የታኅሣሥ 11/2013 ዓ.ም ሰንበት /ዘስብከት 1ኛ/ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ የታኅሣሥ 11/2013 ዓ.ም ሰንበት /ዘስብከት 1ኛ/ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ 

የታኅሣሥ 11/2013 ዓ.ም ሰንበት /ዘስብከት 1ኛ/ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.    ዕብ 1፡1-14

2.   2ጴጥ. 3፡1-9

3.   ሐዋ. 3፡ 17-26

4.   ዬሐ. 1፡44-51

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ፊልጶስንና ናትናኤልን ጠራቸው

በማግሥቱ፣ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አግኝቶ፣ “ተከተለኝ” አለው። ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው። ናትናኤልም፣ “ከናዝሬት በጎ ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ።

ፊልጶስም፣ “መጥተህ እይ” አለው።ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ። ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ፣ ገና ፊሊጶስ ሳይጠራህ አየሁህ” ሲል መለሰለት።ናትናኤልም መልሶ፣ “ረቢ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ።

ኢየሱስም፣ “ያመንኸው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልሁህ ነውን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው፤ ጨምሮም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።

የእለት አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ዛሬ በሥርዓተ አምልኳችን አካሄድ መጪዎቹ ሦስት ሰንበቶች ስብከተ ገና ማለትም የጌታችንን ሰው መሆን ለምናከብርበት ወቅት መዘጋጃ የሚሆን ወቅት ነው። ኃያል፣ ቅዱስ፣ ሰማያዊው አምላክ እኛን መምሰል ሳይሆን እኛን መሆኑን የምናስታውስበት ልዩ ወቅት ነው። ስብከተ ገና የእሱ በዓለም ታሪክ ውስጥ መግባት የዓለምን አቆጣጠር ወደ ዓመተ ምሕረት እንደቀየረው ሁሉ የእኛንም ሕይወት በምሕረቱ ሊሞላት በርሱ በኩል ሁሌም ዝግጁ መሆኑ የሚሰበክበት ወቅት ነውና የዛሬው ሰንበት "ዘስብከት" ይባላል።

በመጀመሪያው መልዕክት ሲነበብ እንደሰማነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይህ አንድያ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ ስልጣንና ኃይል ሁሉ የእርሱ እንደነበረ በማቴ. ወንጌል 28፡ 18 ይገለፃል፡፡ የቡሉይ ኪዳን ነቢያት ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰውን መንገድ አመለከቱ ስለ ክርስቶስ መንግሥት መምጣት ትንቢት ተናገሩ ክርስቶስ ራሱ ግን የእነዚህ ትንቢቶች ፍፃሜ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ አንድያ ልጁ በመሆኑ የአብ የሆነው ሁሉ የእርሱ ነው፡፡ 2ቆሮ4፤4 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ አምሳል ነው ይላል፡፡

እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ የፈጠረው ከዚህ ከአንድያ ልጁ ጋር መሆኑን የዩሐንስ ወንጌል ም.1 ላይ ይናገራል፡፡ “በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ አልሆነም፡፡”

ነቢያቶች አስቀድመው የተነበዩለት መላእክትም በፊቱ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ የሚያገለግሉት ይህንኑ አምላክ መሆኑን መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙር 99፡5 ጀምሮ ተናግሮታል እንዲህም ይላል አምላካችን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት በእግሩ መርገጫ ስገዱ እርሱ ቅዱስ ነውና ሙሴና አሮን ካህናቱ ከነበሩት መካከል ነበሩ ሳሙኤልም ስሙን ከጠሩት መካከል አንዱ ነበር እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ተጣሩ እርሱም መለሰላቸው ከደመና ዓምድ ውስጥ ተናገራቸው እነርሱም ሥርዓቱንና የሰጣቸውን ድንጋጌ ጠበቁ ይላል፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ የተፈጠረው ሁሉ የእርሱ ነው እኛንም በአምሳሉ የፈጠረን እርሱ ነው፡፡ ለዚህ ለፈጠረን ላዳነነ አምላካችን እኛም የድርሻችንን ክብርና አምልኮ ልናቀርብለት ይገባል ከፍ ከፍ ልናደርገው ይገባል በእግሩ መርገጫ ልንሰግድለት ይገባል ምክንያቱም እርሱ ቅዱስ ነውና ፡፡

ለእግዚአብሔር አምላካችን የምናቀርበው ክብርና አምልኮ አይሁዳውያን ያቀርቡ እንደነበረው የሚቃጠል መስዋት ሳይሆን በእርሱ ቃል የሚኖር፣ በእርሱ ተስፋ የሚኖር የተፀፀተና ከኃጢአያት የነፃ ልባችንን ሊሆን ይገባል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ በተነበበው በዕብራውያን መልእክቱ የሚያስተምረን ይህን ነው ፤ ከሁሉ አስቀድመን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪያችን መሆኑን እንድናውቅና ወደን እንድንቀበል ከዛም ለእርሱ ትዕዛዝ ተገዝተን በቃሉ እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡

2ኛ የጴጥ. 3፡1-9 ላይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ዳግመኛ የሚመጣበት ጊዜ ስለዘገየ ከእንግዲህ ወዲህ አይመጣም የዓለም ፍጻሜ የሚባል ነገር የለም በማለት አንዳንድ የሐሰት ትምህርት ስለሚየስተምሩ ሰዎች ይናገራል፡፡ ነገር ግን የእርሱ መዘግየት እኛ ልጆቹ ከክፉ ሥራችን የምንመለስበትንና ከኃጢያታችን ፀድተን እንዲያገኘን በሙሉ ንጽሕና ተዘጋጅተን እርሱን በመጠበቅ ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንድንወርስ ጊዜ ሊሰጠን በመፈለጉ ብቻ ነው፡፡ ደጋግመን በምንሰራው ኃጢያታችን ምክንያት የቆሸሸውን ልባችንን ያደፈውን ሕሊናችንን እንድናፀዳ ጊዜ ስለሰጠን ብቻ ነው። ጊዜና ቦታ በእኛ በሰዎች አመለካከት እንጂ በእግዚአብሔር ቤት ቦታ የለውም እግዚአብሔር በጊዜ አይወሰንም እግዚአብሔር በቦታ አይወሰንም እግዚአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም ለዚህ ነው በጌታ ዘንድ አንድ ቀን አንደ ሺህ ዓመት ሺህ ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ቀን ይቆጠራል የሚለው፡፡ ዳዊትም በመዝሙር 90፤4 ላይ ይህንኑ ሐሳብ እንዲህ ይገልጸዋል ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን እንደ ሌሊትም ንጋት ነው ይላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰዎች አንድ እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም ለዚህም በቂ ጊዜ ሰጥቶናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንድንዘጋጅ ያስፈልጋል፣፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንገት በሚመጣበት ጊዜ ለመዘጋጀት ጊዜ አይኖርም።

የኖህ መርከብ በሩ ከተዘጋ በኃላ እንዳልተከፈተና በመርከቡ ያልገቡት ሁሉ እንደጠፉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንገት በሚመጣበትም ጊዜ እኛም በኃጢያታችን መክንያት እንዳንጠፋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን ጊዜ ውስጥ መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡፡

ከዛሬው ወንጌል በፊልጶስ፣ በናትናኤልና በኢየሱስ መካከል የተደረገውን ንግግር እንውሰድ። ፊልጶስ በኢየሱስ ከተጠራ በኋላ ናትናኤልን ሲያገኘው፦ "ሙሴ በሕግ መጽሐፍ ነቢያትም በትንቢት መጻሕፍት ስለ እርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤ እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው" አለው። ናትናኤል ግን "ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገኝ ይችላልን?" አለው። ፊልጶስም "መጥተህ እይ" አለው። ኢየሱስ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ "እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው!" ሲል ስለ እርሱ ተናገረ(ቁ.44-47)። ጊዜ ሰጥቶ በማስተዋል ላሰበው ሰው በነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በተለያየ መልኩ ይሁን እንጂ ዘወትር የሚደጋገም እውነት አለ። እግዚአብሔር ደካማ ሆኖ፣ በሥጋ ሰው ሆኖ፣ በማይመስለን መልኩ ሲገለጽ ሰው ደግሞ ሲንቀውና ሲጠራጠረው ይታያል። "ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገን ይችላልን?" - እግዚአብሔር ናዝሬትን መረጣት፤ በማይመስልና በሚናቅ ነገር መሥራት ልማዱ የሆነ አምላክ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬም ይህን እውነት ያደርጋል።

ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን ሰው መሆን ነበረበትና ይህን ለመተግበርም ከኃጢአት በስተቀር እንደሰው ተቆጠረ፣ ተወለደ፣ ተናቀ፣ ተንገላታ፣ ተራበ፣ ተጠማ፣ ተሰደደ፣ ታማ፣ ለሌባና ለነፍሰ ገዳይ የሚደረግ ፍትሕና እንክብካቤ ተነፍጎት ተሰቀለ ሞተ። እሱ ፍጹም ሰው ነበርና እያንዳንዷ ስቃይ እኛን ከምታሰቃየን በላይ ብዙ እጥፍ እንደምታሰቃየው መገመቱ ከባድ አይደለም።

ይህ በክርስቶስ ላይ የተፈጸመው እውነታ "በአንድ ወቅት" የነበረ ክሥተት አይደለም። እግዚአብሔር ዛሬም ደካማ ነገሮችን የመምረጥ አሠራሩን አልቀየረም፤ የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ድካም በሆኑ ነገሮች ውስጥ የሚገኘውን ጸጋ መናቁን አላቋረጠም። የሚገርመው ነገር ደግሞ ደካማው ኃያሉን ሲንቅና ኃያሉ ግን ደካማውን ሲይከብረው ማስተዋሉ ነው። ናትናኤል ስለ ኢየሱስ "ከቶ ምን መልካም ነገር ይገኛል" ሲል ኢየሱስ ግን ስለ ናትናኤል "እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው" አለው።

"ከኅብስትና ከወይን ከቶ የክርስቶስ ሥጋና ደም ሊገኝ ይችላልን?" የሚሉ ዛሬ ዛሬ ቁጥራቸው ጥቂት ላይሆን ይችላል። ምናልባትም በቃላት ባይሉትና ባይክዱትም በተግባር ግን በመራቅና ባለመሳተፍ ይህን ንቀት በአክብሮት ስም የሚያስተጋቡትን አካቶ ማለት ነው (የምናከብረውንና የምንወደውን ላለመራቅ የሚቻለንን እንጥራለንና ቅዱስ ቁርባንን ስለማከብርና ስለምወድ አልቀርበውም የሚል አባባል በራሱ የተጋጨና ትርጉም የለው አባባል ነው)። ክርስቶስ ግን "ሥጋዬን የሚበላና ደሜንም የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው" (ዮሐ.6:54) ይለናል። እንደ ወንጌሉ ዛሬም እኛ ስንንቀውና ስናርቀው እሱ ይጋብዘናል፣ ያከብረናል ይቀርበናልም። የእሱ አካል የሆነችውና እሱ ፈቅዶ በተለመደ አመራረጡ በደካማ ሰዎች ላይ የቆረቆራትን ቤተ ክርስቲያንን በተለያየ መልኩ ለመናቅና ለማዋረድ ጥረት ባደረግን ቁጥር ለንስሐና ለቅድስና ዘወትር በራሷ በኩል ይጋብዘናል።

ይህን ሀሳብ የእሱን መወለድ ለማክበር በምናደርገው ዝግጅት ሂደት ውስጥ በጸሎት እያሰላሰልን ዛሬም እግዚአብሔር ደካማ በሚመስሉ ነገሮች የሚያደግልንን ጥሪ ተቀብለን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ዳግም የምንወለድበትን ጸጋ አናሳልፍ።

ይህንንም ለማድረግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን የሰማነውንም  የእግዚአብሔር ቃል በሕወታችን ለመተርጎም እንድንችል ልባችንን ያነሳሳልን፡፡

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

19 December 2020, 12:00