ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ 

ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ

የአዳም ልጆች በሙሉ እንዲመጣላቸው በናፍቆት ይጠብቁት የነበረ መሲሕ በተወሰነ ጊዜ መጣ፡፡ በዚህ ሁኔታ የነቢያት ትንቢት ተፈጸመ፣ ሐቅነቱ በግዙፍ በዓይን ታየ፡፡ እግዚአበሔር ለአባታችን አዳም “መድሃኒት እልክልሃለሁ”  እያለ አስቀድሞ ሰጥቶት የነበረው ተስፋ ቃል ዛሬ ተግባራዊ ሆኖ በዓይን ምስክር ታይቶአል፡፡ ጊዜው ከደረሰ በኋላ እግዚአብሔር እነዚያ በኦሪት ሕግ ሥር የነበሩትን ሊያድን ልጆቹም እንዲሆኑ መብት እንዲሰጣቸው ከሴት የሚወለድ በሕግም የሚሄድ ልጁን ላከ፡፡ የመድኃኒታችንና የአምላካችን ደግነትና ሰውነት በይፋ ተገለጠ፡፡ ባደረግነው የጽድቅ ፍሬ ሳይሆን በምሕረቱ አዳነን አምላክ እኛን ለመምሰል እንደ እኛ ምስኪን ድኻ ሰው ሆነ፡፡

ትልቁ ንጉሥ እስክንድር የፋርስን ሀገር ከያዘ ሳይዘገይ በኢየሩሳሌም ሕዝብ ፊት ተወዳጅነትን እንዲያገኝ በሁሉም እንዲወደድና እንዲታመን በወረራ ኃይል የያዘውን የአገር ልብስ ለበሰ፡፡ ሁሉም ነገር እንደጠበቀውና እንዳሰበው ሆነለት፡፡ ከጠበቀው በላይ ተሳካለት፡፡ በዛሬው ቀን ክርስቶስ አምላካችንም እኛን በማዳን ተከታዮቹና ወዳጆቹ ሊያደርገን ሥጋችንን ለብሶ እኛንም መስሎ በመካከላችን መጣ፡፡ “ቃል ሥጋ ኮነ ወኃደረ ላዕሌነ - ቃል ሥጋ ሆነ በአኛም አደረ" ይላል ቅዱስ ዮሐንስ፡፡ አምላክ የሁሉ ሥነ-ፍጥረት ፈጣሪ ራሱ ሥጋችንን ለብሶ ምስኪን ፍጡር መሰለ፡፡ መለኮታዊ ማዕረጉን ትቶ ትልቅነቱን ንቆ ዝቅተኛና ደካማ ባሕርያችንን ተሸከመ የራሱ አደረገው፡፡ በዚህ ጭንቅ የተሞላበት ከባድ ኑሮአችን ከኃጢአት በስተቀር ልክ እንደ እኛ እንደ አንዱ ሆኖ ለመኖር ስለ ደኀነታችን ፍቅር ከሰማይ ወደ ጊዜያዊ መኖሪያችን ወደ ምድር ወረደ፡፡  1. ዮሐ. 1፣14

“ኦ! ፍቅር ዘመጠነዝ ፍቅር ኦ! ትሕትና ዘመጠነዝ ትሕትና ፍቅር ስሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት እስከዚህ የሚደርስ ፍቅር እስከዚህ የሚደርስ ትሕትና" እያለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይናገራል፡፡

ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ ከእርሱ ጋር በነበረው በአምላክ አንድ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፡፡ በእውነት ብርሃን ከብርሃን እውነተኛ አምላክ ከእውነተኛ አምላክ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ አይደለም፡፡ መለኮታዊነቱ ከአብ ጋር እኩል ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለእርሱ ምንም የሌለ ስለ ደኀነታችን ከሰማይ ወደ በመንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ" ይህ ማን ነው። 

ይህ በፊታችን ያለው ትናንት የተወለደው ሰማያዊ ሕፃን ነው፡፡ ፈጣሪ ሆኖ ሳለ እኛን ሊያጽናናንና የድኀነትን ብርሃን ሊሰጠን ሕፃን  ሆኖ ወደ እኛ መጣ፡፡ አዳም በልጆቹ አማካይነት ይህን መሢሕ በስንት ምኞትና ናፍቆት ጠበቀው፡፡ ቶሎ መጥቶ ከመጥፎ ኑሮው እንዲያድነውም በመሉ ልቡ ቀተማጠነው፡፡ ቀንም ሌሊትም ለመነው፡፡ ይኸው ዛሬ ምኞቱን ሊያሟላለት የድኀንነት ብርሃን ሊያበራለት መሢሕ ወደ እርሱ ቀረበ፡፡ “ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ፡፡ እኛን ፈልጐ ከላይ ወደ ታች ወረደ፡፡ “ደስታዬ ከሰው ልጆች ጋር መሆን ነው" እያለ ከእኛ ጋር ሊቀመጥ ፈለገ፡፡ ከእኛ ጋር በመሆን ሊጠብቀን፣ በሚያስፈለገን ሁሉ ሊረዳን፣ ከጠላት ሊታደገን የምድራዊ የሰው ልጅ መልክ ለብሶ መጣ፡፡ በጸጋዎቹ ሀብታሞች ሊያደረገን የእግዚብሔርን መንገድ ሊመራን ወስኖ ከእኛ ጋር ለመኖር መጣ፡፡

“ወልድ ሰው ሆነ በመካከላችንም ደግሞ ተቀመጠ፡፡ ልዑል አምላክ ስለፍቅራችን እኛን መሰለ" በፍቅሩና በትሕትናው እያመሰገንነው በክፋታችን ከእኛ እንዲርቅ እንዳናደርገው እንጠንቀቅ፡፡ ልባችን ከልቡ ፈቃዳችን ከፈቃዱ እንድናደርገው ቃሉን እንስማ በሁሉ እርሱን እንፈልግ ኑሮአችን ከእርሱ ጋር ይሁን፡፡

08 January 2021, 12:55