ካርዲናል ብርሃነየሱስ የዐባይ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!

"ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር . . .

የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው። እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።"

ዘፍ. 2፡ 10 -13

የእግዚአብሔር ቃል “ግዮን” ብሎ የሚጠራው የዐባይ ወንዝ በኢትዮጵያ የሚገኝ ምድርዋንም የሚከብብ ወንዝ ነው። ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጣት አንጂ ማንም በቸርነቱ ያደረገላት አይደለም። ከእግዚብሔር ከራሱ የተቸራት በመሆኑ በዐባይ ወንዝ የመጠቀም ዕድሏን ማንም ሊከለክላት አይችልም። ዐባይን ማልማት አስቀድሞ አግዚአብሔር የፈቀደውን መተግበር ነው፤ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ምንም ተቃርኖ የለውም። እግዚአብሔር ፍትህን የሚወድድ አምላክ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ዐባይን በማልማት መጠቀም በፈጣሪ የተሰጣት ፍትሐዊ መብቷ ነው። በርካታ የኢትዮጵያ ልጆች አስከዛሬ ድረስ በጨለማ ይኖራሉ። በድህነትም ይማቅቃሉ። ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ ተጠቅማ ሕዝቦቿን ከድህነት እና ጨለማ ማውጣት ተፈጥሯዊ መብቷ ነው። ይልቁንም አጅጉን የዘገየንበት ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የዐባይ ግድብ ግንባታን በተመለከት ቅድሚያ ለውይይት መስጠቱን እና እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ችግሮች በአፍሪካውያን አደራዳሪነት እንዲፈቱ የሚከተለውን እጅግ ብልሃት የተሞላው አካሄድ እናደንቃለን።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የዐባይን ግድብ ግንባታ ከግብ ለማድረስ ያለማሰለስ ስትሠራ፣ ምእመናኖቿን፣ በተቋማቶቿ የሚገለገሉ ሰዎችን፣ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሁሉ ሰታስተባብር አና ድጋፍ ስታሰባስብ ቆይታለች። እንዲሁም በሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ቡድን ውስጥ ኣባል በመሆን እና ተሳትፎ በማድረግ በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር መልካም ግንዛቤ የማስጨበጥ አስተዋጽዖ አድርጋለች። ይኸው ተግባሯም የግድቡ ግንባታ ግቡን አስከሚመታ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰጡትን መግለጫ የሰማነው በከፍተኛ ሃዘን ነው። ፕሬዝደንት ትራምፕ የተናገሩት ንግግር መላውን የአሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥታቸውን ይወክላል ብለን ፈጽሞ አናምንም። ሆኖም ታላቂቷን አሜሪካ ዳግም የመገንባት መርህን አንግቦ ከሚጓዝ መሪ ልናዳምጠው የሚጠበቅ ንግግር ባለመሆኑ አሳዝኖናል።

ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ. ነሐሴ 15 ቀን 2020 ዓ.ም. ባስተላልፉት መልዕክት እንደገለጹት በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ መካከል ያሉት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን የተመለከቱ ልዩነቶች በሙሉ እጅግ በሰለጠነ እና የሁሉንም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ማድረግ እና ይህንን መንገድ ብቻ መደገፍ ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል የምትሉ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና ለሀገራችሁ ብልጽግና ቀናዒ የሆናችሁ በሙሉ ማንኛውንም ልዩነቶቻችሁን ወደጎን በመተው ሀገራዊ በሆኑ ፐሮጀችቶች ላይ ሁሉ የጋራ አቋም በመያዝ ትብብር እንድታደርጉ እማጸናችኋለሁ።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችሁ፣ አናቶቻቸሁ፣ ወንድሞቻችሁ እና አህቶቻችሁ በገዛ ላብ አና ወዛቸው የገነቡት ይህ ግድብ የነገ ተስፋቸው መወጣጫ መሆኑን ተገንዝባችሁ አንድትጠብቁት አና ከግብ ለማድረስ የሚወጠኑ ውጥኖችን ሁሉ አንድትደግፉ፣ እርስ በእርስም በመተባበር አና በመተሳሰብ የነቃችሁ ትውልዶች አንድትሆኑ በቸሩ እግዚአብሔር ስም ዐደራ እላችኋለሁ።

አግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያን የሰላም አና መረጋጋት ምድር ያድርግልን። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ ፊት ሰለ ኢትዮጵያ ትማልድልን። አሜን!

† ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

26 October 2020, 18:24