የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አርማ የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አርማ 

የፊሊፒን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን 500ኛ ዓመት የምስረታ በዓሏን ልታከብር መዘጋጀቷ ተገለጸ።

የካቶሊክ እምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፊሊፒን አገር የገባበትን 500ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓልን ለማክበር መዘጋጀቷን የአገሪቱ ቤተክርስቲያን አስታወቀች። የካቶሊክ እምነት ወደ ፊሊፒን የገባው ታዋቂው ፖርቱጋላዊ አገር አጥኚ፣ ፌርዲናንድ ማጂላን እ. አ. አ በ1521 ዓ. ም. ሰቡ የተባለች አውራጃን በጎበኛት ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከዚህም ጋር ተያይዞ የክርስትና እምነትም ወደ ፊሊፒን የገባው ከ500 ዓመት በፊት መሆኑን በማስታወስ በፊሊፒን የሚገኙ ሁለቱ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች በዓሉ ከሚከበርበት ከሚያዝያ ወር አስቀድመው በተለያዩ ዝግጅቶች የደመቁ በዓላትን በማክበር ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በመላው ፊሊፒን የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች የቤተክርስቲያናቸው ምስረታ 500ኛ ዓመት በዓል ለማክበር በሚዘጋጁበት ባሁኑ ወቅት “የኢዮቤልዩ ቤተክርስቲያናት” ተብለው መሰየማቸው ታውቋል። የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሮሞሎ ቫለስ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን የኢዮቤልዩ ዓመት ንግደት ወይም መንፈሳዊ ጉዞን በብርሃነ ትንሳኤው እሑድ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር መጋቢት 26/2013 ዓ. ም. የቤተክርስቲያናትን “ቅዱስ በር” በመክፈት የሚያስጀምሩ መሆኑ ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሮሞሎ ቫለስ የሥነ-ሥርዓቱን ትርጉም ሲያስረዱ፣ በፊሊፒን ምድር የመጀመሪያው የቅዱስ ቁርባን ሥነ-ሥርዓት መፈጸሙን ያመለክታል ብለዋል። ለአንድ ዓመት የሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት በሰቡ ከተማ እ. አ. አ ከሚያዝያ 18 – 22/2022 ዓ. ም. በሚካሄደው ሁለተኛው ብሔራዊ የተልዕኮ ቀን ሥነ-ሥርዓት የሚገባደድ መሆኑን አስረድተዋል። በኢዮቤልዩ ዓመት ንግደት እንዲደረግ የወሰኑት የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት መሆናቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሮሞሎ ቫለስ፣ አፈጻጸሙም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ደንቦችን የሚያከብር መሆኑንም አክለው አስታውቀዋል። 

የማኒላ ከተማ ሀገረ ስብከት ምስረታ 442ኛ ዓመት

የማኒላ ከተማ ሀገረ ስብከት የተመሰረተበት 442ኛ ዓመት፣ ቅዳሜ ጥር 29/2013 ዓ. ም. በከተማዋ በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ በደማቅ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መጀመሩ ታውቋል። የመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በቀጥታ የተላለፈ ሲሆን የተመራውም በሀገረ ስብከቱ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ በሆኑት በብጹዕ አቡነ ብሮዴሪክ ፓቢሎ እና ከእርሳቸው ጋርም በፊሊፒን የቅድስት መንበር እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቻርል ብራውን እና የሀገረ ስብከቱ ካህናት መገኘታቸው ታውቋል። በዕለቱ የተፈጸመውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የማኒላ ከተማ ዋና ከንቲባ ፍራንችስኮ ኢስኮ ሞሬኖ ዶማጎሶ እንዲሁም ምክትላቸው ወ/ሮ ቼይላ ሃኒ ላኩና ፓንጋን እና የክፍለ ሀገራቱ መንግሥታዊ ባለ ስልጣናት መካፈላቸው ታውቋል። ምዕመናኑ የመስዋዕተ ቅዳሴውን ሥነ-ሥርዓት የተካፈሉት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል ከካቴድራሉ ውጭ በተዘጋጀው መድረክ ላይ መሆኑ ታውቋል። እሑድ ጥር 30/2013 ዓ. ም. ክብረ በዓሉ በሰበካ ደረጃ በሚገኙ ቁምስናዎች መጀመሩ ታውቋል።

“የወንጌል ተልዕኮ ደንብ”

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሮሞሎ ቫለስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት የማኒላ ከተማ ወደ ሀገረ ስብከት ደረጃ የደረሰው እ. አ. አ በ1595 ዓ. ም. መሆኑን ገልጸው፣ ቀጥሎም በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ሀገረ ስብከቶች መመስረታቸውን አስታውሰዋል። የ65 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሮሞሎ ቫለስ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ምዕመናን ዛሬም ቢሆን ወጌላዊ ተልዕኮአቸውን በማስፋፋት የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት ለሌሎች መመስከር ይገባል ብለዋል። መልዕክታቸውን በመቀጠል የወንጌል ተልዕኮ፣ ምቾት ሰጥቶን ባለንበት ቦታ እንድንቀር የሚያደርገን ሳይሆን የቅዱስ ወንጌል ብርሃንን ወደሚያስፈልጋቸው ዘንድ እንድንወስድ ያስገድደናል ብለዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሮሞሎ ወረርሽኙ በድሆች ላይ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ጠቅሰው፣ በመሆኑም ምዕመናኑ ከወንጌል ምስክርነታቸው ቀጥለው ድሆችን በመርዳት እና አንድነትን በማሳደግ የወንጌል ምስክርነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ አደራ ብለዋል። አዛውንትን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ምዕመናን ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የወንጌል መልካም ዜናን ለሌሎች እንዲያደርሱ አሳስበዋል።

የቦሮጋን ሀገረ ስብከት

በፊሊፒን ቦሮጋን ሀገረ ስብከት የሚገኝ የሳማር አውራጃ የክርስትና እምነት ወደ አካባቢው ለመጀመሪያ ጊዜ የደረሰበትን እና ከዚያም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የተስፋፋበትን መጋቢት 8/2013 ዓ. ም. የሚያስታውስ መሆኑ ሲነገር፣ የሳማራ አውራጃ ሕዝብ ከታዋቂው ፖርቱጋላዊ አገር አጥኚ፣ ከፌርዲናንድ ማጂላንን ጋር ከተገናኙ የፊሊፒን ሕዝቦች መካከል የመጀመሪያዎቹ መሆናቸው ታውቋል። አገር አጥኚው ፌርዲናንድ ማጂላን በፍልሚያ መካከል እ. አ. አ ሚያዝያ 27 ቀን 1521 ዓ. ም. መገደሉ ይታወሳል።                         

09 February 2021, 15:59