የሕዳር 20/2013 ዓ.ም 33ኛው እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሕዳር 20/2013 ዓ.ም 33ኛው እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የሕዳር 20/2013 ዓ.ም 33ኛው እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      መጻፈ ምሳሌ 21፡10-13፣ 1430

2.    መ. መዝሙር 127

3.    1ኛ ተሰሎንቄ 5፡1-6

4.    የማቴ 25፡ 14-30

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የሰነፉ አገልጋይ ምሳሌ

“የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ። አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።

“የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።

“ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

“አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው። “ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሮአል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።

“ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ስለ እግዚኣብሔር ስጦታ ያናገራል። እግዚኣብሔር ለእኛ የሚሰጠን ስጦታ “እንደ እየ አንዳንዳችን ችሎታች” እንደ ሆነ ይናገረናል።  ከሁሉም አስቀድመን ግን “ስጦታ እንደተሰጠን” በእግዚኣብሔር ፊትም ባለስጦታዎች እንደ ሆንን ልብ ልንል ይገባል። ስለዚህም ማንም ሰው ቢሆን ከዚህ ውጭ የሆነና የማይጠቅም መስሎት ሊሰማው አይገባም፣ ማንም ሰው ለሌላው ሰው ምንም የምሰጠው ነገር የሌለው ሙልጭ ያለ ደኾ አድርጎ ራሱን መቁጠር የለበትም። አንድ እናት እና አንድ አባት ለልጆቻቸው ሊሰጡት ከሚመኙት ነገር በተሻለ መልኩ ሁላችንም ከእርሱ ስጦታዎች እንድንቋደስ በእግዚኣብሔር የተመረጥን እና የተባረክን ሰዎች ነን። ስለዚህም ከእግዚኣብሔር ፊት ማንም ሰው የተገለለ አይደለም፣ እርሱ ለእያንዳዳችን ተልእኮ ይሰጠናል።

ከዚህም አባትነት ፍቅሩ በመነጨ መልኩ የኃላፊነት ግዴታዎችን ይሰጠናል። ዛሬ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ እያንዳንዱ አገልጋይ ፍሬ እንዲያፈሩበት የተለያዩ ዓይነት ስጦታዎች ሲሰጣቸው ሰምተናል። የመጀምርያዎችሁ ሁለቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ሲወጡ ሦሰተኛው አገልጋይ ግን የተሰጠውን ስጦታ ፍሬያማ እንዲሆን አላደረገም፣ የተቀበለውን ብቻ እንዳለ ምንም ፍሬ እንዲያፈራ ሳያደርግ “በጣም ሰለፈራው የሰጠህኝን ስጦታ ሄጄ በመሬት ውስጥ ቆፍሬ ደበኩት” በማለት መልሶ ለባሌበቱ ስያስረክባል። ይህ አገልጋይ ለፈጸመው ተግባር “አንተ ክፉ እና ሰነፍ አገልጋይ” የሚል ጠንከር ያለ ተግጻጽ ሲደርስበትም ሰምተናል። ታዲያ ባሌበቱ ከዚህ አገልጋይ ያልወደደው ነገር ምንድነው? ይህንንም በአንድ ቃል መግለጽ ይቻላል ይህም አሁን በእኛ ዘመን ብዙን ጊዜ የሚታይ ወቅታዊ የሆነ ቃል ነው ይህም “መተው” ወይ ችላ ማለት የሚለው ቃል ነው ብዬ ለመውሰድ እችላለሁ። የእዚህ አገልጋይ ዋንኛው ችግር የነበረው መልካም ነገር ለማድረግ አለመነሳሳቱ ነው። እኛም ራሳችንን አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ነገሮችን ባለመፈጸማችን ብቻ መልካም እና ሀቀኛ የሆንን ሰዎች እንደ ሆንን  ስለምናስብ በጣም እንደሰታለን። በዚህ መልኩ የምናስብ ከሆንን ግን ያንን “ክፉ እና ሰነፍ” የሆነው አገልጋይ እንመስላለን፣ እርሱም ቢሆን እኮ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር አልሠራም፣ የተሰጠውን ስጦታ አላጣፋም፣ እንዲያውም እንዳይጠፋ በማሰብ መሬት ውስጥ ቆፍሮ ነው በጥንቃቄ ሰው የማያገኝበት ቦታ ነበር የቀበረው። ክፉ ነገር አለማድረግ ብቻ በቂ አይደለም። አንድ አባት  ከልጆቹ መልካም የሆነ ፍቅር ካላገኘ ያዝናል። ይህ ክፉ እና ሰነፍ የሆነ አገልጋይ ስጦታዎቹን የተቀበለው ማካፈል ከሚወደው እና ስጦታችንን ፍሬያማ እንድናደርግ ከሚፈልገው ከጌታ ነው፣ እርሱ ግን ፍሬ እንዲያፈራ ሳይሆን በቅናት ለራሱ ብቻ ደብቆ ማስቀመጥ አስደሰተው። ባለፉት ጊዜያት የተሰጡትን ስጦታዎች ደብቆ የሚያስቀምጥ ሰው በዚህ ተግባሩ የተነሳ ለእግዚኣብሔር ታማኝ ሰው አይደለም። ነገር ግን የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚለን፣  የተሰጠውን ስጦታ ፍሬያም እንዲሆን የሚያደርግ ሰው ታማኝ ነው፣ ምክንያቱም እግዚኣብሔር የሚያስበውን ነገር ነው እርሱም የሚያስበው ሌሎችን ይወዳል፣ ለሌሎች መስዋዕት ለመሆን የሕይወት ቀነበርን ይሸከማል፣ ሁሉንም ነገር በነበረበት ቦታ ሊተው አይፈልግም። ስለ ራሱ ብቻ አያስብም፣ ራሱንም ተቃሚ አድርጎም አይቆጥርም።

የቸልተኛነት መንፈስ በተለይም ለድኾች የምናሳየው ቸልተኝነት በጣም ትልቅ ኃጢኣት ነው። በዚህ ረገድ አንድ ቃል መጠቀም እንችላለን “ችላ” ማለት። “ እኔን አይመለከተኝም፣ የእኔ ተግባር አይደለም፣ የማኅበረሰቡ ስህተት ነው እንጂ የእኔ ችግር አይደለም” በማለት በችግር ውስጥ የሚገኙትን ወንድሞች እና እህቶቻችንን በምናይበት ወቅት ፊታችንን ማዞር፣ መጥፎ ነገር ሲፈጸም እያየን ምንም እንዳልተከሰተ ዝም ማለት ይህ የቸልተኝነት ወይም የምን አገባኝ ስሜት ነው። ነገር ግን እግዚኣብሔር እኛን የሚጠይቀን ክፉ ነገር አልስሰራህም ወይ? ብሎ ሳይሆን ምን መልካም ነገር ሠራህ? ብሎ ነው የሚጠይቀን።

እንዴት ነው ታዲያ ተጨባጭ በሆነ መልኩ እግዚኣብሔርን ማስደሰት የምንችለው? አንድ የምንወደውን ሰው ለማደሰት በማሰብ ስጦታ በምንገዛበት ወቅት ከሰውየው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ስጦታ መፈለግ ይኖርብናል፣ ይህም ስጦታውን ከሚሰጠው ሰው ይልቅ ስጦታውን የሚቀበለው ሰው የተገባ እንዲሆን ይረዳል። ለእግዚኣብሔር የሆነ ነገር መስዋዕት ማድረግ ስንፈልግ፣ እርሱ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ በወንጌል ውስጥ ተጠቅሰው ይገኛሉ። ዛሬ በሰማነው ቅዱስ ወንጌል ምዕራፍ ማብቂያ ላይ “‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል። እነዚህ ትናንሽ የተባሉ ወንድሞች፣ በእርሱ ዘንድ የተመረጡ፣ ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛል፣ እንግዳ ሆኜ አስተናግዳችሁኛል፣ ታስሬ ጠይቃችሁኛል የተባሉት ድኾች እና የተገለሉ፣ ያለ ምንም እርዳታ እየተሰቃዩ የሚገኙ ሰዎች፣ የተረሱ የተጣሉ ሰዎች ናቸው።  በእነርሱ የተጎሳቆለ ፊት ላይ የእርሱን ፊት እናያለን፣ በከንፈሮቻቸውም ላይም ቢሆን ምን አላባት በሕመም ምክንያት ከንፍሮቻቸው እንኳን ዝግ ቢሆኑም “ይህ ሥጋዬ ነው” የሚል የእርሱን ድምጽ እናገኛለን። ድኾችን በመጠቀም ኢየሱስ የእያንዳንዳችንን ልብ በማንኳኳት፣ ተጠምቻለሁ በማለት ፍቅር እንድናሳያቸው ይጠይቀናል። የግድየለሽነት መንፈስን አሸንፈንና በኢየሱስ ስም ለእርሱ ታናናሽ ወንድሞች ለሆኑት ጊዜያችንን በምንሰዋበት ወቅት የእርሱ ጉደኞች እና መልካም አገልጋዮች እንሆናለን።

ስለዚህም ለእኛ የተትረፈረፈ ሕይወት ከመመኘት ይልቅ ለድኾች መልካም ነገር ማድረግ ይሻላል፣ ይህንን በምናደርግበት ወቅት ሁሉም መልካም ነገር ይጨመርልናል። ሚስኪን በመሆናችን የተነሳ ምሕረት የሚያደርግልን እግዚኣብሔር አባታችን ስጦታዎቹን እንዲያለብሰን ፣ ጥበብንና ማፍቀር እንድንችል ብርታት እንዲሰጠን በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር የተደገፈ መልካም ነገር ማድረግ እንድንችል ይርዳን።

28 November 2020, 11:58