መንበረ ታቦት ኢየሱስ ሁሌም በመካከላችን እንደ ሚገኝ ያሳስበናል! መንበረ ታቦት ኢየሱስ ሁሌም በመካከላችን እንደ ሚገኝ ያሳስበናል!  

መንበረ ታቦት ኢየሱስ ሁሌም በመካከላችን እንደ ሚገኝ ያሳስበናል!

መንበረ ታቦት ኢየሱስ ሁሌም በመካከላችን እንደ ሚገኝ ያሳስበናል!

በቤተክርስቲያናችን ውስጥ በመንበረ ታቦትና በቅዱስ ቁርባን አጠገብ የሚያበራ መብራት ኢየሱስ ሁሌም በመካከላችን እንዳለ ያሳስቡናል።ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ በምንገባበት ጊዜ የቅዱስ ቁርባን ማስቀመጫዉን ከመንበረ ታቦት ቅርብ ወይም በጎን ባለዉ ክፍል እናገኛለን፡፡ በጎኑ ደግሞ ቀን ከሌሊት የሚበራ (በተለምዶ ቀይ) መብራት እናያለን። ይህን የቅዱስ ቁርባን መብራት ብለን እንጠራዋለን፡፡ ለመሆኑ የቅዱስ ቁርባን ማስቀመጫ (ታበረናክል) ምንድነዉ? ቀዩ ብርሃንስ ለምን ቀን ከሌሊት ይበራል?

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በሙሴ ዘመን ʺታበርናክል" የእስራኤል ህዝብ አምላካቸዉን የሚገናኙበት መገናኛ ድንኳን ሲሆን፣ ታበርናክል ማለት ድንኳን ማለት ነወ፡፡ በካቶሊክ ቤተክርስቲያናችን “ታበርናክል” ያንን ሙሴ በረዥሙ የበረሃ ጉዞ ወቅት ሕዝቡ ከአምላካቸዉ ጋር ይገናኙ ዘንድ የተከለዉን ድንኳን የሚያሳስብ ነዉ፡፡ በዚያ ስፍራ ሰዎች እግዚአብሔርን ይገናኙት ነበር፡፡፣ በማንኛዉም ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን ማማከር የፈለገ ሰዉ ወደዚህ የመገናኛ ድንኳን ይሄዳል፡፡ (ዘጸ. 33፡7-11)

ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት በሚያነጋግርበት ጊዜ የደመና አምድ በሩን ይሸፍናል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዉ ሁሉ እግዚአብሔር እንዳለ (ሙሴን እያነጋገረዉ እንደሆነ) ይረዳል፡፡

ዛሬ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን መገናኛ ድንኳናችን ይህ ቅዱስ ቁርባን የምናስቀምጥበት "መንበረ-ቁርባን" ወይም  “ታበርናክል” ነዉ።

ቅዱስ ቁርባን በመንበረ-ቁርባን (ታበርናክል) ዉስጥ ይቀመጣል

ካህኑ በመሥዋዕተ ቅዳሴ የተባረከዉን ቅዱስ ቁርባን ለምዕመናኑ ሲሰጥ “የክርስቶስ ሥጋ” እያለ ይሰጣል፣ ምዕመናኑ ደግሞ “አሜን” በማለት ይመልሱለታል፣ ይህም ማለት “አዎ! ይህ የተቀደሰ ዳቦ በእዉነት የክርስቶስ ሥጋ መሆኑን አምናለሁ” ማለት ነዉ፡፡

ምዕመናኑ ሁሉ ከቆረቡ በኀላ የቀረዉን የተባረከ ኅብስት (የክርስቶስ ሥጋ) ካህኑ ወሰዶ በመንበረ ታቦት አጠገብ በሚገኘዉ መንበረ-ቁርባን (ታበርናክል) ዉስጥ ያስቀምጠዋል እንጂ ወደ ሳክርስቲ ይዞ ሄዶ በቁምሳጥን ዉስጥ በፍጹም አያስቀምጠዉም፡፡ ካህኑ ይህን የቀረዉን የተባረከ ኅብስት በቆንጆ “ታበርናክል” ዉስጥ የሚያሰቀምጠዉ ይህ ተራ ዳቦ ሳይሆን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ ስለሆነ ነዉ፣ በመንበረ ታቦት በመሥዋዕተ ቅዳሴ ጊዜ  ይህ ኅብስት ወደ ክርስቶስ ሥጋነት የተለወጠው ካህኑን በወከለዉ በክርስቶስ ራሱ ነዉ፡፡

ይህ ኅብስት ወደ ክርስቶስ ሥጋነት የሚለወጠዉ አንድ የእግዚአብሔር ካህን በመንበረ ታቦት ላይ በሚያሳርገዉ መስዋዕተ ቅዳሴ ነዉ፣ ከመጀመሪያዉ ይህ የተቀደሰ ኅብስት “በታበርናክል” የማስቀመጡ ልምድ የመጣዉ በጊዜዉ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሊገኙ ያልቻሉ ሰዎች ለምሳሌ በሽተኞችና አካል ጉዳተኞች ባሉበት ቦታ ሆነዉ የተባረከዉን የክርስቶስ ሥጋ በቤታቸዉ በመቀበል በቅዳሴዉ እንዲሳተፉ ለማድረግ ነዉ።

በካቶሊክ ቤተክርስቲያናችን ዉስጥ የሚገኘዉ መንበረ-ቁርባን (ታበርናክል) የሕያዉ እግዚአብሔርን ልጅ ክርስቶስን የምንገናኝበትና ከሱም ጋር የምንደሰትበት መገናኛ ድንኳናችን ነዉ፣ ይህ በ“ታበርናክል” ዉስጥ ያለዉ ቅዱስ ቁርባን ክርስቶስ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ከእኛ መካከል ስለ መኖሩ የሚታይና ተጨባጭ ምልክት ነዉ፣ ቅዱስ ቁርባን በቤተክርስቲያናችን ካሉ ድንቅ ስጦታዎች (treasures) ሁሉ ትልቁ ሀብታችን ነዉ፡፡

በዚህ ምክንያት በቀን ዉስጥ ወደ ቤተክርስቲያን እየሄዱ በቅዱስ ቁርባን ፊት በመንበርከክ ከክርስቶስ ጋር መገናኘት፤መወያየት፤መናገር፤ መጸለይ እሱን ማመስገን፤መወደስ፤ “እነሆኝ ጌታየ! በፊትህ ቆምያለሁና ምራኝ” ማለት ከካቶሊካዊ ልምዳችን አንዱ ነዉ፡፡

በመንበረ ታቦት አጠገብ የሚበራዉ መብራት ቅዱስ ቁርባን “በመንበረ-ቁርባን” (በታበርናክል) ዉስጥ መኖሩን ያስታዉሰናል። ይህን ብርሃን ስናይ እኛ ካቶሊኮች ክርስቶስ “በታበርናክል” ዉስጥ በተቀደሰ ዳቦ መልክ እንደሚገኝ እናዉቃለን። ስለዚህ በጉልበታችን ዝቅ ብለን ሰግደን በጽሞና “ጌታዬ ሆይ አንተን ሰላም እላለሁ፤ ላንተ እሰግዳለሁ፤ጌታዬና አምላኬ” እያልን እንጸልያለን፡፡

በጉልበታችን ዝቅ ብለን በመስገዳችን ``በታበርናክል`` ዉስጥ ያለዉን ክርስቶስን እናመልካለን፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፊት ራሳችን ዝቅ በማድረግ የእኛን ትንሽነት እንቀበላለን፤ እግዚአብሔር ራሱ እናት ልጁዋን ከመሬት እንደምታነሳ እንዲያነሳን፤ ከፍ እንዲያደርገን እንለምናለን፡፡

ለበሽተኞች የሚሄደዉ ቅዱስ ቁርባን ከመንበረ-ቁርባን (ከታበርናክል) ዉስጥ ተወስዶ ነዉ

አንድ ካቶሊክ ምዕመን ታሞ በቤቱ ወይም በሆስፒታል ከተኛ ቅዱስ ቁርባን እንዲመጣለት ይጠይቃል፣ ካህን ወይም ዲያቆን ቅዱስ ቁርባንን ``ከታበርናክል`` ውስጥ ወስዶ በትልቅ አክብሮት ወደ በሽተኛዉ ይዞ ይሄዳል፣ በዚህ ዓይነት ቅዱስ ቁርባንን በመዉሰድ በሽተኛዉ በቤት ወይም በሆስፒታል ሆኖ በመሥዋዕተ ቅዳሴ ይሳተፋል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰዉ ለእኛ ለካቶሊኮች መንበረ-ቁርባን (ታበርናክል) ጌታችን ኢየሱስን በቅዱስ ቁርባን የምንገናኝበት መገናኛ ድንኳናችን ነዉ፣ የመንበረ ታቦት መብራት ደግሞ የመገናኛ ድንኳኑን ደጃፍ በመሸፈን ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር እየተናገረ እንደሆነ በሚያመለክተዉ የደመና አምድ አምሳል አሁንም እግዚአብሔር አጠገባችን እንደሆነ፤በቅርባችን እንዳለ፤ ከእኛ ጋር እንደሚራመድ፤ በመካከላችን እንዳለና እንደሚወደን የሚያሳይ ምልክት ነዉ፡፡

ምንጭ፡ የካቶሊካዊ እምነታችን ማንነትና ምንነት! ካቶሊካዊ ደስታ። በክቡር አባ አበራ ማኬቦ ዘማህበረ ካፑቺን የተዘጋጀ

28 January 2021, 10:25