ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  

በአንዲት ቅድስት ካቶሊካዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እናምናለን!

ለምን ቤተክርስቲያናችንን ካቶሊክ እንላለን?

“ካቶሊክ” ማለት አጠቃላይ፤ ዓለም አቀፋዊ፤ ለሁሉም ሰዉና ለሁሉም ዓለም የሚሆን ማለት ነዉ፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉንም ዓለም፤ ሁሉንም አገር፤ ሁሉንም ዘር፤ ሁሉንም ባህልና፤ ሁሉንም ትዉልድ የምታቅፍ ስለሆነች ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንላታለን፡፡

ለምን ቤተክርስቲያናችንን ሮማዊት እንላለን?

ቤተክርስቲያናችን ሮማዊት ነች፤ ምክንያቱም የቤተክርስቲያናችን የመጀመርያ እረኛ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮማ ስለኖረ፤ ስለሞተና እዛዉም ስለተቀበረ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመርያዉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስ ነዉ፡፡ አሁንም ታዲያ የሮሙ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ የመላዋ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የበላይ እረኛ ነዉ፡፡ እሱ የክርስቶስ ተከታዮችን በአንድ ላይ የሚጠብቅና የመላዋ ቤተክርስቲያን አንድነት ምሳሌ ነዉ፡፡ በሮም ያለዉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳችን ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የመሠረተበት የጴጥሮስ አለት ነዉ፡፡ ከዚህ እረኛዋ ጋር ሆና በምታደርገዉ ትግል ቤተክርስቲያን ምን ጊዜም የዓለም ኃይላት ሊያሸንፉዋት አይችሉም፣ ይህ ደግሞ ክርስቶስ ራሱ የገባላት ቃል ነዉ፡፡ (ማቴ. 16፡18)

ሌሎች ደግሞ ኦርቶዶክስ የሆኑ ካቶሊኮች አሉ፤ በተለይም ግርክና ራሽያ በመሳሰሉ አገሮች ዉስጥ የሚገኙ፤ ከነዚህ አንዳንዶቹ ከሮማው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ኅብረት ያላቸዉ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ የሌላቸዉ ናቸዉ፡፡

ለምን ቤተክርስቲያናችን አንዲት ናት እንላለን?

ቤተክርስቲያናችንን አንዲት ናት የምንልባቸዉ በርካታ ምክንያቶች አሉ።

ከሰዉ ዘር ሁሉ የተወጣጡ በሁሉም ሀገሮች የሚገኙ ካቶሊካዊያን ሁሉ እኩል የሚያከብሩትና የሚጋሩት አንድ ቅዱስ ቁርባን ያላት በመሆኑ ነዉ፡፡ በዚህ እጅግ ቅዱስ በሆነዉ ምሥጢር አማካይነት ክርስቶስ  በዚህ ማዕዱ ዙሪያ እንደ አንድ ቤተሰብ ሰብስቦን በግልጽ የሚያስተሳስረን እርሱ ነዉ፡፡

እኛ ካቶሊኮች በዓለም ዙሪያ ሁሉ ተመሳሳይ የአምልኮ ስርዐት ያለን ሲሆን  ካቶሊኮች ሁሉ ከሮማው ጳጳስ ጋር በጠበቀ ኅብረት ሲኖሩ ምን ጊዜም በማንኛዉም ስህተት ሳይነቃነቁ ከጴጥሮስ አለት ጋር በፍጹም አንድነት ይኖራሉ፡፡

በሮም ያሉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመላይቱ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአንድነት ተምሳሌት(ቋጠሮ) ናቸዉ፡፡ እሳቸዉ ዝም ብሎ የቤተክርስቲያኒቱ ራስ ወይም የበላይ ሳይሆኑ ክርስቶስን ወክሎ በቅዱስ ቁርባን ምሥጢር ከክርስቶስ ጋር ለሚኖረን ፍጹም አንድነት የሚመሩ ሊቀ ካህን ናቸዉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ክርስቶስ የተመኘዉ አንድነት በተከታዮቹ ዘንድ በሙላት ያለመኖሩ በጣም ያሳዝነናል፡፡ ለዚህ አንድነት ማጣት ካቶሊክ ቤተክርሰቲያን በቱርክ ዉስጥ ያደረገችዉ አስተዎጽዖ አለ፡፡ በመሆኑም ር.ሊ.ጳ ጳዉሎስ 6ኛ እና ዮሐንስ ጳዉሎስ ዳግማዊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በዘመናት ጉዞዋ ለክርስቶስ ተከታዮች መልካም የፍቅርና የእምነት ምሳሌ ያልሆነችባቸዉ አጋጣሚዎች እንዳሉ አምነዉ በዚህ ምክንያት በክርስቲያኖች መካከል ስለተፈጠረዉ መከፋፈል ሁሉ እኛም እኩል ተጠያቂዎች ነን በማለት በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የሆነ ሆኖ “ሁሉም አንድ እንዲሆኑ” ከጌታ ጋር እኛም በጸሎት እንተጋለን፡፡ (ዮሐ.17፡21)

ቤተክርስቲያናችንን ለምን “ሐዋርያዊት” እንላታለን?

ቤተክርስቲያናችንን በትክክል “ሐዋርያዊት” የምንልበት ሁለት ምክንያቶች አሉ፡-

አንደኛዉ ባልተቆራረጠ ሰንሰለት ከሐዋርያት ጀምሮ በጳጳሳትና አቡናት መተካካት እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀች በመሆኗ ሲሆን ሁለተኛዉ ቤተክርስቲያናችን በር.ሊ.ጳጳሳት እና በአቡናት አመራር ሥር ሆና የሐዋርያትን ትምህርትና እምነት የምትኖር፤ የምታስተምርና የምትጠብቅ በመሆኗ ነዉ፡፡

ቤተክርስቲያናችንን “ቅድስት” የምንለዉስ ለምንድነዉ?

ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስብስብ ማለት ነዉ፤የጌታ የሆኑ ሁሉ ማለት ነዉ፡፡ ቤተክርስቲያንን “ቅድስት” የሚያደርጋት ጌታ ራሱ ነዉ፡፡ እሱ ሙሽራዉ ሙሽሪትን እንደሚወድ ቤተክርስቲያንን ይወዳታልና፡፡ እኛ ካቶሊኮች ሐጥያተኞች መሆናችንን እንናዘዛለን፤ ነገር ግን የክርስቶስ ፍቅር እንደሚቀድሰንና የቅድስት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አካል እንደሚያደርገን እንናገራለን/እናዉጃለን፡፡

ክርስቶስ ስለቤተክርስቲያኑ ሞቷል፤እኛን ሐጥያተኞቹን ይቅር ብሎን እንደገና ይቀድሰናል፡፡ ለዘለዓለም ከኛ ጋር ሆኖ ሊቀድሰንና ሊያጠነክረን ስለፈለገ ቅዱስ ቃሉንና ሰባቱን ምሥጢራት ሰጥቶናል፡፡ ራሱ ክርስቶስ በመካከላችን ሆኖ ከኛ ምስኪን ባህሪያችንና አሳፋሪ ዉድቀታችን ባሻገር ሮማዊት ካቶሊካዊት ሐዋርያዊትና ቅድስት ቤተክርሰቲያናችንን ሁሌም ይቀድሳታል፡፡ ይህ ሁሌም በደስታና በኩራት የምንናገረዉና የምናበስረዉ ካቶሊካዊ እምነታችን ነዉ፡፡

 

06 November 2020, 11:33