ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገቡ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገቡ 

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገቡ

በብርሃኔ ሦስት ጊዜ አይበታለሁ እኔ ሳልፍ ሁሉቱ የዓይን ብሌኖቼ ተነስተው የሁለት ወገኖቼን ብርሃን እንዲመልሱ በበጎ ፈቃደኝነት ቃል ገብቻለሁ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የካቲት 11/2013 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ በመገኘት ከዚህ ዓለም በሚያልፉበት ጊዜ የዓይን ብሌኖቻቸው ተነስተው ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻቸው እንዲሰጡ ቃል ገብተዋል።

ብፁዕነታቸው ይህንን በጎ ተግባር ለመፈጸም የተነሳሱት ይህን መሰሉ ተግባር ታላቅ የፍቅር ሥራ መሆኑን ሰለሚያምኑ እንደሆነ ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው በልገሳ ቃልኪዳን ሥነ ሥርአቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ብርሃንን ለሌሎች የማስተላለፍን ተግባር ካቶሊካውያን፣ ክርስቲያኖች በሙሉ እንዲሁም ወንድም እና እህት ሙስሊም ወንድሞቻችን በሙሉ ሊከተሉት የሚገባ ታላቅ የፍቅር ስጦታ መሆኑን ገልጸዋል። ብርሃን ለሰው ልጆች ታላቅ ስጦታ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ በርካታ ዜጎች በቀላል ህክምና ሊድን በሚችል የዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት በጨለማ ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የእነዚህን ወገኖቻቸውን ብርሃን ለመመለስ የዛሬውን የዓይን ብሌን የመለገስ ቃልኪዳን በከፍተኛ ደስታ የሚፈጽሙት መሆኑን ተናግረዋል። አያይዘውም ከእርሳቸው አስቀድሞ ይህንኑ ተግባር በመፈጸም አርዓያ ለሆኑ ዜጎቻችን እና ቃላቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ትብብር ላደረጉ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

ወ/ሮ ለምለም አየለ የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ዳይሬክተር  በበኩላቸው ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ይህንን በጎ ተግባር ለመፈጸም በአካል ጽ/ቤታቸው ድረስ በመምጣታቸው ታላቅ ኩራት የሚሰማቸው መሆኑን በመግለጽ ይህ ተግባራቸው ለበርካቶች አብነት እንደሚሆን ከፍተኛ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። ለዚህ ታላቅ ተግባር መታሰቢያ እንዲሆንም የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ብፁዕነታቸውን የበጎ ምግባር አምባሳደር ሆነው የተሰየሙ መሆኑን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት በክብርት ዳይሬክተሯ ተበርክቶላቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በዓይን ብሌናቸው ላይ በሚገገኝ ጠባሳ ምክንያት ማየት የተሳናቸው ሦስት መቶ ሺ ዜጎች ያሉ ሲሆን እስካሁን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሰዎች አስር ሺህ የደረሱ መሆኑ ታውቋል። በተሳካ ህክምና የዓይን ብሌን ተቀይሮላቸው ማየት የቻሉ 2523 ዜጎች መኖራቸው በሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ብቸኛው ሲሆን በአፍሪካም ለአብነት የሚጠቀስ አገልግሎቶችን እያከናወነ ይገኛል።

Photogallery

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገቡ
19 February 2021, 12:07