50ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤው ተከነወነ 50ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤው ተከነወነ 

50ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤው ተከነወነ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት 50ኛ መደበኛ  ጉባኤ ከታኅሣሥ 6 እስከ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኮንሶላታ አባቶች ገዳም ተካሂዷል።

ጉባሄው ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት በመሩት መሥዋዕተ ቅዳሴ ተጀምሯል። ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በጉባኤው መክፈቻ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ በማለት በሃገራችን በተከሰተው ግጭት እና አለመረጋጋት ምክንያት በጉባኤው ላይ መገኘት ያልቻሉትን የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴን እና በሀገረስብከቱ የሚገኙ ካህናት፣ ደንግል እና ምእመናንን በሙሉ በማሰብ እንዲሁም በትግራይ ክልል እና በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች አማካኝነት ውድ ሕይወታቸውን ላጡ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን በሙሉ ልዩ ጸሎት አድርገዋል። ሕዝበ እግዚአብሔር በሙሉ ጸሎት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉም አበክረው አሳስበዋል።

ብፁዕ ሊቀ ጳጳሳት አንቷን ካሚሌሪ በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር አምባሳደር በበኩላቸው በጉባኤው ለተሳተፉ ጳጳሳት መልዕክት በማስተላለፍ የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ በዚህ ጉባኤ ላይ መሳተፍ ባለመቻላቸው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል። አያይዘውም ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በቅርበት የሚከታተሉት መሆኑን በተደጋጋሚ በይፋ የገለጹ እና ሰላማዊ መፍትሔም እንዲፈለግ ያሳሰቡ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጉባኤው በቆይታው በሃገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያሉ ሁኔታዎችን አስመልክቶ በጥልቀት የተወያየ ሲሆን ቤተክርስቲያን በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብዕእዊ ድጋፍ ማበርከት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል። እንዲሁም ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ካሪታስ ኢንተርናቲኦናሊስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል። በትግራይ እና በሌሎች የሃገራችን አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ የሚያስተባብር ግብረሃይልም ቀደም ሲል ተቋቁሞ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን የኢትዮጵያ የገዳማት የበላይ ዐለቆች ጉባኤም በሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎቱ የሚሳተፍ መሆኑ ታውቋል። ጉባኤው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት በአዲስ መልክ እንዲደራጅ በጽ/ቤቱ የአስተዳደር ኮሚቴ የቀረበለትን ምክረ ሃሳብ ተቀብሎ በማጽደቅ አዲሱ መዋቅር እ.አ.አ. ከጥር 1/2021 ዓ.ም. ጀምሮ በጽ/ቤቱ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፏል። ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የገቢ ማስገኛ የሚሆን ባለ ስድስት ወለል ሕንጻ ግንባታ ለማከናወን ታኅሣሥ 8/2013 ዓ.ም. የሰበካ ጳጳሳት በተገኙበት በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት መሪነት የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል። የሕንጻ ግንባታው የሚከናወነው በተለምዶ ሰሚት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን ቤተክርስቲያን ለምታከናውናቸው አገልግሎቶች የራስን የገቢ ዐቅም ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑ ተመልክቷል።

ጉባኤው እስከ ታኅሣሥ 10/2013 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን ለብፁዕ አቡነ ተስፋ ስላሴ መድህን የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ የወዳጅነት መግለጫ ደብዳቤ አስተላልፈዋል። በተያያዘም በማላዊ የሊሎንጉዌ ሊቀጳጳሳት በነበሩት ታርቺዚዮ ጌርቫዚዮ ዚያዬ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ የሃዘን መግለጫ መልዕክት ለማላዊ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ እና ለሊሎንጉዌ ሰበካ ልከዋል።

ምንጭ፡ አቶ ሐብታሙ አብርደው፣ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ሴክሬቴሪያት አዲስ አበባ

19 December 2020, 13:28