ብጹዕ ፓትሪያርክ አቡነ ፒዬር ባቲስታ በኢየሩሳሌም በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ  ብጹዕ ፓትሪያርክ አቡነ ፒዬር ባቲስታ በኢየሩሳሌም በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ  

በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል የተከሰተው ቀውስ በውይይት የሚፈታ ነው ተባለ

በቅድስት አገር የኢየሩሳሌም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ፒዬር ባቲስታ ፒሳ ባላ በፍልስጤምና እና እስራኤል መካከል የተቀሰቀሰው ጥቃት እንዲበርድ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ውይይት እንዲካሄድ አሳስበዋል። ለዚህ ጥቃት ዋና መነሻው ከዚህ በፊት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ቁስል ሳይታከም በመቆየቱ ነው ብለው ይህም ከፍተኛ የውስጥ አመጽን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባሁኑ ወቅት የእስራኤል አውሮፕላኖች በጋዛ ውስጥ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ መሆናቸው እና በሌላ ወገንም ከጋዛ በኩል የሐማስ ታጣቂዎች ተወንጫፊ ሚሳይሎችን ወደ እስራኤል በመወርወር ላይ መሆናቸው ታውቋል። ከሁለቱም መሣሪያ ታጣቂዎች በኩል የሚወጣው ዜና እንደሚያመለክተው የእስራኤል አውሮፕላኖች ከ150 በላይ ኢላማዎች ላይ ድብደባ ማካሄዳቸውን እና ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ሚሳይሎች ከጋዛ ወደ እስራኤል መወንጨፋቸውን ገልጸዋል። እስከ ዓርብ ግንቦት 6/2013 ዓ. ም ድረስ በፍልስጤም በኩል የሞቱት ሰዎች ቁጥር 119 ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰላሳ አንዱ ሕጻናት መሆናቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት አስታውቀዋል። አክለውም በፍልስጤም ውስጥ በሚኖሩ አረቦች እና አይሁዳዊያን መካከል በተለይም በአገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት ውስጥ አዳዲስ አመጾች መቀስቀሳቸውን ገልጸዋል። በኢየሩሳሌም ውስጥ የተነሳው አመጽ መቀዝቀዙን የኢየሩሳሌም ካቶሊካዊ ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ፒዬር ባቲስታ ፒሳ ባላ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

በኢየሩሳሌም የላቲን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ፒዬር ባቲስታ ፒሳ ባላ በአገራቱ መካከል ሰላምን ለማውረድ ምዕመናን በጸሎት መተባበር እንደሚያስፈልግ አሳስበው ሁለቱ ወገኖች ለውይይት እንዲቀርቡ አደራ ብለዋል። ከሁለቱም ወገኖች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እየተስፋፉ መሆኑን ተናግረው የአመጹ መነሻ በሆነች ኢየሩሳሌም ሁከቱ ረገብ ማለቱን ተናግረዋል። ዓርብ ግንቦት 6/2013 ዓ. ም. ከተካሄደው የሙስሊም ማኅበረሰብ ጸሎት በኋላ አመጽ እንደሚቀሰቀስ የተፈራ ቢሆንም አልፎ አልፎ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን እና መጠነኛ አመጾች መኖራቸውን ብጹዕ ፓትሪያርክ አቡነ ፒዬር ባቲስታ ፒሳ ባላ ገልጸዋል።

በሁለቱም አካባቢዎች በሚኖሩ አረቦች እና አይሁዳዊያን መካከል አመጽ መኖሩን ገልጸው የግጭቶችን ምክንያት መለየት ለጊዜው አስቸጋሪ እንደሆነ እና እስካሁን አብረው በቆዩባቸው ዓመታት በተለይም በአረቦች መካከል የመገለል ስሜት በማደጉ ምክንያት ተስፋ መቁረጥ መኖሩን ገልጸዋል። “ያም ሆኖ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለሚከሰቱ አመጾች መነሻው አንድ ነው” ያሉት ብጹዕ አቡነ ፒዬር ባቲስታ ፒሳ ባላ፣ የሁለቱም ወገኖች  ጉዳይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ችላ መባሉ እና መልስ ሳያገኙ ለበርካታ ዓመታት መቆየቱ፣ ከእነዚህም መካከል የኢየሩሳሌም ከተማ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ሳይወሰን መቆየቱ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል። እነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት በጉልበት ወይም በኃይል ሳይሆን በስምምነት እንደሆነ አስረድተው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ቁስል ሳይፈወስ ለዓመታት መቆየቱ ሁል ጊዜ ለግጭቶች ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ጦርነት እና ወታደራዊ ጥቃቶች ለችግሩ መፍትሄ አይሆኑም ያሉት ብጹዕ አቡነ ፒዬር ባቲስታ ፒሳ ባላ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለረጅም ዓመታት ለዘለቁት ችግሮች መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው በውይይት መሆኑን ተናግረዋል።

15 May 2021, 16:29