ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዚያስቶስላቭ ሼቭቹክን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት፤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዚያስቶስላቭ ሼቭቹክን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት፤ 

ሊቀ ጳጳስ ሼቭቹክ፣ “የብርሃነ ልደቱ ተስፋችን ከእኛ ጋር ያለው እግዚአብሔር ነው” በማለት አስገነዘቡ።

በዩክሬን የኬይቭ-ሃይሊች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዚያስቶስላቭ ሼቭቹክ፣ በምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ታኅሳስ 29/2013 ዓ. ም. የተከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ” የሚለውን ከሉቃ. 2:10 በመጥቀስ፣ ለመላው የዩክሬን ምዕመናን መልዕክት አስተላለፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ታኅሳስ 29/2013 ዓ. ም. ላከበሩት ወንድም እና እህት የምስራቅ ኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በላኩት መልዕክት “ብርሃናችን እና ተስፋችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ፣ መልካም የብርሃነ ልደቱ በዓል ይሁንላችሁ” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሼቭቹክ፣ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ስናከብር ብቸኞች አለመሆናችንን እናረጋግጣለን፤ ፍርሃት እንዳይዘን ብርታትን እናገኛለን፤ እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ በሰዎች መካከል የመገለጡ ምስጢርም ይህ ነው” በማለት፣ ከምስራቅ አብያት ክርስቲያናት መካከል በዩክሬን ለሚገኙት የግርክ-ካቶሊክ እና ኦርቶዶክስ ምዕመናን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ታኅሳስ 28/2013 ዓ. ም. የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ጊዜ፣ የምስራቅ ቤተክርስቲያናት፣ የኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናንን በማስታወስ “ሰላማችን እና ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በዩክሬን የኬይቭ-ሃይሊች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሼቭቹክም በበኩላቸው፣ አስቸጋሪውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሚያድነን ብቸኛው መንገድ መረዳዳት እና ወንድማማችነት መሆኑን አስረድተው፣ የአንድ ቤተስብ አባል መሆናችንን የምናውቀው ሰብዓዊ ክብራችንን እና ለችግር ተጋላጭነታችንን ስናውቅ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ ያከበሩት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከሌላው ጊዜ የተለየ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሼቭቹክ፣ መላው ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጠቃበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው "የብርሃነ ልደቱ በዓል ከእምነታችን የሚወለድ የተስፋ ምንጭ ነው" ብለው፣ እኛ ክርስቲያኖች ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስን በመመልከት እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ ወደ እኛ መምጣቱን እንገነዘባለን ብለዋል። አክለውም "በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ላይ ያለን እምነት፣ በመጪዎቹ ዘመናትም ብቻችን እንዳንሆን ተስፋን፣ ብርሃንን እና ጥበቃን በመስጠት፣ በቤተልሔም የተወለደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ብቻችን የማይተወን ተስፋችን ነው" ብለዋል።

“ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ” የሚለው የብርሃነ ልደቱ መልዕክት ድፍረትን እና ኃይልን እንደሚሰጥ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሼቭቹክ፣ ዩክሬን ባሁኑ ወቅት በፍርሃት ውስጥ እንደሚገኝ፣ በሚቀጥለው ዓመትም ምንም ዓይነት ዋስትና በሌለበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የመልአኩ መልካም ዜና ብርታትን እንደሚሰጣቸው እና በችግር ወቅት እግዚአብሔር ብቻቸውን እንደማይተዋቸው ገልጸዋል። ፍርሃትን ማሸነፍ የሚቻለው መጭው ጊዜ የጥፋት፣ የሞት እና የችግር ጊዜ እንዳልሆነ ገልጸው ተስፋቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንም አስረድተዋል።

"በተለይ ዘንድሮ እኛ ሁላችን የአንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባል መሆናችንን የተረዳንበት ነው" ያሉት ብጹዕ አቡነ ሼቭቹክ “ዘመናዊው የብቸኝነት ባሕል፣ የሰው ልጅ በሙሉ የአንድ ቤተሰብ አባል መሆኑን ለማወቅ አስችሎናል” ብለዋል። “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከገለጠልን እውነት አንዱ የሰው ልጅ በሙሉ አቅመ-ቢስ እና ደካማ መሆኑን ነው” ብለው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስም “አንዱ ያለ ሌላው እርዳታ ወይም እገዛ ሊኖር እንደማይችል” በማለት መናገራቸውን አስታውሰዋል። “እርስ በእርስ መረዳዳት ወንድም እና እህት መሆንን ያረጋግጣል” ብለው፣ አንድነትን በማሳደግ እና በመተጋገዝ ብቻ ተስፋን በማግኘት አስጨናቂውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቋቋም እንችላለን” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሼቭቹክ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ “መላው ዓለም አንድ ቤተሰብ መሆኑን በመገንዘብ፣ ደስታን እና ስቃይን፣ ተስፋን እና ሐዘንን በጋራ በመካፈል፣ መልካም ተግባሮቻችንን ለሌሎች የምንመሰክር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቤተክርስቲያን አባል ነን” ብለዋል።

07 January 2021, 20:20