የምዕራብ አፍሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ለተፈናቃዮች ትኩረት እንዲሰጥ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የምዕራብ አፍሪካ ብጹዓን ጳጳሳት በ2020-2021 ዓ. ም. ባካሄዱት ሁለተኛው መንፈቅ ጉባኤ ላይ እንደገለጹት በቀጣናው ሳይፈታ የቆየው የውስጥ ተፈናቃዮች ችግር አዳዲስ ውጥረቶችን እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል። የችግሩን ምክንያት ሲገልጹ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውስጥ ተፈናቃዮች፣ እገዛ እና ድጋፍ በማድረግ ላይ ካለው ከተቀረው ማኅበረሰብ ጋር ተስማምቶ መኖር ቀላል አለመሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት ለሕዝብ የበለጠ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል
ብጹዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው እንደገለጹት፣ መንግሥት በቀጠናው ለተፈናቀሉት ሕዝቦች ከገባላቸው ቃል በተጨማሪ መረጋጋትን ለማምጣት ብቃት ባላቸው የመንግሥት ባለስልጣናት በኩል ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ማረጋገጫ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። ተፈናቃይ ሕዝብ እና አስተናጋጅ ማኅበረሰብ ተግባብተው በሰላም መኖር እንዲችሉ ለማድረግ በመካከላቸው የጋራ ውይይትን እና የመንግሥት ባለስልጣናትን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራት እንደሚያስፈልግ ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከል ገልጸዋል።
ልዩነት እና መገለል ሊኖር አይገባም
ብጹዓን ጳጳሳቱ በሰጡት አስተያየት፣ በተፈናቃዮች መካከል ልዩነት እና መገለል እንዳይፈጠር የሚያደርግ መርሃ ግብር ሊኖር እንደሚገባ አሳስበው፣ አንዳንድ ማህበረሰቦች ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ከእስላማዊ አሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተደርገው መታየታቸው ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል።
የታላቁ ኢማም የጳጳሳትን ጉባኤ መጎብኘት
የምዕራብ አፍሪካ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ጉባኤያቸውን የጎበኙትን የፋዳ ታላቁ ኢማም አቡበከር ኪናን ተቀብለው ያስተናገዱ መሆኑ ሲገለጽ፣ ታላቁ ኢማም በጉብኝታቸው ወቅት በቡርኪና ፋሶ ሰላም እና የሕዝቦች አንድነት እንዲያድግ ጸሎት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ታላቁ ኢማም በማከልም ለአሥርት ዓመታት በክርስቲያን እና ሙስሊም ማኅበረሰብ መካከል የቆየው መልካም ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።
ቀጣይነት ያለው አመጽ መካሄዱ
ፊዴስ የዜና ምንጭ፣ የካቲት 11/2013 ዓ. ም. በማሊ እና ቡርኪና ፋሶ በተካሄዱት የተለያዩ ጥቃቶች በርካታ ንጹሐን ሰዎች መገደላቸውን አስታውቆ፣ በቡርኪና ፋሶ ውስጥ በማርኮዬ እና ቶካባንጉ ከተሞች በተፈጸሙት ጥቃቶች የተገደሉት ሰዎች ወደ ዶልቤል እና ኒጀር ሲጓዙ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል። በዚህ ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲገደሉ፣ በዘጠኝ ስዎች መቁሰላቸው ፊዴስ የዜና ምንጭ አስታውቋል።