ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል  

የሚያዝያ 24/2013 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ከሙታን የተነሳው ጌታ ሁላችንንም ያለገደብ ይወደናል!

የእለቱ ንባባት

1.      የሐዋርያት ሥራ 34-43

2.    መዝሙር 117

3.    ቆላስያስ 3፡1-4

4.    ማርቆስ 24፡13-35

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ገዙ። በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጠዋት በማለዳ፣ ገና ፀሓይ እንደ ወጣች፣ ወደ መቃብሩ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ “ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።

ቀና ብለው ሲመለከቱ፣ በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከደጃፉ ላይ ተንከባሎ አዩ። ወደ መቃብሩ እንደ ገቡም፣ ነጭ ልብስ የለበሰ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ።

እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትደንግጡ፤ የምትፈልጉት የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው፤ እርሱ ተነሥቶአል፤ እዚህ የለም፤ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውላችሁ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ ‘ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ሴቶቹም እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሽተው ወጡ፤ ፈርተው ስለ ነበር ለማንም አንዳች አልተናገሩም።

የእለቱ አስተንትኖ

ሴቶቹ ቅባት የሚቀባ አካል እንደሚያገኙ አስበው ነበር ወደ እዚያ ቅባታቸውን ይዘው የሄዱት፣ ነገር ግን ያገኙት ባዶ መቃብር ነበር። ወደ እዚያ የሄዱት አንድ በሞተ ሰው ለማዘን አስበው ነበር፣ ይልቁንም የሰሙት በሕይወት እንደ ሚኖር የሚገልጽ አዋጅ ነበር። በዚህ ምክንያት የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደ ምነግረን ሴቶቹ እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሽተው ወጡ”  (ማርቆስ 16፡8)። መደነቅ። በመቃብሩ ላይ የነበረው ድንጋይ ተንከባሉ በማየታቸው እና ነጭ ልብስ ለብሶ በውስጡ የቆመ አንድ ወጣት ሲመለከቱ ልባቸው በመገረም እና በፍርሃት የተሞላ የተቀላቀለ ስሜት ውስጥ ገብተው ነበር። “አትደንግጡ፤ የምትፈልጉት የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው፤ እርሱ ተነሥቶአል” (ማርቆስ 16፡6) የሚለውን ቃል በመስማተቸው ተደንቀው ነበር። ከእዚያም በመቀጠል መልአኩ በመልእክትቱ “ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ‘ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” (ማርቆስ 16፡ 7) በማለት ይነግራቸዋል። እኛም ይህንን የፋሲካ መልእክት መቀበል ይኖርብናል። እናም ይህንን የትንሳኤ መልእክት ተቀብለን ከሞት የተነሳው ጌታ ወደ ሚያመልክተን ወደ ገሊላ እንሂድ። ስለእዚህ “ወደ ገሊላ መሄድ” ማለት ምን ማለት ነው?

ኢየሱስ ያስደንቀናል፣ እምነት ሕያው እንዲሆን ያደርጋል

ወደ ገሊላ መሄድ ማለት በመጀመሪያ ደረጃ እንደገና በአዲስ መልክ መጀመር ማለት ነው። ለደቀ መዛሙርቱ ጌታ በመጀመሪያ እርሱ ወደ ሚፈልግበት ስፍራ እንዲጓዙ እና እርሱን እንዲከተሉት ወደ ጋበዛቸው የመጀመሪያ ስፍራ ተመልሰው እንዲሄዱ ማለቱ እንደ ሆነ ይገባቸዋል። በመጀመሪያ ከእርሱ ጋር የተገናኙበት ስፍራ እና የእርሱን ፍቅር በመጀመርያ የቀመሱበት ስፍራ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዓሳ ማጥመጃ መረቦቻቸውን ትተው በመሄድ ኢየሱስን ተከትለው ስብከቱን በማዳመጥ እና እሱ ያደረጋቸውን ተአምራት እየተመለከቱ ነበር። ሆኖም ሁል ጊዜም ከእርሱ ጋር ቢሆኑም፣ ነገር ግን እሱን ሙሉ በሙሉ አልተረዱትም ነበር። በተደጋጋሚ ቃላቱን በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ስለነበረ በመስቀሉ ፊት ትተውት ሸሹ። ይሁን እንጂ  ከሙታን የተነሳው ጌታ ቀድሟቸው ወደ ገሊላ እንደ ሚሄድ እና ከሙታን የተነሳውን ጌታን በእዚያ እንደ ሚያገኙት የምያመለክት መልእክት ይልክባቸዋል። እርሱ ቀድሟቸው ይሄዳል። እርሱ በፊታቸው ቆሞ እሱን እንዲከተሉ ያለማቋረጥ ይጠራቸዋል። እርሱ “ቀደም ሲል ይህንን ተልዕኮ ከጀመርንበት ስፍራ አሁንም ቢሆን በአዲስ መልክ እንጀምር። እንደገና እንጅመር። የሆነው ነገር ቢሆንም እንኳን እንደገና ከእኔ ጋር በአዲስ መልክ እንድትጀምሩ እፈልጋለሁ” ይላቸዋል። በእነዚህ ገሊላዊያን ውስጥ በሽንፈታችን ጎዳና ላይ አዳዲስ መንገዶችን በሚከፍተው የጌታ ማለቂያ በሌለው ፍቅር መደነቅ እንጀምራለን።

ይህ እኔ ለእናንተ የማቀርበው የመጀመሪያው የፋሲካ መልእክት ነው- ሁሌም ውድቀቶች ቢኖሩብንም እንኳን እግዚአብሔር በውስጣችን ሊያነቃን የሚችል አዲስ ሕይወት ስላለ ሁል ጊዜ በአዲስ መልክ መጀመር ይቻላል። በልባችን ውስጥ ከሚገኘው ፍርስራሽ እግዚአብሔር የጥበብ ሥራን ሊፈጥር ይችላል። ከተበላሸው የሰው ልጅ ቅሪታችን እግዚአብሔር አዲስ ታሪክ ማዘጋጀት ይችላል። እርሱ ከፊት ለፊታችን መሄዱን አያቆምም -በመከራ ፣ ባድማ በሆነ ሥፍራ፣ በሞት እና በመስቀል ውስጥ ብናልፍም እንኳን እንደገና በሚነሳው የሕይወት ክብር ውስጥ ፣ በሚቀየር ታሪክ ፣ እንደገና በመወለድ ተስፋ ውስጥ እንድንሳተፍ ያደርገናል። በዚህ በተፈጠረው ወረርሽኝ ጨለማ ወራቶች ውስጥ እንደገና እንድንነሳ እና መቼም ተስፋ እንዳንቆርጥ ስለሚያደርገን ከሙታን የተነሳውን ጌታን እናዳምጠው።

ወደ ገሊላ መሄድ ማለት ሕይወታችንን በአዲስ መልክ መኖር መጀመር ማለት ነው!

ወደ ገሊላ መሄድ ማለት በአዳዲስ መንገዶች ላይ መጓዝ ማለት ነው። ከመቃብር ስፍራ ርቆ መሄድ ማለት ነው። ሴቶቹ ኢየሱስን በመቃብር ውስጥ ይፈልጉት ነበር፣ ከእርሱ ጋር በነበራቸው ጊዜያት ውስጥ ያጋጠሟቸውን ነገሮች ለማስታወስ በማሰብ ወደ እዚያው ሄዱ። ሀዘናቸው ወደ ደስታ ለመቀየር ወደ እዚያው ሄዱ። አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የገጠሙንን አስደሳች የሆኑ ነገሮችን አሁን በቀላሉ ለማስታወስ የሚያስችል የእመነት ዓይነት አለ። ብዙ ሰዎች እንደዚህ ያለ “አስታዋሽ የሆነ እምነት” ያጋጥማቸዋል ፣ ኢየሱስ ባለፉት ጊዜያት ከእነርሱ ጋር የነበረ፣ በልጅነታቸው ጊዜ የነበረ፣ ነገር ግን አሁን ሩቅ የሆነ ጓደኛ እንደ ነበረ፣ በልጅነታቸው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በሚማሩበት ወቅት ተከስቶ የነበረ፣ ከብዙ ጊዜ በፊት ተከስቶ የነበረ ክስተት አድርገው ሊቆጥሩት ይችሉ ይሆናል። በልማዶች ፣ ካለፉት ነገሮች ፣ ከልጅነት ጊዜ አንስቶ የነበረ፣ በልጅነት ትዝታዎች የተዋቀረ እምነት ፣ ነገር ግን የእዚህ ዓይነቱ እምነት የሚያንቀሳቅሰኝ ወይም የሚፈታተነኝ እምነት አይደለም። በሌላ በኩል ወደ ገሊላ መሄድ ማለት እምነት በሕይወት ለመኖር ወደ መንገዱ መመለስ እንዳለብን መገንዘብ ማለት ነው። የመጀመሪያውን የጉዞ ደረጃዎች ፣ የመጀመሪያውን ገጠመኝ በማስታወስ እና በመደነቅ በየቀኑ መታደስ አለበት። እናም እሱ ሁሉንም ነገር ቀድሞውኑ ያውቃል ብሎ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በእግዚአብሔር መንገዶች የሚደነቁትን ትህትናን ይቀበላል ፣ በእርሱ መታመናችንን መቀጠል አለብን። እንግዲያው እግዚአብሔር በልጅነት ትዝታችን መካከል ሊቀመጥ እንደማይችል በመገንዘብ ሕያው እና በሚያስደንቁ ነገሮች የተሞላ መሆኑን ለማወቅ ወደ ገሊላ እንሂድ። ከሙታን ተነስቶ ፣ ኢየሱስ እኛን ማስገረሙን መቼም አያቆምም።

ይህ እንግዲህ ሁለተኛው የፋሲካ መልእክት ነው-እምነት ያለፈ ትውስታዎችን የሚያስታውሰን የፎቶ አልበም አይደለም ፤ ኢየሱስ ጊዜ ያለፈበት አይደለም። እዚህ እና አሁን በሕይወት አለ። በጥልቀት በተስፋዎቻችን እና በሕልሞቻችን ውስጥ በየቀኑ ፣ በሚያጋጥሙን እያንዳንዱ ሁኔታዎች ውስጥ ፣ በጽናት መቋቋም በሚኖርብን እያንዳንዱ ፈተና ውስጥ ከእኛ አጠገብ ሆኖ ይራመዳል። እኛ ባልጠበቅንበት ጊዜ አዳዲስ በሮችን ይከፍታል፣ ያለፈውን ጊዜ ወይም የዛሬውን ነቀፌታ ወደ ናፍቆት እንድንቀይር ያሳስባል። ምንም እንኳን ሁሉም ነገር እንደጠፉ ሆኖ ቢሰማንም ፣ ኢየሱስ ባመጣው አዲስ ነገር ለመደነቅ ራሳችንን እንክፈት፣ እርሱ በእርግጥ ያስደንቀናልና።

ወደ ገሊላ መሄድ ማለት ወደ ከተማዎቻችን ዳርቻዎች መሄድ ማለት ነው

ወደ ገሊላ መሄድም እንዲሁ ወደ ከተማቻችን ዳርቻ መሄድ ማለት ነው። ገሊላ አውራጃ ነበረች: - በዚያ የተለያዩ እና የማይነጣጠሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ሐይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓታዊ ንጽህና በጣም የራቁ ነበሩ። ሆኖም ኢየሱስ ተልእኮውን የጀመረው ከእዚያ ነው። እዚያም ከቀን ወደ ቀን ለመኖር ለሚታገሉ ፣ ለተገለሉ ፣ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ እና ለድሆች መልእክቱን እዚያው አመጣ። እዚያም ተስፋ የቆረጡትን ወይም የጠፉትን ፣ ወደ ሕልውናቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ፊት እና ከእነርሱ ጋር አብሮ ሊኖር የሚችለውን እግዚአብሔርን አመጣላቸው፣ ምክንያቱም በእሱ ፊት ማንም አናሳ፣ የማይገለል ስለሆነ። የተነሳው ጌታ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እለት ተእለት ኑሮዋቸው እንዲመለሱ ፣ በየቀኑ ወደ ሚጓዙባቸው ጎዳናዎች እንዲሄዱ፣ ወደ የከተሞቻቸው ማዕዘናት እንዲሄዱ አሁንም እየጠየቃቸው ነው። እዚያ ጌታ ከእኛ ቀድሞ በመሄድ በአካባቢያችን ባሉ ሰዎች ፣ የእኛን ቀን በሚጋሩ ሰዎች፣ በቤቶቻችን፣ በሥራ ገበታችን፣ ችግሮቻችንን እና ተስፋዎቻችንን በሚጋሩ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እርሱ ራሱን እንዲገኝ ያደርጋል። በገሊላ ውስጥ ትልቅ ሕልም በሚያልሙ ሰዎች እና ያለሙት ሕልም ባለመሳካቱ የተነሳ በገዛ ፈቃዳቸው ተስፋ የቆረጡ ሰዎች እንባ፣ እነዚህን እና እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች የተነሳ ተስፋ በቆረጡ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ፊት ከሙታን የተነሳውን ጌታ ማግኘት እንደምንችል እንማራለን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በመከራ ውስጥ በሚገኙ እና በድሆች እና ተገልለው በሚኖሩ ሰዎች ፊት ላይ እርሱን እንመለከትለን። የእግዚአብሔር ታላቅነት በትንሽነት እንዴት እንደሚገለጥ ፣ ውበቱ በድሃ እና በቀላሉ እንዴት እንደሚበራ በማየት እንገረማለን።

ከሙታን የተነሳው ጌታ ሁላችንንም ያለ ገደብ ይወደናል

እናም ይህ ሦስተኛው የትንሳኤ በዓል መልእክት ነው - ከሙታን የተነሳው ጌታ ኢየሱስ ያለ ገደብ ይወደናል እናም በእያንዳንዱ የሕይወታችን ጊዜ ውስጥ ይገኛል። በዓለማችን እምብርት ውስጥ እርሱ ራሱን እንዲገኝ አድርጎ እራሱን ካቀረበ በኋላ መሰናክሎችን እንድናሸንፍ ፣ ጭፍን ጥላቻን እንድናስወግድ እና የዕለት ተዕለት ኑሮን ፀጋ እንደገና እንድናገኝ በየቀኑ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ እነዚህን በገሊላ የተከናወኑ ነገሮችን ለማወቅ እንሞክር። ከእሱ ጋር ሕይወት ይለወጣል፣ ከሁሉም ሽንፈቶች ፣ ክፋቶች ፣ እና ሁከቶች ሁሉ ፣ ከመከራ እና ሞት ሁሉ በላይ ፣ ተነስቶ የሚኖር እና ታሪክን የሚመራው እርሱ ከሙታን የተነሳው ጌታ ብቻ ነው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ -በዚህ ምሽት የጨለማ ሕይወት እያጋጠማችሁ ከሆነ፣ ገና ያልነጋ ጊዜ እያጋጠመህ ከሆነ፣ ብርሃንህ እየደበዘዘ ወይም ሕልማችሁ እየጨነገፈ ሆኖ ከተሰማችሁ፣ በትንሳኤ መልእክት ለመደነቅ ልብዎን ይክፈቱ “አትፍሩ ፣ ተነስቷል! እርሱ በገሊላ ይጠብቃችኋል”።  የምትጠብቁት ነገር እንዲያው ሳይፈጸም በከንቱ አይቀርም፣ እንባችሁ ይታበሳል፣ ፍርሃታችሁ በተስፋ ይተካል። ጌታ ከእናንተ ይቀድማልና ከእናንተ በፊት ይሄዳል። እናም ፣ ከእሱ ጋር ሕይወት እንደገና በአዲስ መልክ ይጀምራል።

ምንጭ፡ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት 25/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

01 May 2021, 11:11