በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ፣ ቃሲር ኣል ያሁድ የተባለ አካባቢ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ፣ ቃሲር ኣል ያሁድ የተባለ አካባቢ 

ከ54 ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ቦታ የጥምቀት በዓል እንዲከበር ተወሰነ

በቅድስት አገር የሚገኙ ፍራንችስካዊያን ወንድሞች ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀበት፣ ቃሲር ኣል ያሁድ በተባለ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ እሑድ ጥር 2/2013 ዓ. ም. የጥምቀት ክብረ በዓልን እንደሚያከብሩ ታውቋል። ሥፍራው በእስራኤል አገር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1967 ዓ. ም. ከተደረገው ጦርነት በኋላ በፈንጂ ታጥሮ የቆየ ሲሆን አሁን በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ የጸሎት ሥፍራ እንዲሆን መወሰኑ ታውቋል። በውሳኔው የተደሰቱት ፍራንችስካዊ ካህን ክቡር አባ ኢብራሂም ፋልታስ ዕለቱ መልካም ዜና የተሰማበት ታሪካዊ ዕለት ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሥፍራው የሚገኘው ወደ ኢያሪኮ መግቢያ ምስራቃዊ ዳርቻ ላይ ሲሆን፣ ይህ ሥፍራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ መሆኑ ታውቋል። በቅድስት አገር የሚኖሩ ፍራንችስካዊያን ወንድሞች እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1641 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ቦታው መንፈሳዊ ጉዞን ሲያደርጉ መቆየታቸው ታውቋል። ነገር ግን ከ1967 ዓ. ም. ጀምሮ በጦርነት ምክንያት ለመንፈሳዊ ጉዞም ሆነ ለሀገር ጎብኝዎች ተከልክሎ መቆየቱ ሲነገር፣ በኋላም በፈንጅ ከታጠረ በኋላ ወታደራዊ ክልል ሆኖ መቆየቱ ታውቋል።

ፈንጂ የማምከን ሥራ

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 2000 ዓ. ም. ወደ ቅድስት አገር ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ጥባብ ቦታ ብቻ ክፍት እንዲሆን ቢደረግም እንደገና መዘጋቱ ታውቋል። ባለፉት ዓመታት ጠቅላላ የቃሲር አል ያሁድ አካባቢዎችን ከፈንጂ ነጻ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል። በእስራኤል እና ፍልስጤም ባለስልጣናት ፈቃድ መሠረት በሥፍራው የተሰማራው “ሃሎ ትረስት” የተሰኘ የእንግሊዝ ባለሞያ ድርጅት ቢያንስ 4000 ፈንጂዎችን ማምከኑ ታውቋል።

ፈንጂ የማምከን ሥራ
ፈንጂ የማምከን ሥራ

የጥምቀት ክብረ በዓል

እሑድ ጥር 2/2013 ዓ. ም. የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት ክብረ በዓል የሚከበር ሲሆን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከቅድስት አገር የሚመጡ ጥቂት ምዕመናን የሚካፈሉ መሆኑ ታውቋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ሥፍራው መንፈሳዊ ጉዞን የሚያደርግ የምዕመናን ቁጥር ዝቅተኛ እንደሚሆን ሲነገር በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ መንፈሳዊ ኡደት እና የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ጥምቀት የሚገልጽ የቅዱስ ወንጌል ንባብ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል።

ቃሲር ኣል ያሁድ የተባለ ሥፍራ
ቃሲር ኣል ያሁድ የተባለ ሥፍራ

ታሪካዊ ዕለት ነው

በቅድስት አገር የሚኖሩ ፍራንችስካዊያን ወንድሞች ከ54 ዓመታት በኋላ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በተጠመቀበት፣ ቃሲር ኣል ያሁድ በተባለ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ተገኝተው የብርሃነ ጥምቀት በዓልን የሚያከብሩ መሆኑ ታውቋል። ክቡር አባ ኢብራሂም ፋልታስ ዕለቱ ለፍራንችስካዊያን ታሪካዊ ዕለት እንደሆነ ገልጸው፣ በጦርነት ምክንያት ወደ ሥፍራው መጓዝ ባይቻልም ፍራንችስካዊያን ወንድሞች ይህን ቅዱስ ሥፍራ ዘወትር ሲያስታውሱት መኖራቸዋን አባ ኢብራሂም ገልጸዋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1920 ዓ. ም. በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ መሬት ገዝተው በቅዱስ ዮሐንስ ስም የሚጠራ ገዳም ማነጻቸውን የገለጹት ክቡር አባ ኢብራሂም፣ በኋላ በ1967 ዓ. ም. በአካባቢው በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ገዳማቸውን ማጣታቸውን ገልጸው ከ54 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለማሳረግ መዘጋጀታቸወን አስረድተዋል። በዕለቱ የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓትን የሚመሩት፣ በቅድስት አገር የሚኖሩ የፍራንችስካዊያን ወንድሞች ማኅበር አለቃ፣ ክቡር አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን መሆናቸውን እና በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ በኢየሩሳሌም የቅድስት መንበር እንደራሴ እና የጣሊያን፣ የስፔን፣ የቤልጄም እና የፈረንሳይ ቆንሲላ ተወካዮች፣ እንዲሁም ፍራንችስካዊያን ወንድሞችን ጨምሮ ከ50 የማይበልጡ ምዕመናን የሚገኙ መሆኑን ክቡር አባ ኢብራሂም ፋልታስ አስታውቀዋል።

የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ
የዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ

“ይህ አዲስ ዓመት እንደገና የምንወለድበት ነው፣ የምስጢረ ጥምቀት ዋና ትርጉምም ይህ ነው” ያሉት ክቡር አባ ኢብራሂም ፋልታስ፣ በቅድስት አገር የሚገኙ ፍራንችስካዊያን ወንድሞች የተሰማቸው ደስታ መጠን የለውም ብለዋል። እሑድ ጥር 2/2013 ዓ. ም. በሚካሄደው በዓል ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተጠመቀበት የዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ኡደት እንደሚደርግ እና በመጨረሻም የቡራኬ ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድ መሆኑን ክቡር አባ ኢብራሂም ፋልታስ አስታውቀዋል።

በቅድስት አገር፣ የቃሲር ኣል ያሁድ መንደር
በቅድስት አገር፣ የቃሲር ኣል ያሁድ መንደር

የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ተስፋን እንዳይቆርጡ የሚያበረታታ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ኢብራሂም ፋልታስ፣ ሥፍራውን መልሰን እንድምናገኝ ማንም ባያስብም ነገር ግን ሁል ጊዜ ተስፋን ሲያደርጉ ለረጅም ዓመታት መቆየታቸውን ገልጸው፣ አንድ ቀን በቅድስት አገር ሰላም እንደሚወርድ በማመን፣ በእምነታቸው ጠንካራ ከሆኑት ከቅድስት አገር ምዕመናን ጋር በርትተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ክቡር አባ ኢብራሂም ፋልታስ በመጨረሻም ቀዳሚ ምኞታቸው በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ሰላም ወርዶ ማየትን እንደሆነ ገልጸው፣ ሌሎች የተቀሩት መንፈሳዊ ሥፍራዎችም ለማኅበራቸው እንደሚመለሱላቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

09 January 2021, 17:10