የወጣቶች ስደት እና የቤተክርስቲያን እንክብካቤ የወጣቶች ስደት እና የቤተክርስቲያን እንክብካቤ 

የወጣቶች ስደት እና የቤተክርስቲያን እንክብካቤ

ክፍል ስምንት

1.   የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ  እንክብካቤ  መመዘኛዎች፥

ቤተክርስቲያን የክርስቲያን ተስፋ ምልክት ናት፥  ክርስቶስ ለወደደው ህዝቡ ያሳየውን ፍቅር ፣ በቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ የምታስታውሰው እና የምትሰብከው ተስፋ ነው “እውነት እውነት እላችኋለሁ ፣ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” (ማቲ 25፥40) ፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተዋጾ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሕብረተሰቡ ውስጥ ወሳኝ ቦታ መኖሩን ያሳያል፡፡ ስለ ቤተክርስቲያናችን እይታ ስልታዊ እሳቤዎች በማህበራዊ እና በተለይም በዓለም ዓቀፍ ዙሪያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና ቀጣይነት ያለው ጥምረትና ድጋፍ እየሰጥች ትገኛለች፡፡ ይህ መሰረታዊ የቤተክርስቲያን ዓላማ ነው። እንደ አገራችን ኢትዮጵያ የአገልግሎት መጠንና የወጣቶች ግንዛቤ ልለይ ይችላል።

 የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ  እንክብካቤ ለስደተኞች አስፈላጊነት፥ እ.ኤ.አ በ 2018 ዓ.ም ር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮስ ለ104ኛው የስደተኞች ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት “በቤተክርስትያኗ ውስጥ የተቀደሰ ሐዋርያዊ ሕይወት ማቋቋሚያዎች የሚጫወቱት ሚና በስደተኞች ሐዋርያዊ አገልግሎት እንክብካቤ ላይ ባበረከቱት አስተዋጽኦ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ተመስሏል።  ስለሆነም፣ ስለዛሬው የዓለም ቀውስ እውነታዎች ለመናገር የቤተክርስቲያኗ ተሳትፎ፣ ለዘመኑ ምልክቶች ምላሽ በመስጠት ፍላጎቷ እንደምትቀጥል ያሳያል፡፡ የለውጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት እንክብካቤ ቁርጠኝነት ሁል ጊዜ የሚጠይቅ  መሆኑን ይገልጻል፡፡ ቤተክርስቲያኗ በክርስቶስ በተሰጣት ተልእኮ አማካይነት ለደካሞች በልዩ እርዳታ ትኩረት በመስጠት እና እንክብካቤ በማድረግ ትታያለች፡፡ ይህም እውነቱና አስፈላጊ  ልዩ ሥራዋ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

እንድሁም የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ፣ ለዓለም ስደተኞች ቀን እ.አ.አ በ2012 ዓ.ም ባስተላለፉት መልእክት እንዳስገነዘቡት “ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚመጡ ክርስቲያን ስደተኞች በሐይማኖታቸው ጸንተው እንዲቆዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፣ ተስደው የሄዱበትን አገር ሁኔታ በሚገባ ይረዱት ዘንድ ውይይት ማደረግ ይገባል፣ ለማሕበራዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ትኩረት ሰጥቶ መጓዝ ያስፈልጋል፣  ይጠይቃል፣ የካቶሊክ እመነት ተከታይ ለሆኑት ደግሞ ልዩ ሐዋርያዊ እንክብካቤ ማደረ ይገባል፣ በአከባቢው በቤተ-ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማደረግ የቤተክርስቲያኗ ወጣቶች አብረው እንዲራመዱ ማበረታታት፣ ወጣቶች  እና ጎልማሶች እንዲተባበሩ ቦታ መስጠት መልካም” ማለታቸው ይታወሳል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በበኩላቸው እንዳስገነዘቡት “ቤተክርስቲያኗ ከገዛ አገራቸው ለተፈናቀሉ ፣ አስቸጋሪ እና አስገዳጅ በሆነ መልኩ ለተለያዩ ቤተሰቦች ፣ በእኛ ዘመን ፈጣን ለውጦች ውስጥ ፣ በየትኛውም ስፍራ የተረጋጋ ቤተሰብ ማግኘት ለማይችሉ ሁሉ ቤተክርስቲያኗ ጆሮን ትሰጣለች። ያለአንዳች ቅሬታ መብት የሌላቸውን ሥቃይ ታካፍላለች፡፡ ቤተክርስቲያኗ በፖለቲካው ዘርፍ ቢሆን ለሰው ልጅ ተጠያቂነትዋንና ድምጹዋን ታሰማለች” ማለታቸው ይታወሳል።

ተስፋ፣ መተማመን እና ወንድማማችነት የሚሉት ሦስት ቃላት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኃላ ስድተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ በተመለከተ በተደጋጋሚ የተናገሩዋቸው ቃላት እንደ ሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በሰኔ 13/2012 ዓ.ም  በመላው ዓለም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አነሳሽነት በዓለም ደረጃ የስደተኞች ቀን ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ 66 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከገዛ ሀገራቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ተፈናቅለው እንደ ሚኖሩ የሚታወቅ ሲሆን ይህ መፈናቀል የተከሰተው በጦርነት፣ በብጥብጥ፣ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖሌቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተነሳ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካወጣው ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር ወር 07/2010 ዓ.ም ለእዚሁ ዓለማቀፍ የስደተኞች ቀን መዘጋጅ ይሆን ዘንድ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት “የእኛን በር የሚያንኳኳ እያንዳንዱ እንግዳ ኢየሱስን ለመገናኘት እድሉ ይከፍትልናል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን “ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መቀበል፣  መጠበቅ፣ ማብቃት እና ማዋሃድ" ያስፈልጋል በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ ኤርሚያስ ኩታፎ

24 July 2020, 11:10