የየካቲት 7/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርአዮ 4ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ የየካቲት 7/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርአዮ 4ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ 

የየካቲት 7/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርአዮ 4ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ዕብ 12፡12-21

2.   2ኛጴጥ 1፡19-25

3.   ግ.ሐዋ 7፡29-34

4.   ዮሐ 10፡34-42

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሕጋችሁ፣ ‘እናንት አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ አልተጻፈምን?  የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ‘አማልክት’ ካላቸውና መጻሕፍም ሊሻር የማይቻል ከሆነ፣ ታዲያ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ተሳድበሃል ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ? አባቴ የሚያደርገውን ባላደርግ አትመኑኝ፤ የማደርገው ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ታምራቱን እመኑ።” እንደ ገናም ሊይዙት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አመለጠ።

ከዚያም ኢየሱስ፣ ቀደም ሲል ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደነበረበት፣ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተመለሰ፤ በዚያም ሰነበተ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “ዮሐንስ አንድም ታምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ነገር ግን ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። በዚያም ስፍራ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ (ዮሐ 10፡34-42)

 

 

የእለቱ አስተንትኖ

በቅስና ስለመኖር

በእግዚአብሔር የተወደዳችሁና የተመረጣችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!  

ከሁሉ አስቀድሜ የእግዚአብሔር ፀጋና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን እያልኩ፤ እንደሚታወቀው ያለንበት ወቅት እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር  ዘጥምቀት - አስተርእዮ 4ኛ ሰንበትን እናከብራለን ፡፡ በዚህም ወቅት ምስጢረ ጥምቀትን የምናስብበት ጊዜ ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ቆም ብለን በማጤን  የምንታደስበት፣ የምንለወጥበትና አዲስ ሰው ወይም ፍጡር በሁለንተናችንና በክርስትና አማካይነት የተቀበልነውን ኃላፊነት የምንወጣበት እና የምንለማመድበት ወቅት ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ሲያስተምረን እኛ ክርስቲያኖች ደህንነታችን የተጠበቀ ሆኖ እንዲገኝ ከሁሉ በላይ የቅድስና ኑሮ እንደሚያስፈልገን አበክሮ ይመክረናል። “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ በቅድስናም ለመኖር ትጉ ምክንያቱም ያለቅድስና ማንም እግዚአብሔርን ማየት አይችልም” ዕብ 12፡14 ይለናል።

የአንድ ክርስቲያን የህይወቱ የመጨረሻ ግቡ እግዚአብሔርን ማየት ነው። እግዚአብሔርን ደግሞ በሁለቱ የህይወታችን ጉዞአችን ውስጥ እናገኘዋለን አንደኛው በምድራዊ ጉዞአችን ለሰማያዊ ጉዞአችን ነፀብራቅ ነው። እኛ ክርስትያኖች እንደመሆናችን መጠን የየዕለት ኑሮአችን ጤናማ እና እንደክርስቲያን የተለየ መሆን አለበት፤ ይህም ማለት አካሄዳችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የተቆራኘ እና የተጣበቀ መሆን ይገባዋል። ለእዚህም መመዘኛና ማረጋገጫው የቅድስና ሕይወት ነው።

የቅድስና ሕይወት ማለት እንከን የለሽ ሕይወትን መኖር አልያም ምንም ኃጢአት ሳይሰሩ መኖር ማለት አይደለም። ይልቁንስ በኃጢአት ቀንበር በምንያዝበት ወቅት እና ከቅድስና ሕይወት መስመር በምንስትበት ጊዜ ከኃጢአት ጋር ተጋድሎ የምናደርግበት መሣርያ ነው። ይህንንም ቃል ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መለዕክቱ አበክሮ ይገልጽልናል። “ስለዚህ የእግዚአብሔርን የጦር መሣርያ በሙሉ አንሱ፣ በዚህ ሁኔታ ክፉ ቀን ሲገጥማችሁ የጠላትን ኃይል መቃወምና እስከመጨረሻም ከተዋጋችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁ።” ኤፌ 6፡13   በምድራዊ ሕይወት እስካለን ድረስ ሁላችንም የክርስቶስ ወታደሮች ነን።

ሙሉ ለሙሉ የቅድስና ሕይወታችንን ታጥቀን በተጋድሎ እንኖር ዘንድ ክርስቲያናዊ ኃላፊነት አለብን፤ ይህም ትጥቃችን የእግዚአብሔር ቃል እና ምስጢራት ናቸው። በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ቃል ከከበረው ዕንቁ በላይ ልንከባከበው የሕይወታችን መሳርያ ልናደርገው ይገባል ምክንያቱም ቃሉ ለሕይወታችን ስንቅ ለመንገዳችን ብርሃን ነውና። በኃጢአት በምንወድቅበት ወቅት እንደገና ኃይል የሚሰጠን ከጸጋው ሙላት እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህም ለቅድስና ሕይወታችን ጉዞ ስንቅ ይሆነን ዘንድ በቃሉና በምስጢራቱ በሙላት በመሳተፍ ከሁሉ አብልጠን በልባችን ልንይዘው፣ ልንለማመደው፣ የእራሳችን ልናደርገው እና ዕለት በዕለት መሣርያችን ልናደርገው ይገባል።

“ይህንንም ይሚያረጋግጥልን ይነብያት ቃል አለን፤ ይህን ቃል ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ በወለላ እንደሚበራ መብራት አድርጋችሁ ብትጠብቁት መልካም ነው።” 2ኛጴጥ 1፡14 ካለቅድስና ሕይወት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ እንዲሁም የእርሱን ክብር ማየትም አይቻልም።

በሐዋርያት ሥራ በዛሬው መልዕክት ላይ የምናገኘው “ሙሴ ከእርሱ ወገን የሆነ ዕብራዊ በአንድ ግብጻዊ በመደብደብ አሽዋ ስር ደፍቶ በምድረ በዳላይ ይገድለዋል ከዚያም ከሟቹ ወገኖች ሸሽቶ ወደ ደብረሲና በረሃ በወረደ ጊዜ በሚነደው ቁጥቋጦ ነበልባል ውስጥ የእግዚአብሔር መላዕክ ታየው፤ ሙሴም ባየው ነገር ተገርሞ ወደ እሳቱ ሲጠጋ የቆምክበት ምድር የተቀደሰ ስለሆነ ጫማህን አውልቅ አለው።” የ ሐዋ. ሥ. 7፡3 እውነት ነው ያለቅድስና ሕይወት የእግዚአብሔርን ክብር ማየት አይቻልም፤ ሙሴ ከኃጢአት ይነፃ ዘንድና እስራኤላውያንንም ለእግዚአብሔር በቅድስና ያቀርብ ዘንድ አስቀድሞ እራሱን ለአምላኩ ክብር ቀደሰ፤ በቁጥቋጦ ውስጥም ያናገረው መልአክ ሙሴን ከፊቱ ለሚጠብቀው የቅድስና ሕይወትና ጉዞ ኃይል አስታጠቀው።

የዛሬው የወንጌል መልዕክትም ይህንን ያጠናክርልናል፤ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅድስና እንኖር ዘንድና ፍሬም እንድናፈራ ይጋብዘናል። የእርሱ ዋናው ተልዕኮ እኛን ለቅድስና ሕይወት ማብቃት ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዩሐ 7፡36 – 38  “ታድያ አብ የቀደሰውንና ወደዓለም የላከውን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላለ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ትናገራለህ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆንኩ ግን በእኔ እንኳን ባታምኑ በሥራዬ እመኑ በዚህ ዓይነት አብ በእኔ እንደሆነና እኔም በአብ እንደሆንኩ በሚገባ ታውቃላችሁ።” በማለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለ ተልዕእኮውና ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ኅብረት ይናበራል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እራሱ በብዙ መልኩ በምሳሌ በማስተማርና ምሳሌ በመሆን በሕይወታችን የሚከብደንንና ልንወጣ የማንችለው የሚመስለንን ነገር ያስተምረናል። ይህንንም በእራሱ ሕይወት ሰው ሆኖ እንደሰው እና የሰው ልጅ ሊቋቋመው በማይችለው መንገድ ፈተናን በመቀበልና በመኖር በመራብ፣ በመሰቃየት፣ በምድረበዳ ክብደቱን ለመግለጽ የሚይስቸግር መስቀልን በመሸከም ረጅም መንገድ በመጓዝና በመስቀል ላይ በመሞት ከአብ ጋር በመሆን ሁሉንም ፈተና በድል ተወጥቷል። ይህም ዛሬ ለሁላችንም የሕይወት ምሳሌአችን ነው።

በክርስትና የቅድስና ጉዞአችን ፈተና ሲገጥመን እና ይህንን ማለፍ የተሳነን ሲመስለን ልክ እንደ ክርስቶስ ከ እግዚአብሔር ጋር በመጣበቅ የእርሱን ሕይወት በመመልከት ለኃጢአት እጃችንን ሳንሰጥ ዳግም ከወደቅንበት በመነሣት ወደ ቅድስና የሕይወት መስመር ውስጥ መመለስ ይገባናል።

በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ እንዳለን ሁሉ ዕለት ተዕለት ዲያቢሎስን እየተቃወምነው መንፈሳዊ ጉዞአችንን እንድንቀጥል በቃሉ ይመክረናል በሕይወቱም ምሳሌ ይሆነናል። “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም ውጪ እንድትወስዳቸው አይደለም።” ዮሐ 17፡15  ስለዚህም የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ወደ ፀጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ ከፀጋው ሙላት እንካፈል የሚያበረታን መንፈስ እርሱ ራሱ ይሰጠናል፤ እንዲሁም በቅድስና በመኖር ተጋድሎን እያደረግን ከእርሱ ጋር ደስ የሚያሰኝ ሕይወትን እንኑር።

ይህንንም ለማድረግ በቅድስና ሕይወት በመኖር ምሳሌ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን የሰማነውንም  የእግዚአብሔር ቃል በሕወታችን ለመተርጎም እንድንችል ልባችንን ያነሳሳልን፡፡

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

       

13 February 2021, 09:42