ኢየሱስ ብዙዎችን ፈወሰ ኢየሱስ ብዙዎችን ፈወሰ 

የየካቲት 07/2013 ዓ.ም 5ኛው መደበኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የሰው ልጆችን ሁሉ መቅረብ ነው”

የእለቱ ምንባባት

1.    መጽሐፈ ኢዮብ 7፡1-4.6-7

2.   መዝሙር 146

3.   1ቆሮንጦስ 9፡16-19፣22-23

4.   ማርቆስ 1፡29-39

በእለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል

ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ። የስምዖን አማት በትኵሳት በሽታ ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤ ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኵሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር።

ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፣ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ።

የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር። እርሱም በተለያየ በሽታ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትም አወጣ፤ ነገር ግን አጋንንቱ የኢየሱስን ማንነት ያውቁ ስለ ነበር እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።

ኢየሱስ በገለልተኛ ስፍራ ጸለየ

ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድ፣ ኢየሱስ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራም ሄዶ ይጸልይ ጀመር። 36ስምዖንና ባልደረቦቹም ተከትለው ይፈልጉት ጀመር፤ ባገኙትም ጊዜ፣ “ሰዉ ሁሉ ይፈልግሃል” አሉት። እርሱም፣ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው። ስለዚህ ወደ ምኵራባቸው እየገባ በመስበክና አጋንንትን በማስወጣት በመላዋ ገሊላ ይዘዋወር ጀመር (ማርቆስ 1፡29-39)።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

የእለት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን ዋላችሁ!

የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ (ማርቆስ 1፡29-39) ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት እና ከዚያ በኋላ በዙሪያው የተሰበሰቡትን ሌሎች ብዙ በሽተኞችን እና በአጋንት የተያዙ ሰዎችን እንደ ፈወሰ ይናገራል።  የጴጥሮስ አማት ፈውስ ወንጌላዊ ማርቆስ ያቀረበው የመጀመሪያው አካላዊ ፈውስ ነው - ሴቲየዋ ትኩሳት ይዟት አልጋ ላይ ተኝታ ነበረች፣ ኢየሱስ ለእርሷ ያሳየት አመለካከት እና ለእርሷ ያደረገላት ተግባር አርማ ምልክት ነው “እጇን ይዞ አነሳት” (ማርቆስ 1፡31) ወንጌላዊው ማርቆስ ኢየሱስ የሴቲዬዋን እጅ ይዞ እንዳነሳት ልብ ይላል። ተፈጥሯዊ በሚመስለው በዚህ ቀላል ድርጊት ውስጥ በጣም ርህራሄ አለ “ትኩሳቱ ለቀቃት ፣ እሷም አገለገለችሁ ”። የኢየሱስ የመፈወስ ኃይል ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልገጠመውም ነበር፣ እናም የተፈወሰቺው ሴት ስለ ራሷ ሳይሆን ስለ ሌሎች በማሰብ ወዲያውኑ መደበኛ ሕይወቷን ትቀጥላለች - እናም ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፣ የእውነተኛ “ጤና” ምልክት ነው!

ያ ቀን ሰንበት ነበር። የመንደሩ ሰዎች ፀሓይ እስክትጠልቅ ድረስ ይጠባበቁ ነበር፣ ከዚያም የእረፍት ቀን ግዴታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ (በወቅቱ በነበረው ሕግ መሰረት በእረፍ ቀን ምንም ዓይነት ሥራ መስራት አይፈቀድላቸውም፣ በሽተኞችንም አንኳን ተሸክመው መሄድ አይፈቀድም ነበር) የታመሙትን እና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ፣ እርሱም ይፈውሳቸው ጀመር፣ ነገር ግን አጋንንት እርሱ ክርስቶስ መሆኑን እንዲገልጹ አልፈቀደላቸውም ነበር (ማቅርቆስ 1፡32-34)። ስለዚህ ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢየሱስ በአካልም ሆነ በመንፈስ ለሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ እርሱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እንደ ሆነ ያሳያል፣ እሱ የአባቱ ቅድመ-ምርጫ ነው ፣ የእሱ ሥራ በቃል እና በተግባር የሚገለጽ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ለዚህ የዐይን ምስክሮች ነበሩ። ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ የእርሱ ተልዕኮ ተመልካቾች ብቻ እንዲሆኑ አልፈለገም - እሱ እነሱን አካተታቸው፣ ላካቸው፣ እርሱ ደግሞ ድውያንን እንዲፈውሱ እና አጋንንትን እንዲያወጡ ኃይል ሰጣቸው (ማቴ 10፡1 ፣ ማርቆስ 6፡7)። እናም እስከ ዛሬ ድረስ በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያለማቋረጥ ይህ ቀጥሏል። ሁሉንም ዓይነት በሽተኞችን መንከባከብ ለቤተክርስቲያን “እንደ አማራጭ እንቅስቃሴ” ፣ ተጨማሪ ነገር ፣ አይደለም። እንደ የኢየሱስ ልዑክ የእሷ ተልእኮ ወሳኝ አካል ነው-የእግዚአብሔርን ርህራሄ ለተሰቃዩ የሰው ልጆች ማምጣት የተልዕኮዋ ወሳኝ አካል ነው። ይህንን በጥቂት ቀናት ውስጥ ማለትም እ.አ.አ በየካቲት 11/2021 ዓ.ም በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በተቋቋመው የዓለም የሕሙማን ቀን እንድናስታውስ ያደርገናል።

በወረርሽኙ ሳቢያ በመላው ዓለም እያጋጠመ ያለው እውነታ ይህን መልእክት በተለይ ተገቢ ያደርገዋል። በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ውስጥ የሚያስተጋባው የኢዮብ ድምፅ እንደገና የእኛ ሰብአዊ ሁኔታ ትርጉም የሚሰጥ ነው፣ በክብር ከፍ ያለ እና በተመሳሳይ ጊዜ በጣም ደካማ መሆናችንን ያሳያል። ከዚህ እውነታ አንፃር “ለምን?” የሚለው ጥያቄ ሁል ጊዜ በልብ ውስጥ ይነሳል።

ቃል ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነው ኢየሱስ ይህንን ጥያቄ መልስ የሰጠው በማብራሪያ አይደለም ነገር ግን ከጴጥሮስ አማት ጋር እንዳደረገው ሁሉ እጅን የሚይዝ እና ከፍ የሚያደርግ ፍቅር በመኖሩ ነው (ማርቆስ 1፡31)። የእግዚአብሔር ልጅ ጌትነቱን የሚገለጠው “ከላይ ወደ ታች” አይደለም ፣ ከሩቅ ሳይሆን በቅርብ ፣ በርህራሄ ፣ በፍቅር ነው። እናም የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ምንባብም ይህ ርህራሄ ከአብ ጋር ባለው የጠበቀ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስታውሰናል-በማለዳ እና ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ለብቻው ለመጸለይ ሄደ (ማርቆስ 1፡35)። ከዚያ ሥፋር ተልእኮውን ለመወጣት፣ ለመስበክ እና ፈውሶችን ለማከናወን የሚያስችለውን ጥንካሬን አገኘ።

ቅድስት ድንግል ማርያም በኢየሱስ እንድንፈወስ ዘንድ ራሳችንን ወደ እርሱ እንድናቀርብ ትርዳን፣ ስለዚህ እኛ በተራችን የእግዚአብሔርን የፈውስ ርህራሄ ምስክሮች እንሆን ዘንድ በቅድሚያ እኛ ሁልጊዜ ፈውስ ያስፈልገናል።

ምንጭ፡ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በጥር 30/2013 ዓ.ም ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

13 February 2021, 10:36