የቃሉ ነገረ-ክርስቶሳዊነት የቃሉ ነገረ-ክርስቶሳዊነት  

የቃሉ ነገረ-ክርስቶሳዊነት

በመለኮታዊ ቃል አማካይነት ሁሉም እውነታዎች የቅድስት ሥላሴ የእጁ ሥራ እንደ ሆነ ከዚህ እይታ እንረዳለን፣ ወደ ዕብራዊያን ሰዎች በተላከው መልዕክት ውስጥ የጸሐፊውን ሐሳብ ለመረዳት ስንሞክር “እግዚአብሔር በቀድሞ ዘመናት በተለያዩ ብዙ መንገዶችና፣ በነቢያት አማካኝነት ለአባቶቻችን ተናግረዋል፤ ነገር ግን በነዚህ በመጨረሻዎቹ ቀናት የሁሉ ነገር ወራሽ አድርጎ በሾመውና በዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች ሁሉ በእርሱ በተፈጠሩለት በልጁ አማካይነት ለእኛ ተናግሯል” (ዕብራዊያን 1፡ 1-2)። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ ሁሉ ቃሉን ለእኛ ማስተላለፉን መገንዘብ ምንኛ መልካም ነገር ነው፤ በእርግጥ “ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳንና” (ዘፍ 15፡18)፣ በሙሴ አማካኝነት የእስራኤልን ልጆች የራሱ ሕዝብ አድርጎ በመሰብሰባቸው (ዘጻአት 24፡8) ፣ በቃልና በተግበር እንደ አንድ ሕያውና እውነተኛ አምላክ ሆኖ ራሱን ለእነርሱ ገለጠላቸው። ይህም የሆነው እስራኤላውያን ከሰው ዘር ሁሉ ጋር በመሆን የእግዚአብሔርን መንገድ በሕይወት ውጣ ውረድ ሁሉ እንዲማሩ፤ ከዚህም አልፎ በነቢያት አማካይነት የሚነገርላቸውን የእግዚአብሔርን ድምጽ በመስማት ቀስ በቀስ የእርሱን መንገድ በሙላትና በግልጽ በመረዳት በአሕዛብ መካከል ራሳቸውን በሰፊው እንድያስተዋውቁ መፈለጉ የእርሱ ብቸኛ ዕቅዱ ነበር (መዝ 21፡28-29፣ 95፡ 1-3፣ ኢሳ 2፡1-4፣ ኤር 3፡ 17)” ።

ይህ የእግዚአብሔር ራሱን “ዝቅ የማድረግ” ተግባሩን የፈጸመው በአስገራሚ ሁኔታ ቃል ሥጋ በመሆኑ ነበር በፍጥረታት አማካይነት የተገለጠው፣ በደህንነት ታሪክ ዉስጥ የተላለፈዉ የዘለዓለም ቃል በክርስቶስ አማካይት ሰው ሆኖ “ከሴት ተወለደ” (ገላ 4፡4) ። እዚህ ላይ ቃል በመጀመሪያ የተገለጠው በውይይት ስልት፣ በተለያዩ ሐሳቦች ወይም በሕግ አስገዳጅነት አልነበረም። በዚህ ምክንያት እነሆ አሁን እኛ በኢየሱስ ፊት ተደላድለን እንገኛለን። የእርሱ ብቸኛና አስገራሚ ታሪክ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በይፋ የሚናገረው የማይለወጥ ቃሉ ነው። እንደምንረዳው ከሆነ “ክርስቲያን መሆን ማለት የሥነ-ምግባር ምርጫ ወይም ጥራዝ ነጠቅ የሆነ ሃሳብ ማፍለቅ ለምን አይሆንም፤ ነገር ግን ክርስቲያን መሆን ማለት ለሕይወት ጽኑ የሆነ አቅጣጫ፣ አዲስ የሕይወት አድማስ የሚሰጥ ሰውን ወይም ሁኔታዎችን መገናኘት ማለት ነው” ። የዚህ ዓይነት ያልተቋረጠ የመገናኘትና የግንዛቤ መንገድ የሚያድገው፣ የሚያስገርም የእግዚአብሔር ሥራ እኛ ሰዎች በራሳችን ግምት ወይም ምክንያት ልናልመው በማንችለው ሁኔታ በእርሱ አነሳሽነት በአማኞች ልብ ውስጥ ሲሞላ ነው።

ስለዚህ እኛ የምንናገረው “በእኛ መካከል ሥጋ ለብሶ ከእኛ ጋር ስለሚኖረው” (ዮሐ 1፡14) ከሰው አእምሮ በላይ ስለሆነውና ከዚህ በፊትም ተደርጎና ለወደፊትም ሊደረግ ስለማይችል ዘለዓለማዊ ቃል ነው። ይህ ቃል የሚያመለክተው የንግግር ቅንጅት አይደለም የተኖረበት ሕይወት እንጂ፤ የዓይን ምስክር የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ይለናል አንድ ልጅ ጸጋና እውነት ለብሶ ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን (ዮሐ 1፡14) ። ሥጋ ለብሶ ከእኛ እንደ አንዱ ስለሆነው የዘለዓለም ቃል የሐዋርያት እምነት ይህን ይመሰክራል። ይህ የሚያረጋግጥልን መለኮታዊ ቃል በእውነት በሰብዓዊ ቃላት መገለጽን ነው።

የአበውና የመካከለለኛው ክፍለ ዘመን ይህንን “የቃሉን ክርስቶሳዊ” ጎኑን ሲያሰላሰሉ ቀስቃሽ አገላለጽ ያለበትን ትንሽ የሆነው ቃል የሚለውን አባባል መጠቀማቸውን ያስታውሳሉ። “የቤተክርስቲያን አባቶችም የብሉይ ኪዳን በግሪክ ትርጓሜአቸው የትንቢተ ኢሳያስን አባባል በኋላም ቅዱስ ጳውሎስ የሚጠቅሰውን ቃል ሲያመለክቱ የእግዚአብሔር አዲሱ መንገድ እንዴት ቀደም ብለው በብሉይ ኪዳን እንደተነገረ ያሳያል። እንዲህም ሲል ይነበባል “እግዚአብሔር አምላክም ቃሉን አሳጥሮ በምህጻረ ቃል አስቀምጦታል (ትን.ኢሳ. 10፡23 ፣ ሮሜ 9፡28)…. ልጁ ራሱ ቃል ነው የዘለዓለም ቃል ትንሽ ሆነ፣ በከብቶች መመገቢያ ውስጥ እስኪሆን ድረስ ትንሽ ሆነ፡፡ እኛ እንድንረዳውና ቃሉ በእኛ እንዲዳሰስ ነው እርሱ ሕጻን የሆነው።” እንዲሁም አሁን ቃሉ የሚደመጥ ብቻ አይደለም ድምጽም ብቻ ያለው አይደለም ፤ ነገር ግን አሁን ቃሉ አካል አለው የሰውንም መልክ ይዟል ፤ እኛ ማየት የምንችለው እርሱ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።

የወንጌል መረጃዎችን በምናነብበት ጊዜ የምንረዳው የኢየሱስ ልዩ ሰብዓዊነት በትክክል የሚታየው በራሱ በቃለ እግዚአብሔር ነው። በፍፁም ሰብዓዊነቱ ሁል ጊዜም የአባቱን ፍቃድ ይፈጽማል ፤ ኢየሱስ ድምጹን በመስማት በፍጹም ማንነቱ ይታዘዝለታል ፤ አብን ያውቀዋል የእርሱንም ትዕዛዝ ይጠብቃል (ዮሐ 8፡ 55) ፤ አብ ለእርሱ የተናገረውን ሁሉ ለእኛ ይናገራል (ዮሐ 12፡ 50) አንተ የሰጠኸኝን ቃል እኔ ደግሞ መልሼ ለእነርሱ ሰጥቻቼዋለሁ (ዮሐ 17፡ 8) ኢየሱስ ለእኛ የተሰጠ መለኮታዊ ቃል በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ አዲሱ አዳም እውነተኛ ሰው እንከን በሌለበት መልኩ የራሱን ሳይሆን የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። እርሱ “በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ፊት በጥበብ ፣ በክብርና በዝናም እየጨመረ ይሄድ ነበር” (ሉቃ 2፡52) እንከን የለሽ በሆነ መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ለእኛ ይገልጻል ያስተላልፋልም (ሉቃ 5፡1 )።

የኢየሱስ ተልዕኮ ፍጻሜውን ያገኘው በፋሲካ ምስጢር ነው ፤ በዚህ ሁኔታ እኛ ራሳችንን “በመስቀሉ ቃል” ፊት እናገኛለን (1ቆሮ 1፡18) ። ለእኛ መናገር የፈለገውን ምንም ሳይቆጥብ ፣ ለነገ ሳይል በሙላት “ተናግሮ” ተልዕኮን ሲያበቃ አሁን ግን በሞታዊ ጸጥታ ቃሉ ዝም አለ። ይህን ልብ የሚነካውን ቃል የቤተክርስቲያን አባቶች ብዙ ካወጡና ካወረዱ በኋላ ከድንግል ማርያም ጋር ያመሳስላሉ ፣ እንደሁም “ተናጋሪውን ፍጥረት የፈጠረው የአብ ቃል ራሱ ቃለ አልባ ሆነ፣ በቃሉ ፈጥሮ ከእስትንፋሱ ሕይወት የሰጣቸውና የሚንቀሳቀሱትን ነገሮች ሁሉ የሚያንቀሳቅሱ የእርሱ ዓይኖች ሕይወት አልባ ሆኑ” ።  ይህ ነው “ታላቁ ፍቅር” ፤ ለወዳጆቹ ሕይወት ስለ ራሱን አሳልፎ የሰጠው ፍቅር (ዮሐ 15፡ 13) እኛም ሁላችን ፍቅሩን ተካፍለናል ፣ ቀምሰናል፣ አጣጥመናልም።

በዚህ በታላቁ ምስጢር ኢየሱስ እንደ አዲስ ቃልና እንደ ዘለዓለማዊ ኪዳን ሆኖ ተገልጧል ፤ በተቸነከረው ሥጋው አማካይነት መለኮታዊ ነጻነትና ሰብዓዊ ነጻነት በማያወላውል ሁኔታ በማይጠፋውና በዘለዓለማዊነት ሙላት ተገናኝተዋል ፣ ኢየሱስ ራሱ ቅዱስ ቁርባን በመሠረተበት በመጨረሻው እራት ላይ ሲናገር ለብዙዎች የሚፈሰው ደሙ አዲሱና ዘለዓለማዊ ኪዳን እንደሆነ ገልጾ ነበር (ማቴ 26፡ 28፤ ማር 14፡ 24፣ ሉቃ 22፡ 20) ፤ እንዲሁም ከባርነት ነጻ የሚያወጣን እውነተኛው የተሰዋ በግ እንደሆነ ራሱን ያመለክታል።

ይህ ፀጥታ የለበሰው ቃሉ በእውነተኛነትና በማያሻማ ትርጉም እጅግ በጣም አንጸባራቂ በሆነው በትንሣኤው ምስጢር ራሱን ገልጠዋል፣ ወይም ማንነቱን አሳይቷል ዝም እንዳለ አልቀረም። ክርስቶስ ሰው የሆነው ፣ የተቸነከረውና ሞቶ ከሞት የተነሣው የእግዚአብሔር ቃል እርሱ የሁሉም ጌታ ነው ፣ እርሱ ድል አድራጊ ነው ፤ እርሱ ሁሉን ፈጣሪ ነው እናም ሁሉም ነገር ለዘለዓለም በእርሱ ተጠቃሎ ይገኛል (ኤፌ 1፡ 10) ። ስለዚህ ያ ክርስቶስ ነው “የዓለም ብርሃን የሆነው” (ዮሐ 8፡12) “ብርሃኑም በጨለማ ያበራል” (ዮሐ 1፡ 5) ይህንን ብርሃን ጨለማው ከቶም አያሸንፈውም ። በዚህን ጊዜ ነው የመዝሙረ ዳዊትን 119 ትርጉም እኛ በስፋት መረዳት የምንችለው ፣ ይህም ቃል ሲነበብ “ቃልህ ለእግሬ መብራት ነው ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ 119፡ 105) ፤ ከሞት የተነሳው ይህ ቃል ታዲያ የማይለወጥና የማይጠፋ ዘወትር የመንገዳችን ብርሃን ነው። ከመጀመሪያ አንስቶ በክርስቶስ አማካይነት የእግዚአብሔር ቃል አካል ሆኖ እንደቀረበ ክርስቲያኖች ይረዱ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ፣ የሰው ዘር ሁሉ የሚፈልገው እውነተኛው ብርሃን ነው። በትንሣኤው ኃይል የእግዚአብሔር ልጅ የዓለም ብርሃን ሆኖ ተገለጸ፤ አሁን በተራችን እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋርና በእርሱ በመኖር በብርሃን መኖር እንችላለን።

“ቃሉ ክርስቶሳዊ” ማዕከል እንደነበረ ሁሉ አሁንም ቦታዉን ሳይለቅ ይኖራል ፣ ሥጋ በለበሰው ቃሉ ላይ የመለኮታዊ ዕቅድን ውህደት ማንፀባረቅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትልቅ ጉዳይ ነው።  አዲስ ኪዳን ፣ የፋሲካን ምሲጢር፣ በቅዱስ መጽሐፍ መሠረት የተከናወነና የእርሱ ፍጻሜ እውነተኛው ገጽታ አድርጎ ያቀርባል። ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያዉ የቆሮንጦስ መልዕክቱ ላይ ሲገልጽ ‘በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈው” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞቷል ይላል (1ኛ ቆሮ. 15፡3)። ሐዋርያው ጳውሎስም የጌታች የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ታሪክን በብሉይ ኪዳን ውስጥ በእግዚአብሔርና በህዝቡ መካከል ካለው የቃል ኪዳን ታሪክ ጋር ያገናኛል። በእርግጥም እርሱ የሚያመላክተን ታሪክ ውስጣዊ ጽንስ ሐሳብንና እውነተኛ ትርጉሙን የያዘው ከዚህ ክንውን በኋላ መሆኑን ነው። በፋሲካ ምስጢር “የቅዱስ መጽሐፍ ቃል” ፍጻሜን አግኝተዋል ፤ በሌላ አባባል ይህ ሞት የተከናወነው እንደ “ቅዱስ መጽሐፍ” ፈቃድ ነው ፤ ቃሉን በውስጡ ጠቅልሎ የያዘ ክንውንና ውስጣዊ እውነታ የተሞላበት ነው ፤ የእግዚአብሔር ቃል ፍፁም የሰውን “ሥጋ” እንደለበሰና ሰብዓዊ “ታሪክ” እንደሆነ የክርስቶስ ሞት ይመሰክራል።

“በቅዱሳት መጽሐፍት እንደተገለጸው በተመሳሳይ ሁኔታ የክርስቶስ ትንሣኤ ከሦስተኛው ቀን በኋላ ተከናውኗል” ፣ እንደ አይሁድ እምነት አንድ የሞተ ሰው አካል ከሶስተኛው ቀን በኋላ መበሰበስ ይጀምራል፤ ስለዚህ መበስበስን ሳያገኝ በተነሳው በክርስቶስ ኃይል ቅዱሳት መጽሐፍት ፍፃሜን አግኝቷል። ያንን ሐዋርያዊ ትምህርት ነበር ቅዱስ ጳውሎስ ለዛሬይቱ ቤተክርስቲያን በታማኝነት ያስተላለፈው (1ቆሮ 15፡3) ፣ ይኼውም ክርስቶስ ሞትን ድል ማድረጉ በእግዚአብሔር ቃል ጥበብ መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው። ይህ መለኮታዊ ኃይል ደስታንና ተስፋን ያመጣል ፤ ይህ ቃል በቃል ሲተረጎም ነጻ የሚያወጣን የፋሲካ ምስጢር ነው። በትንሳኤዉ ኃይል እግዚአብሔር ራሱ የክፋትና የሞትን ኃይል የሚያስወግደውን የቅድስት ሥላሴን ፍቅር ገለጠልን።

የእምነታችን መሠረት የሆኑትን እነዚህን ዐበይት ነገሮችን ሁሌ በማስታወስ በክርስቶስ አማካይነት በፍጥረታት መካከል ስላለው ስለጥልቅ አንድነት፤ በክርስቶስ ስለሆነው አዲስ ፍጥረትና አጠቃላይ የደህንነት ታሪክን ማሰላሰል እንችላለን።

ለምሳሌ ያህል ቁሳዊ ሥነ-ፍጥረትን ከአንድ መጽሐፍ ጋር ማነጻጸር ይቻላል ፣ ጋሊሊዮ ራሱ ይህን ምሳሌ ተጠቅሞ ስለነበር ራሱን በፍጥረት “ቅላጼ” እንደሚገልጽ እንደ አንድ ደራስ ሥራ ይቆጥር ነበር።  በዚህ ጣዕመ ዜማ አንዱ አንድ የተወሰነ ነገርን ያገኛል ይህም በሙዚቃው ቋንቋ አጠራር “ሶሎ” የሚባል ነው መልዕክቱም ለአንድ ተራ ሙዚቃ ወይም ድምጽ የተሰጠ በጣም አስፈላጊ የሆነው የአጠቃላይ የሥራው ትርጉም በእርሱ የተጣለበት ነው። ይህ “ሶሎ” ኢየሱስ ነው ሰማይና ምድርን ፍጡርና ፈጣሪን፣ ሥጋና መንፈስን አጠቃሎ የያዘው የሰው ልጅ ነው፣ እርሱ የፍጥረትና የታሪክ ማዕከል ነው ፣ በእርሱ ያለ ምንም ግራ መጋባት ደራሲውና ሥራው ይገናኛሉ።

ይህንንም ለማድረግ እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ታማልደን ።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

የጽሑፉ ምንጭ፡ Verbum Domini (የጌታ ቃል)

24 April 2021, 08:50