ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳስ  

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2013 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የ2013 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልከት ለመላው ምዕምናን ያስተላለፉት መልዕክት ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ከርስቶስ ለሚታየዉ እግዚአብሔር እዉነተኛ ምሳሌ ነዉ፤ እርሱ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነዉ” (ቆላ 1፡ 15)

ብፁዓን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናት ፣ ገዳማውያንና/ውያት

ክቡራን ምዕመናን

በጎ ፈቃድ ላላቸዉ ሰዎች ሁሉ

ክቡራንና ክቡራን

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላዉ ክርስቲያን ምዕመናኖቻችን በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ብርሃነ ልደት በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጽላችኋለሁ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ከመወለዱ ከሺህ ዓመት በፊት አስቀድሞ እግዚአብሔር በናታን ነብይ አማካኝነት ከዳዊት ዘር አንድ ልጅ እንደሚወለድና እርሱም ንጉስ እንደሚሆን ለመንግስቱም መጨረሻ እንደሌለዉ ተናግሮ ነበር ፡፡

እንደሚታወቀዉ ከጌታችን መደኃኒታችን ኢየሱሰ ክርሰቶስ ቅድመ ልደት የነበረዉ ዘመን የእንቅልፍና የጨለማ ዘመን የነበረ ነዉ ፡፡ ሆኖም ሁሉን የሚችል የማይታየዉ አምላክ በልጁ አማካኝነት ምሳሌ በመሆን ተገለጸልን ፡፡

“እነሆ ህፃን ተወለዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ይባላል”(ኢሳ 9፡6)። ስለሆነም እርሱ በክብር ተወልዶ የእኛ ብርሃንና ሕይወት ሆኖልናል ፡፡ እኛም በልጁ አማካኝነት የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን በቅተናል ፡፡

ዓለም ሳይፈጠር በፊት እግዚአብሔር በልጁ በኩል ራሱን ከእኛ ከሰዎች ጋር ለማስተዋወቅ ማንነቱን ለማሳየት ፍጹም አምላክ ፍፁም ሰዉ የሆነዉን ልጁን ወደ ዓለም እንደሚልከዉ የታቀደ ነበር። ጌታም እንደ ሰው ሥጋ ለብሶ ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ ዓለም መጥቷል ፡፡ የደኅንነታችንንም መንገድ በማስተማር የመጣበትን ዓላማ ፈጽሟል ፡፡

ሁላችንም እንደምንገነዘበዉ በጌታ ልደት መንፈሳዊ ነፃነታችን ተሰጥቶናል ፤ ምክንያቱም ኃጢያታችንን ደምስሶ ነፃ አዉጥቶናል፤ በልደቱም የጽድቅ ልብስ አልብሶናል፤ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን የእኛም ንጉሥና መደኃኒት ሆኗል፡፡ ለዚህም በመዝሙር 95፡2-4 ላይ “ለእግዚአብሔር ዘምሩ አመስግኑትም የአዳኝንቱን መልካም ዜና በየቀኑ አብስሩ እግዚአብሔር ታላቅ ነዉ፤ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባዋል” ይላል። ለዚህም ነዉ እኛም በየቀኑ እግዚአብሔርን የምናመሰግነዉና ስሙንም የምንባርከዉ።

በዚህ የልደት ቀን እራሳችንን ለእግዚአብሔር በማቅረብ በልጅነት መንፈስ ተቀድሰን በጽድቅና በሕይወት መንገድ መጓዝ ይገባናል፡፡ ለዚህም ደግሞ በክርስቶስ ምሕረት በመደገፍ በፍቅር ተሳስረን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ በነገሮቻችን ሁሉ ፈጣሪያችንን እያስቀደምን ከተጓዝን እርሱ ክብር ይሆንልናል፤ በእኛ ላይም ይከብራል፡፡ ሁሌም ያለ እርሱ ድጋፍ መልካም መሆን የለምና ምሕረትህን አበርክትልን እያልን በአዲስ መንፈስ ወደ እርሱ እንቅረብ ፡፡

እኛም በክርስቶስ ልደት ለሰዎች የምንከፍለዉ ዕዳ አለብን ፡፡ ይህም ዕዳ ለሰዉ ልጆች ሁሉ የፍቅር ሥራ የሆነዉን መልካም ምግባር መፈፀም ነዉ ፡፡ ሰለዚህ መላዉ ክርስቲያን ምዕመናኖች ከሁሉ በሚበልጠዉ የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ “የተቸገርውን መርዳት” በሚለዉ ቃሉ መሰረት ለችግረኞችና ለምስኪኞች በተለይ በአሁኑ ጊዜ በስደት፣ በመፈናቀልና በመከራ ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን በማገዝ፣ በመደገፍ፣ በጌታ ፍቅር መልካም ነገሮችን እያደረጋችሁ በዓሉን በጋራ በማክበር ክርስቲያናዊ ግዴታችሁን እንድትፈፅሙ አደራ ማለት እወዳለሁ ፡፡

በመላዉ አገራችን በየጊዜዉ የምናየዉና የምንሰማዉ የሰዉ ልጆች ለቅሶና ሰቆቃ እንዲሁም መፈናቀል ክቡር የሆነዉና እግዚአብሔር በአርዓያዉና በአምሳሉ የፈጠራቸዉ ሰዎች በከንቱ ሕይወታቸው ልባችንን እያሳዘነ ማለፉ እንዲያበቃ ሁላችንም የሰላም ሰዎች በመሆን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ የጎሳ፣ የዘር፣ የቀለም፣ የጾታና የዕድሜ ልዩነት ሳይለያየን እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን ልንተባበር፣ ልንረዳዳና ልንተጋገዝ፤ አንድ ሆነን ልንቆም ይገባናል፡፡ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንዳፈቀረን እኛም በፍቅር ተሳስረን መኖር ይገባናል፡፡ መንግሥትም የሰዎች የመኖር መብትና የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ሰላም እንዲሰፍን የተያያዘዉን ጥረት አጠናከሮ እንዲቀጥል እንጠይቃልን ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በዚህ የጌታ ልደት የሰላም ሰዎች በመሆን ወደ እርሱ እንመለስ ተግተንም እንጸልይ ፡፡

መላዉ ሕዝባችን የዓለማችንና የአገራችን ስጋት ከሆነዉ ከኮቪድ 19 በሽታ እራሳቸውን ለመከላከል ተገቢዉን የመከላከያ ዘዴዎችን ሳይሰለቹ በመጠቀምና በመተግበር ከበሽታዉ እራሳቸዉን እንዲጠብቁም ማስገንዘብ እንወዳልን ፡፡

በመጨረሻም በወጭ አገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮያውያን መልካም ኑሮና ሕይወት እንዲኖራችሁ፣ በህመም ላይ በየሆሰፒታሉና በየቤታችሁ የምትገኙ ፈዉስን፣ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ታራሚዎች መፈታትን፣ በስደት ላይ የምትገኙ ወገኖቻችን ወደ አገራችሁና ወደ ቄያችሁ በሰላም መመለስን፣ የአገርን ድንበርና የሕዝቦችን ሰላም ለማስከበር በየጠረፉ የምትገኙ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላት የሥራ ሰኬትን እየተመኘሁላችሁ ሁላችሁንም እንኳን ለ2013 ዓ.ም ለጌታችን ለመደኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

እግዚአብሔር አገራችንን እና ሕዝቦቻችንን ይባርክልን ይጠብቅልን

መልካም የልደት በዓል ይሁንላችሁ

+ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት

06 January 2021, 11:38