እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ናት እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ናት 

እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ናት!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዛሬ ነሐሴ 16/2012 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት መሆኗን በመግለጽ የሚከበርበት አመታዊ በዓል በመከበር ላይ ይገኛል። “እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ናት” ስንል ምን ማለታችን ነው?

 “ወትቀው ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወሐብርት ስምዒ ወለትየ ወርእዬ ወአጽምዒ እዝነኪ፡፡ ንግሥቲቱ በንጹሕ ወርቅ ያሸበረቀ ጌጠኛ ልብስ ተጐናጽፋ ከዙፋንህ በስተቀኝ ቆማለች፡፡ የንጉሥ ሙሽራ የሆንሽ አንቺ ልጄ ሆይ! እኔ የምልሽ ጆሮዎችሽን አዘንብለሽ ስሚ ቃሌንም አድምጪ” (መዝ. 44፣10) እያለ ዳዊት ከስንት ዘመናት በፊት ስለዚህች የተመረጠች የአዳም ልጅ ትልቅነት በትንቢት ቃል ተናገረና ተነበየ; አንድ ቀን እመቤታችን ድንግል ማርያም ወደ ክብረ መንግሥት እንደምትደርስ አብራርቶና አረጋግጦ ተናገረ ትንቢቱም በፍልሰታ ቀን ተፈጸመ፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም ወደ ሰማይ አረገች፣ ለእርሷ የተዘጋጀ በቂ የሆነውን ክብር ተቀደጅታ ይህንን የለቅሶ ሕይወት በመተው አለፈች፣ የተወደደው ልጅዋ ኢየሱስ በስተቀኙ አዘጋጅቶላት ከነበረውም የክብር ዙፋን አስቀመጣት የሰማይ ንግሥት ብሎ ሰማያት፣ ለፍጡር የማይገባ ትልቅ ሥልጣን ሰጣት፣ የመነግሥቱ ክብር ተሳታፊ አደረጋት፣ «የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ´ ትላታለች እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን፡፡ «ንግሥቲቱ የወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ በቀኝህ ትቆማለች፣ ልጄ ሆይ ስሚ! እዪ! ጆሮዎችሽን አዘንቢዬ ወገንሽንና የአባትሽንም ቤት እርሺ፣ ንጉሥ ውበትሽን መርጧልና፣ እርሱ ጌታሽ ነውና፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም ወደ ሰማይ ወጣች ከንጉሡ አጠገብ በጐኑ ተቀመጠች፡፡ ከፍ ብሎ እንደተገለጠው ሁሉ የመንግሥቱ ክብር ተሳታፊ ሆነች፣ ከኢየሱስ ቀጥላ የመላእክትና የቅዱሳን ንግሥት ሆነች፣ በሰማይም ሆነ በምድር የላቀና ከእርሷ የማመይታለፍ ሥልጣን ተቀብላለች፡፡ ሰማያውያን መላእክትና ቅዱሳን ሁሉ አድናቆታቸው እየገለጹ ያመሰግኑታል፡፡

የሰማይ ንግሥት ተባለች፣ በምድር ምንም እንኳን ከነገሥታት ዘር ብትሆንም እንደ ማንኛዋም ተራ ሴት ሆና የሰማያዊ ንጉሥ እናት ሕይወቷን በትሕትና በድህነት አሳለፈች፡፡ ማን እንደሆነች ሳታውቅ ምድራዊ ዘመኗን ፈጸመች፡፡ ከአረፈች በኋላ ግን በሰማይ በሚገባ የሥነ ፍጥረት በሙሉ ንግሥት መሆኗን ገለጠች፡፡ እግዚአብሔር በምድርር ላይ ጸጋ እንደሰጣት እንዲሁም ዓለምን ከሄደች በኋላ በሰማይ ልዩ ጸጋ ሸለማት፡፡ አስቴር ንግሥት ሆና ከተሸለመች በኋላ በተሰጣት ሥልጣን ሕዝቧን በመረዳት ከሞት ልታድናቸው ቻለች፡፡ “የድህነትሽን ቀን አስታውሺ፣ ስለ እኛ ለንጉሥ ተናገሪ፣ ከሞት አድኚን” (አስቴር 4፣8) እያለ መርዶክዮስ ተናገራት፡፡ አኛም ይህን ልመና ወደ ሰማይ ንግሥት እናታችንልናቀርበው ይገባናል፡፡

እመቤታችን ማርያም ስለ እኛ ነው የአምላክ እናት የሆነችው፤ የሰማይ ንግሥት የሆነችው ለጥቅማችን ነው፤ በምድር በነበረች ጊዜም እንደ ልጆችዋ አድርጋ ታስብልንና ትመለከተን ነበር፡፡ አሁንም እንግዲሁ በሰማይ ከሆነች አልረሳችንም፣ ከልብዋ እኛን ከማሰብ አላቋረጠችም፣ አልቦዘነችም፡፡ የበለጠ ክብርና ሥልጣን ስለተቀበለች በይበልጥ ስለ እኛ ታስባለች፣ በሰማይ ዙፋን ተቀምጣ ስለ ሰው ፍጥረት ሁሉ ታማልዳለች፡፡

ሰላም ላንቺ ይሁን ንግሥት ሆይ እያልን እናክብራት፣ ከፍ ያለ ምስጋና እናቅርብላት፣ ዘወትር ሳይሰለቸንና ሳይደክመን በዙፋንዋፊት ቀርበን እንለምናት፡፡ «ልጄ ሆይ! ስሚ! እዩ! ጆሮዎችሽን አዘንብለሽ አድምጪ´ ይላል ዳዊት፡፡ እኛም በበኩላችን «እናታችን ሆይ! ተመልከቺን፣ ልመናችንን ስሚና ጩኸታችንን ተቀበዪ፣ መክራችንንም እዪ አግዥን፣ ያለንን ምኞትና ሐሳብ አቅኚልን እንበላት፡፡

በዚህ ዓለም በርኀራኄሽ ከእኛ ጋር ሆነሽ ደግፊን እያልን እንለምናት፡፡ ይህችን የሰማይ ንግሥት እናስታውስ፣ በእርስዋም ሙሉ እምነት እናድርግ፡፡

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

22 August 2020, 08:52