የግራንድቻምፕ መነኮሳት ለክርስቲያኖች አንድነት በሚያደርጉት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የግራንድቻምፕ መነኮሳት ለክርስቲያኖች አንድነት በሚያደርጉት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት  

ለክርስቲያኖች አንድነት የሚሆን የጸሎት ሳምንት መጀመሩ ተገለጸ

ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያናዊ ማኅበራት ለአንድነት እንዲጸልዩ በቀረበው ጥሪ መሠረት፣ በስዊዘርላንድ የሚገኙ መነኮሳት በዚህ ሳምንት ውስጥ ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎታቸውን የሚያቀርቡ መሆኑ ታውቋል። እነዚህ መነኮሳት በኮቪድ-19 ምክንያት የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በፌስቡክ ገጾች በኩል የሚያካሂዱ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዘንድሮ ለክርስቲያኖች አንድነት በሚደረግ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ተከታዮች እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ለአንድ ሳምንት የሚካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ፥ “አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ (ዮሐ. 17:21) ያለውን ጸሎት በማስታወስ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የዘንድሮ የጸሎት ሳምንት መሪ ጥቅስ ከዮሐ. 15:5-9 የተወሰደው “በፍቅሬ ኑሩ፤ ብዙ ፍሬም ታፈራላችሁ” የሚል መሆኑ ታውቋል። ይህን የጸሎት ሳምንት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እንደ አመቺነቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚያከብሩት ሲሆን በዋናነት ከጥር 10-17 የሚካሄድ ሲሆን፣ እንደ ሌሎች ዓመታት ዘንድሮም በሮም በሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ ጥር 17/2013 ዓ. ም. የሚካሄደውን የመዝጊያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር በመገኘት የሚነሩት መሆኑ ታውቋል።

የክርስቲያኖች ውህደት እንቅስቃሴ አጀማመር

ከሰሜን አሜሪካ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ጋር ግንኙነት የነበረው የስኮትላንድ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፣ ክርስቲያናው እምነትን ለማደስ በሚል ዓላማ ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስተባብር መልዕክት ማስተላለፉ ሲታወስ ይህም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ወደ 1740 ዓ. ም. ገደማ መሆኑ ይነገራል። በዚያን ወቅት ዮናታን ኤድዋርድ የተባሉ ወንጌላዊ፣ አብያተ ክርስቲያናትን ለጋራ የወንጌል ተልዕኮ የሚያነሳሳ፣ አንድ ቀን የሚወስድ የጸሎት እና የጾም ሥነ-ሥርዓት ማስተባበራቸው ይታወሳል። በኋላም የቁንስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቀዱስ ኢያቄም 3ኛ ለክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ጸሎት እንዲደረግ የሚጋብዝ ሐዋርያዊ መልዕክት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1902 ዓ. ም. መላካቸው ይታወሳል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1908 ዓ. ም. ክቡር ፖል ዋትሰን የተባሉ ወንጌላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ግሬይሙር በተባለ ቦታ በዘላቂነት የሚካሄድ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከጥር 10-17 እንዲሆን ማስጀመራቸው ይታወሳል።

ወሳኝ ሰነዶች

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1964 ዓ. ም. ከፓትሪያርክ አትናጎራስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኝተው “ሁሉም አንድ እንዲሆኑ” (ዮሐ. 17:21) በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ያቀረበውን ጸሎት በጋራ ማቅረባቸው ይታወሳል። ወቅቱ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ “Unitatis Redintegratio” ወይም “የጋራ ስምምነት” በሚለው ሰነዱ፣ ጸሎት ለክርስቲያኖች ውህደት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የጸሎት ሳምንት እንዲዘጋጅ ያሳሰበበት ወቅት መሆኑ ይታወሳል። የክርስቲያኖችን ውህደት በተመለከተ መጪው ሚያዝያ ወር መላው የአውሮፓ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመካከላቸው ያለውን ኅብረት ለማሳደግ የጋራ ስምምነት ያደረጉበት 20ኛ ዓመት መታሰቢያ ወቅት መሆኑ ታውቋል።

የጸሎት ሳምንታት ጠቀሜታዎች

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1968 ዓ. ም. ጀምሮ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ምክር ቤት እና በጳጳሳዊ ምክር ቤት የክርስቲያኖች አንድነት ማስፋፊያ ምክር ቤት በጋራ ጸሎት የክርስቲያኖችን አንድነት የሚያሳድግ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1975 ዓ. ም. ጀምሮ የክርስቲያኖችን ውህደት የሚያጠናክሩ ጽሑፎች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልዕክቶች እና አስተያየቶች ለጸሎት ሳምንት እንዲሆን በየዓመቱ ተዘጋጅቶ በእያንዳንዱ አገር እንዲቀርብ ተደርጓል። በዚህም መሠረት እነዚህ መንፈሳዊ ሃሳቦች እና ጸሎቶች የእያንዳንዱን ቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓትን እና ባሕልን በሚያከብር መልኩ የክርስቲያኖችን ውህደት ለማበረታታት ጥረት ተደርጓል። በእርግጥ በአንዳንድ ቦታዎች ይህንን ሀሳብ እውን ለማድረግ የሚያስችሉት ቀድሞውንም ቢሆን ሥርዓታዊ መዋቅሮች መኖራቸው ተስተውሏል።

የ2021 ዓ. ም. የጸሎት ሳምንት መርሃ ግብር

ዘንድሮ ከጥር 10-17 2013 ዓ. ም. ድረስ ባሉት ስምንት ቀናት ውስጥ ምዕመናን ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል በተመረጡ የተለያዩ ጥቅሶች ላይ እንዲያስተነትኑ ተጋብዘዋል። በመጀመሪያው ቀን በእግዚአብሔር መጠራታችንን በማሰብ “እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም” (ዮሐ. 15:16)፤ በሁለተኛው ቀን ውስጣዊ ዕድገትን በማሳየት “በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ” (ዮሐ. 15:4)፤ በሦስተኛው ቀን አንድ አካል በመሆን “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ” (ዮሐ. 15:12)፤ በአራተኛው ቀን በጋራ መጸለይን በማሰብ “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ” (ዮሐ. 15:15)፤ በአምስተኛው ቀን ራስን በቃሉ መለወጥን በማሰብ “እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ” (ዮሐ. 15:3)፤ በስድስተኛው ቀን በእንግድነት መቀባበልን በማሰብ “ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ” (ዮሐ. 15:16)፤ በሰባተኛው ቀን ኅብረትን ማሳደግ በተመለከተ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ” (ዮሐ. 15:5)፤ በስምንተኛው የማጠቃለያ ቀን ከፍጥረታት ጋር መታረቅን በማሰብ “ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሐ. 15:11)።

ያለ መከራ ወዳጅነት የለም

ለክርስቲያኖች አንድነት የሚደረግ የጸሎት ሳምንት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይኖሩታል። የመጀመሪያው ክፍል የተመሰረተው በእያንዳንዱ ግለሰብ የውስጥ አንድነትን እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መኖርን ይመለከታል። ሁለተኛው ክፍል በክርስቲያኖች መካከል ያለውን የሚታይ አንድነት ለማወቅ ፍላጎት ማሳደርን ይመለከታል። ሦስተውኛው ክፍል በሰዎች እና በፍጠረታት መካከል ያለውን አንድነት ለማወቅ ራስን ነጻ ማድረግን ይመለከታል። የተለያዩ ባህሎች እና ልማዶች መሠረት አንዳንድ ተጓዳኝ ምልክቶች በተለያዩ መንገዶች ሊከናወኑ የሚችሉ ናቸው። “ከሌሎች ሰዎች ጋር መቀራረብ ፣ በህብረት አብሮ መኖር ፣ አንዳንድ ጊዜ ከእኛ ባሕል በጣም የተለየ እና ፈታኝ ሊሆን ይችላል” በማለት በፈረንሳይ የቴዜ ክርስቲያን ማኅበረሰብ መሪ የሆኑት ወንድም ሮጄር ገልጻን መነኮሳት በጽሑፋቸው ይጠቅሳሉ። ወንድም ሮጄር በዚህ ገልጻቸው በማከል “ያለ መከራ ወዳጅነትን መመስረት አይቻልም፣ ያለ መስቀል ፍቅርን መግለጽ እንደማይቻል እና መስቀል ብቻ የማይመረመረውን ጥልቀት ፍቅር እንድናውቅ ያስችለናል” ብለዋል።  

አንድነትን የሚገልጹ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክቶች

ለአቅመ ደካሞች መጨነቅ፣ ማኅበራዊ አንድነትን ማሳደግ፣ ድሆችን እና መከራ የደረሰባቸውን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 እና 2020 ዓ. ም. ለክርስቲያኖች አንድነት በተካሄዱ የጸሎት ሳምንት መልዕክታቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። በተለይም ከአንድ ዓመት በፊት በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በጀልባ ተጉዞ ወደ ማልታ በደረሰ ጊዜ ጀልባው ለቀናት ያህል በአውሎ ነፋስ ክፉኛ መመታቱን እና በዚህም የተነሳ ከእርሱ ጋር የነበሩት ብዙዎች ተስፋ በቆረጡ ጊዜ እርሱም እስረኛ እንደነበር እና ከአቅመ ደካሞች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግሮር ማጽናናቱን መግለጻቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ይህን የገለጹት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለማችንን ማስጨነቅ በጀመረበት፣ ምዕመናን ባልተገኙበት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ በመጋቢት ወር 2012 ዓ. ም. ባቀረቡት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደነበር ይታወሳል። ዛሬም ቢሆን አንድነት የግድ አስፈላጊ፣ የምንናፍቀው እና አስቸኳይ ተስፋ በመሆኑ በጋራ ለአንድነት መጸለይ አሁንም በጣም አስፈላጊ ነው።      

18 January 2021, 16:02