የግንቦት 22/2013 ዓ.ም የአምስተኛው የትንሳኤ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የግንቦት 22/2013 ዓ.ም የአምስተኛው የትንሳኤ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የግንቦት 22/2013 ዓ.ም የአምስተኛው የትንሳኤ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.      የሐዋርያት ሥራ 9፡26-31

2.    መዝሙር 21

3.    1ዮሐንስ 3፡18-24

4.    ዮሐንስ 15፡1-8

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የወይን ግንድና ቅርንጫፎቹ

“እውነተኛው የወይን ተክል እኔ ነኝ፤ አትክልተኛውም አባቴ ነው። እርሱም በእኔ ያለውን፣ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቈርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን የበለጠ እንዲያፈራ ይገርዘዋል። ከነገርኋችሁ ቃል የተነሣ እናንተ አሁን ንጹሓን ናችሁ። በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም።

“እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በእርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና። በእኔ የማይኖር ተጥሎ እንደሚደርቅ ቅርንጫፍ ነው፤ እንዲህ ያሉት ቅርንጫፎች ተለቅመው ወደ እሳት ይጣላሉ፤ ይቃጠላሉም። 7በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ፤ ይሰጣችኋልም። ብዙ ፍሬ በማፍራት ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብትገልጡ፣ በዚህ አባቴ ይከብራል።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በዚህ በፋሲካ አምስተኛው እለተ ሰንበት ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ. 15 1-8) ውስጥ ጌታ ራሱን እንደ እውነተኛ የወይን ተክል አድርጎ ያቀርባል ፣ እናም እኛ ቅርንጫፎች በመሆናችን የተነሳ ከእርሱ ጋር ካልተባበርን በስተቀር መኖር እንደማንችል ስለእኛ ይናገራል። እናም ስለዚህ እርሱ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎች ናችሁ” ይላል (ዮሐንስ 15፡5)። ያለ ቅርንጫፎች የወይን ግንድ ሊኖር አይችልም፣፣ እና በተቃራኒው ቅርንጫፍ ከሌለ የወይን ግንድ ሊኖር አይችልም። ቅርንጫፎቹ ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ አይደሉም ፣ ግን ሙሉ በሙሉ የሚመረኮዙት የህልውናቸው ምንጭ በሆነው የወይን ተክል ላይ ነው።

ኢየሱስ “በእኔ ኑሩ” የሚለውን ግስ አጥብቆ ይናገራል። በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ንባብ ውስጥ ሰባት ጊዜ የሚደጋገም ቃል ነው። ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እና ወደ አብ ከመሄዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ጋር አንድ ሆነው መኖር መቀጠላቸውን ሊያረጋግጥላቸው ይፈልጋል። እሱም “በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ ውስጥ እኖራለሁ” (ዮሐንስ 15፡ 4) ይላለናል። ይህ በእኔ ኑሩ የሚለው ቃል በራሱ በሕይወት በመግባት ጌታ እንዲወደን በመፍቀድ በጌታ ውስጥ “አንቀላፍቶ” ዝም ብሎ የመኖር ጥያቄ አይደለም። ይህ አይደለም። በእርሱ ውስጥ መኖር ማለት እርሱ ለእኛ በሚያቀርብልን መሰረት በኢየሱስ ውስጥ መኖር፣ በንቃት መኖር ማለት ነው፣ እንዲሁም ደግሞ በምላሹ እርሱ በእኛ ውስጥ እንዲኖር መፍቀድ ማለት ነው። ለምን? ያለ ወይኑ ቅርንጫፎች ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ለማደግ እና ፍሬ ለማፍራት የሕይወት ምንጭ ያስፈልጋቸዋል፣ ዛፍ ግንዱ ላይ ፍሬ የማያበቅል በመሆኑ የተነሳ ወይኑም ቅርንጫፎቹን ይፈልጋል። እሱ እርስ በእርሱ የመደጋገፍ ፍላጎት ነው ፣ ፍሬ ለማፍራቱ ደግሞ እርስ በእርስ የመተዛዘን ጥያቄ ነው። እኛ በኢየሱስ እንኖራለን ኢየሱስም በእኛ ውስጥ ይኖራል።

በመጀመሪያ ለእኛ እርሱ ያስፈልገናል። ጌታ ትእዛዛቱን ከማክበራችን በፊት፣ ብሩክ ከመሆናችን በፊት፣ የምሕረት ተግባራትን ከመፈጸማችን በፊት፣ ከእርሱ ጋር አንድ መሆን ፣ በእርሱ ውስጥ መቆየት አስፈላጊ መሆኑን ሊነግረን ይፈልጋል። በኢየሱስ ውስጥ ገብተን መኖር ካልቻልን ጥሩ ክርስቲያን መሆን አንችልም። በእርሱ በኩል በምትኩ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን (ፊል 4፡13)። በእርሱ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን ፡፡

ነገር ግን ኢየሱስ እንኳን እኛን ይፈልጋል ፣ እንደ ወይኑ ከቅርንጫፎቹ እርሱ ከእኛ ጋር መሆን ይፈልጋል።  ምናልባት ይህ ማለት ለእኛ ድፍረት ይመስላል ፣ እናም እኛ እራሳችንን እንጠይቃለን-ኢየሱስ በምን መልኩ ነው እኛን የሚፈልገው? እርሱ የእኛን ምስክርነት ይፈልጋል። ልክ እንደ ቅርንጫፎቹ መስጠት ያለብን ፍሬ እንደ ክርስቲያኖች በሕይወታችን ስለ እርሱ መመስከር ይገባናል። ኢየሱስ ወደ አብ ካረገ በኋላ የደቀመዛሙርቱ ተግባር - የእኛ ተግባር ነው - በቃላት እና በተግባር ወንጌልን ማወጅ መቀጠል ነው። ደቀ መዛሙርቱም - እኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት - ይህን የምናደርገው ስለ ፍቅሩ በመመስከር ነው-ፍሬ ማፍራት ፍቅር ነው ከክርስቶስ ጋር ተያይዘን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች እንቀበላለን እናም በዚህ መንገድ ለባልንጀሮቻችን መልካም ማድረግ ፣ ለህብረተሰቡ እና ለቤተክርስቲያን መልካም ማድረግ እንችላለን። ዛፉ በፍሬው ይታወቃል። እውነተኛ የክርስቲያን ሕይወት ስለ ክርስቶስ ይመሰክራል።

እናም ይህንን ለመፈጸም እና ለማሳካት እንዴት እንችላለን? ኢየሱስ እንዲህ ይለናል-“በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ፤ ይሰጣችኋልም” (ዮሐንስ 15፡7)። ይህ ደግሞ ደፋር የሆነ ሐስተሳሰብ ሊመስል ይችላል፣ የምንለምነው ነገር እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። የሕይወታችን ፍሬያማነት በጸሎት ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ እርሱ ለማሰብ ፣ እሱን ለመምሰል ፣ ዓለምን እና ነገሮችን በኢየሱስ ዓይኖች ለመመልከት መጠየቅ እንችላለን። እናም በዚህ መንገድ ከድሆች እና በጣም ከሚሰቃዩት ጀምሮ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን መውደድ ፣ በልቡም መውደድ እና የመልካምነትን ፣ የበጎ ፍሬ ፣ የሰላም ፍሬዎችን ለዓለም ማምጣት እንችላለን።

ለድንግል ማርያም አማላጅነት እራሳችንን በአደራ እንስጥ። እሷ ሁል ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሙሉ በሙሉ አንድነትን በመፍጠር ብዙ ፍሬ አፍርታለች። ከሙታን የተነሳውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለም ውስጥ መመስከር እንችል ዘንድ በክርስቶስ ፣ በፍቅሩ ፣ በቃሉ እንድንኖር እርሷ ሁላችንንም በአማላጅነቷ ትርዳን።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 24/2013 ዓ.ም በቫቲክን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ መእመናን ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

29 May 2021, 14:52