸጥታ መደፍረስ ውጥረት መካከል መሆኑን ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የጉባኤው ፕረዝዳንት ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. “ባልንጀራዬ ማን ነው?”2 በሚል የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸው ነበር። በዚሁ መልዕክታቸው ላይም በሀገራችን ላይ ያንዣበቡ አደጋዎች የሰው ልጆች ሕይወት በከንቱ መጥፋት፣ የንብረት መውደም፣ የዜጎች ከቀያቸው መፈናቀል፣ የሰደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ፣ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ህጻናት እና ሴቶች ጉዳይ መላውን ካቶሊካውያን ጳጳሳት በጥልቅ ያሳሰቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል። መላውን የጉባኤ አባላት ጳጳሳትን በመወከልም እነዚህ ፈተናዎች በቀላሉ ልናያቸው የሚገቡ አለመሆናቸውን በማስገንዘብ ካቶሊካውያን ሌት ተቀን በጸሎት እንዲተጉ በተለይ ደግሞ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በነሐሴ ወር የሚዘወተረውን የፍልሰታ ጾም ካቶሊካውያን በሙሉ በልዩ ጸሎት እና ምህላ እንዲያሳልፉ ጥሪ አስተላልፈዋል። በሀገራችን ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉም በማስተዋል፣ በጥበብ፣ ቅንነት በተሞላበት መንገድ እና የሕዝብን ጥቅም፣ አንድነት እና አብሮነት ባማከለ መንገድ ውይይት እንዲያደርጉ በእግዚአብሔር ስም ተማጽኗቸውን አቅርበዋል።

ካቶሊካውያን ምእመናንም ማናቸውንም የሰውን ልጅ መለኮታዊ ክብር የሚነኩ ሃይማኖታዊም ሆኑ የብሔር አጀንዳዎችን ከማራመድ እንዲቆጠቡን የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ እና እኩል ክብር ያለው በመሆኑ እንደራሳችን አድርገን አንድንወደው ከአምላክ የተሰጠን መለኮታዊ ትዕዛዝ መሆኑን አስታውሰዋል። ካቶሊካውያንም የሰላም መሳሪያ በመሆን በአካባቢያቸው ለሚኖሩ ሁሉ አብነት የሚሆን የፍቅር ተግባር የመፈጸም ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከያዝነው ዓመት መባቻ ከመስከረም ወር አንስቶ በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት አማካኝነት ለበዓላት በሚተላለፉ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች ለሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም ለንጹሃን ዜጎች የመኖር ዋስትና መከበር አጽንዖት በመስጠት እንዲዘጋጁ በማድረግ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ካቶሊካዊ ሰበካዎች ጳጳሳት፣ ለየሀገረስብከቱ ሐዋርያዊ እና የማሕበራዊ ልማት ክፍሎች በማሰራጨት እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱ ብቸኛ ሐዋርያዊ ልሳን በሆነው በፍቅርና ሰላም ጋዜጣ በማሳተም፣ ለሚመለከታቸው ሁሉ፣ ለመንግሥት እና ለግል መገናኛ ብዙሃን በመላክ ለሕዝብ እንዲደርስ አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል፦

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በመስከረም 2013 ዓ.ም. ባስተላለፉት የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት3 ላይ የሀገራችንን የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት ተምሳሌትነት እያጠፋን ሕዝቦቻችን በኃዘን፣ በስጋት፣ በለቅሶ እና በፍርሃት የሚኖሩባት ምድር እያደረግናት መሆኑን በመግለጽ ትውልዳችን በአንድነት እና በሕብረት በመቆም ለመጪው ትውልድ መልካም ነገር መሥራት እና ማቆየት አንደሚያስፈልገው አሳስበዋል። መንግሥትም የዜጎችን ደህንነት፣ ሰላም እና በሕይወት የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባው ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በቁጥር CBCE-039-20 የኢትዮጵያ ጳጳሳት ጉባኤ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎችን በማስመልከት ባስተላለፈው “የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና”4 (ማቴ.5:9) በተሰኘ መልዕክት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተደጋጋሚ በንጹሐን ወገኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት በጽኑ አውግዛለች። የሰውን ልጅ ክብር የሚያጎድፍ፣ ለስቃይ፣ ለእንግልት እንዲሁም ለሞት የሚዳርግ ማናቸውም ዓይነት ተግባራት በማንኛውም አካል ሊፈጸም እንደማይገባ በግልጽ አሳስባለች።  

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የካቶሊክ ቢተክርስቲያን አጋር ድርጅቶች በሙሉ በትግራይ እና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለውን ጦርነት እና ግጭቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ ሕዝቦች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ በማስተዋል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ስም እርዳታ እንዲሰባሰብ ጥሪ አቅርበው የዕርዳታ ጥያቄ ለሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ አጋር ድርጅቶች ተልኳል። በምላሹም 80,000,000.00 (ሰማንያ ሚሊዮን ብር) የሚጠጋ በመሰብሰብ ለተጎጂዎች እንዲደርስ አድርጋለች። ይህ አሃዝ የካቶሊክ እርዳታ ድርጅቶች በራሳቸው በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮምያ ክልልሎች የሚያከናውኗቸውን ሰፊ አገልግሎቶች ሳይጨምር ነው።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                           በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የዘለቀውን አለመግባባት ለማርገብ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ የተደረገው ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ በመካከላቸው እየተባባሰ የመጣው አለመግባባት ዛሬ ወደ ግጭት ደረጃ መድረሱ እጅጉን ያሳዘናት መሆኑን በመግለጽ ሁለቱም ወገኖች የገቡበትን የተካረረ ሁኔታ በአስቸኳይ በማቆም ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ፣ በመከባበር፣ በመደማመጥ እና በመተማመን ላይ በተመሰረተ ውይይት ብቻ እንዲፈቱ ተማጥኖዋን አቅርባለች።

መላው ኢትዮጵያዊም ይህንን ሁኔታ በአንክሮ በመመልከት ጉዳዩ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አለመሆኑን በመገንዘብ ዕርቅ እንዲሰፍን፣ ሕዝባዊ አንድነት እንዲጠናከር ሰላም እና ጸጥታም እንዲረጋገጥ በባለቤትነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፋለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘም መንግሥት የሚወስዳቸው ማናቸውም ዓይነት እርምጃዎች የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የማይጥሉ እና ሀገርንም ከማትወጣበት አዘቅት ውስጥ የማይከቱ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት በጥብቅ አሳስባለች።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገራት ተቀምጠው የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን የሚያቀርቡ በሙሉ የሙያ ሥነምግባርን የተከተሉ፣ ግጭትን የማያባብሱ እና ሕዝብን በሕዝብ ላይ የማያነሳሱ ዘገባዎችን በጥንቃቄ እንዲያስተላልፉ ዐደራ ጭምር አሳስባለች።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ሐዋርያዊ ኮሚሽን ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ባከናወነበት ወቅት የአዲግራት ሀገረስብከት ተወካዮች በጉባኤው ላይ ለመገኘት ባለማቻላቸው ምክንያት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ ለብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ፣ በሰበካው ሐዋርያዊ አገልግሎት ለሚያበረክቱ እና ለምእመናን በሙሉ የአብሮነት መግለጫ መልዕክት ልከዋል።

ከታህሣሥ 8 እስከ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደው 50ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ መደበኛ ጉባኤ በአዲግራት፣ በባህር ዳር-ደሴ፣ በነቀምት እና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ የሰላም እጦት እና የተፈጠረውን ጉዳት መጠን ቅድሚያ ሰጥተው ተወያይተዋል።5 ቤተክርስቲያን መስጠት ያለባትን ፈጣን ምላሽ በተመለከተም ተግባራዊ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። ለዓለም አቀፍ ምግባረ ሰናይ ተቋማትም የአስቸኳይ ድጋፍ ጥሪ አቅርበዋል። ለብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ፣ በአዲግራት ሀገረስብከት ለሚገኙ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን በሙሉ የአብሮነት መግለጫ መልእክት ልከዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2013 የጌታችን እና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን አስመልክተው ለመላው ምእመናን ባስተላለፉት መልዕክት6 በሀገራችን ኢትዮጵያ በየጊዜው የምናየው እና የምንሰማው የሰው ልጆች ለቅሶ፣ ሰቆቃ ፣ መፈናቀል እንዲሁም ክቡር የሆነው እግዚአብሔር በአርዓያው እና በአምሳሉ የፈጠራቸው ሰዎች ሕይወት በከንቱ መቀጠፍ እንዲያበቃ ሁላችንም የሰላም ሰዎች እንድንሆን እና በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት መንፈስ እንደ አንድ ቤተሰብ አንድ ሆነን ልንቆም ይገባል በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በጥር እና በየካቲት ወራት 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ልዑካን በአዲግራት ሀገረስብከት፣ በባህር ዳር-ደሴ ሀገረ ስብከት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ተዘዋውረው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከየሰበካዎቹ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግል እና ምእመናን ጋር ተወያይተዋል።7 እንዲሁም በየክልኩ እና ዞኖች የሚገኙ የመንግሥት አስተዳደር አካላትን አነጋግረዋል። በተጨማሪም በተከሰተው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በየሚገኙባቸው የመጠለያ ጣብያዎች በመሄድ አጽናንተዋል፣ እንዲሁም ለዕለት ደራሽ የሚሆን ድጋፍ እና ዘላቂ የመልሶ ማቋቋም ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ ውይይቶችን አድርገው ተመልሰዋል።

በተለይ ወደ አዲግራት ሀገረስብከት ተጉዞ የተመለሰው የልዑካን ቡድን ከጉዞው እንደተመለሰ በጉብኝቱ ተዘዋውሮ የተመለከተውን እንዲሁም ከሰበካው ጳጳስ፣ ካህናት፣ ደናግል እና የምእመናን ተወካዮች ያዳመጠውን አጠናቅሮ ለዓለም ዓቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አጋር ተቋማት፣ ለምስራቅ አፍሪካ የጳጳሳት ጉባኤዎች ሕብረት፣ ለቫቲካን ኤምባሲ፣ ለኢትዮጵያ የገዳማት የበላይ ዐለቆች ጉባኤ እና ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ለሆኑ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አጋር ድርጅቶች በማቅረብ የጉብኝቱን ውጤት እና የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ በተመለከተ ግንዛቤ እንዲያገኙ አድርጓል።

በአጠቃላይ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ለደረሱ ጉዳቶች እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ቤተክርስቲያኒቱ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ የዕለት ደራሽ ድጋፍ በማቅረብ ላይ ትገኛለች። ከዚህ ድጋፍ ውስጥ ከ75% በላይ የሚሆነው ገንዘብ በትግራይ ክልል ለደረሰው አደጋ አጣዳፊ ምላሽ ለመስጠት የዋለ ነው።

በየካቲት ወር 2013 ዓ.ም. ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የዐብይ ጾም መግቢያን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት8 ላይ ደግሞ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ያላችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ካቶሊካውያን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ በጾም እና በጸሎት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣብያዎች የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ወደቀያቸው ተመልሰው የተለመደውን የተረጋጋ ሕይወት መምራት እንዲችሉ የጾማችን ፍሬ የሆነውን የፍቅር ሥራ ሁሉ እንድናከናውን ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከመጋቢት 21-22 ቀን 2013 ዓ.ም. የተከናወነው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን ጠቅላላ ጉባኤ በሀገሪቱ በተከሰቱት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ዕርዳታ ድርጅቶችን በማስተባበር ፈጣን ምላሽ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል።8 በፈጣን ድጋፍ መስጫ መርሃግብሩ ከታቀፉት አካባቢዎች መካከልም የአዲግራት፣ የባህር ዳር-ደሴ፣ የነቀምት እና የሶዶ ሀገረስብከቶች እንደሚገኙበት አሳውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብረሃነየሱስ የ2013 ዓ.ም. የጊታችን እና የመድኃኒታችን ትንሳኤ በዓልን በማስመልከት9 ባስተላለፉት መልዕክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ሲነሣ የሰጠን ትልቁ ስጦታ ሰላም ነው። እኛ እርሱን አምነነው እንድንከተለው እና የሰላም መሣሪያ እንድንሆን ጠርቶናል። ዛሬ በሃገራችን በሀዘን ሆነን የምናየው በጐሣና በሃይማኖት ባለን ልዩነት ላይ ተመስርተን በጥላቻ ንግግር፣ የሰውን ሕይወት በማጥፋት፣ ንብረትን በማውደም፣ በመዝረፍ፣ ሰዎችን በማሳደድ፣ የሃሳብ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት በመሞከር እና ከሰላም፣ ከይቅር ባይነት ይልቅ ጥላቻን በመዝራት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ትውልድ የሚተላለፍ መርዝ ትተን ኃጢያትን ያሸነፈው፣ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ በሚሰጠን ኃይልና ጸጋ ይሄን መጥፎ ሁኔታ መሻገር አለብን ብለዋል።

አክለውም የሀገራችን ሕዝቦች ሁሉ ሰላም ፈላጊዎች ናቸው፤ ሁሉም ጸሎታቸው ስለ ሰላም ነው። ይህች ሰላም ደግሞ በጥል በጦርነት በኃይል የምትገኝ አይደለችም። ስለሆነም ይህን ሰላም ማግኘት የምንችለው እርስ በእርስ በመዋደድ በመያያዝ በትዕግስትና በመቻቻል ሲሆን በመለኮታዊ ቃሉ “ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ ለእነርሱ አድርጉላቸው” (ሉቃ.6፣31) የሚለውን ቃል ይዘን ስንመራ ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር አብ መንፈሱን አብልጦ እንዲሰጠን መለመን አለብን። ያሉት ብፁዕነታቸው ለዚህ ደግሞ ራሳችንን በንፁህ ልብና ሕሊና አቅርበን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ እውነት እየተመራን በፍቅርና በደግነት ለመኖር የነፍሳችን አባት ወይም ባለቤት የሆነውን አምላካችንን ሌትና ቀን ሳናቋርጥ በመጸለይ አሁን የገባንበት ችግርና መከራ እንዲሁም ጭንቀት፣ ስደት፣ መገፋት፣ ጦርነት ሁሉ ተወግዶ የእርስ በእርስ መዋደድንና ፍቅርን እንዲሰጠን ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ቂምና በቀልን፣ ክፋትና ጥላቻን፣ ጭንቀትና ሐዘንን፣ ደካማነትን አውጥቶ በእርሱ ፋንታ ሰላምና እርቅን ባለፈውም ነገር መጽናናትን እንዲሰጠን እርሱ የሚጠላውን መሥራት ትተን እርሱ የሚወደውን እናድርግ ብለዋል።

እግዚአብሔር በአርዓያና በአምሳሉ ፈጥሮ ካስቀመጠን ከእርሱ ልጅነት ዝቅ ብለን፤ በጦርነት የሰው ነፍስ በማጥፋት፣ ሰውን በማሳደድና በማሰቃየት እግዚአብሔርንና ሰዎችን የሚያሳዝን ስሜት ፈጥሮብናል። በላያችን በነገሡት ነገሮች እግዚአብሔር የሰጠን ጸጋ እየከሰመ እንዳይሄድ መጠንቀቅ አለብን። በየቦታው ጥይት በሰዎች ላይ እየዘነበ ግልጽ ግድያና ሽብር፣ ስደትና መከራ እየተስፋፋ ሁላችንም ሰላም ነን ለማለት አንችልምና ሁሉን አቁመን ሰላምን እንፈልጋት እንከተላትም (መዝ. 3፣14) በማለት የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከእነዚህ ሁሉ በተጨማሪ የተለያዩ ካህናት፣ ደናግል፣ እንዲሁም ምእመናን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ እና በተሳተፉባቸው ልዩ ዝግጅቶች የንጹሃንን ሕይወት መቅጠፍ፣ ሰዎችን በማናቸውም ምክንያት ለጉዳት መዳረግ እና ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀል የሚወገዝ ተግባር መሆኑን እና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጽኑ የምትቃወመው ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል። ከእነዚህም ጥቂቶቹን ለመግለጽ ክቡር አባ ኃይለገብርኤል መለቁ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ በሰዎች መብት፣ በሰላም እና ፍትህ ዙሪያ ግንዛቤ አስጨብጠዋል። ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ ከተለያዩ የሬዲኦ፣ የቴሌቪዥን ጣብያዎች ጋር ያደረጓቸው ቃለ ምልልሶች በተለይ ረቡዕ ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም.10 እና ቅዳሜ ሚያዝያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም.11 በታተሙት የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ላይ ሰዎችን መግደልና ማፈናቀል በሰው ዘንድ የተወገዘ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተጠላ ኃጢአት መሆኑን በግልጽ አስረድተዋል።

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዛሬም በመላው ሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ሰዎች ከግጭት እና ጦርነት በጸዳ አካባቢ እንዲኖሩ ማድረግ የሚገባትን ሁሉ በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን አሁንም መንግሥት ግጭቶች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ያሉ ወንጀል ነክ ሁኔታዎችን በፍጥነት በማጣራት የዜጎችን ሰብዓዊ መብትን እና ክብርን የገሰሱ አካላት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ታሳስባለች።

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ፣ ይጠብቅ !

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት 

02 June 2021, 13:28