ጳራቅሊጦስ እና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ጳራቅሊጦስ እና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች 

ጳራቅሊጦስ እና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች

ጳራቅሊጦስ

ሐዋርያት ኢየሱስ እንደሚተዋቸው ሲያውቁ አዘኑ፡፡ “እሄዳለሁ ስላልኋችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞላ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፡፡ ካልሄድኩ መንፈስ ቅዱስ አይመጣላችሁም፡፡ ከሄድኩ ግን እልክላችኋለሁ” (ዮሐ. 16፣6) መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ እውነትን ሁሉ ያስተምራችኋል (የሐዋ. 16፣13)፡፡ አባቴ ከእናንተ ጋር ለዘወትር የሚኖር አጽናኝ እንዲልክላችሁ እለምነዋለሁ (ዮሐ. 14፣15) ከላይ የሚወርድ ኃይል መንፈስ ቅዱስ እስክትቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ´ (ሉቃ. 24፣49) እያለ አበረታታቸው፡፡

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እነርሱም ቃሉን አምነው ከእመቤታችን ማርያምና ከሌሎች ሴቶች ጋር በጽዮን አዳራሽ በጸሎት ተጠመዱ፡፡ እንደዚህም ሆነው ሲጠብቁት ሳለ ነፋስ የሚመስል ድምፅ ያሉበትን ቤት ሞላው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ፡፡ በራሳቸውም ላይ የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ነጸብራቆች ታዩአቸው፡፡ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ በተለያዩ ቋንቋዎችም መናገር ጀመሩ (የሐዋ. 1፣12፤ 2፣1-14)፡፡

1.                «ከላይ ኃይል እስኪሰጣቸው ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ´፡፡ ካለዚህ ሰማያዊ ኃይል ሐዋርያት እውተኛ ተከታዮች አይሆኑም ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላቸው ኖሮ ኢየሱስ የሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት ባልፈጸሙት፣ ወንጌል ሊሰብኩ በዓለም ባልዞሩ ነበር፡፡ ችግር ሲያጋጥማቸው በፈሩ፣ በርግገውም ኢየሱስን ትተውት በተበታተኑ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፡፡ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ ሀገር ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ´ እያለ ተንብዮላቸው ነበር። (የሐዋ. 1፣8 ) ትንቢቱ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ተፈጸመ፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ሲወርድባቸው በመለወጣቸው መንፈሳዊ ሐሳብ አደረባቸው፡፡ ካለ ኢየሱስ በስተቀር ስለ ሌላ አይናገሩም፣ አያስቡም ነበር፡፡ በመጀመሪያ የነበራቸው ፍርሃት ጥርጣሬ ተወግዶ መንፈሳቸው ጽናትን አገኘ፣ እምነትና ብርታት ሞላባቸው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለብሰው ስለ ክርስቶስ በሁሉ ቦታ በግልጽ ሊሰብኩ፣ ለሰው ደኀንነትን ማብሰር ጀመሩ፡፡ ስብከታቸው ደግሞ ብዙ ፍሬ አፈራ፡፡ ነፍሳት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሳባቸው፡፡

እኛም ደግሞ በጥምቀት በሜሮን መንፈስ ቅዱስ ተቀበልን፡፡ በእኛ ላይ ወርዶ ከኃጢአት ልጆች የጽድቅ ልጆች አደረገን፡፡ ከእኛ ጋር አለ፣ ይመራናልም፡፡ በጸጋው አእምሮአችንን ያበራልናል ምኞታችንን ያሳካልናል፡፡ ሐዋርያት በጥሩ ዝግጅት ተቀብለውት እኛ ግን በቀዘቀዘ መንፈስ እንቀበለው ይሆን; በሐዋርያት ላይ ሲወርድ የቅድስና ፍሬ አሳየ፡፡ በእኛ ላይ ግን በበደላችን ምክንያት ያለ ቅድስና ፍሬ ይቀራል፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የግድ ያስፈልገናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣልን ተዘጋጅተን በልባችን እንቀበለው፡፡ በደንብ እናዳምጠው፡፡ በሙሉ ልባችን እንታዘዘው እናክብረው፡፡ በኃጢአት ከእኛ እንዳይርቅ እንጠንቀቅ፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች

መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ ሲወርድ የሚከተሉትን ሰባቱን ሰማያዊ ሀብቶቹን ያድለናል፡

1ኛ/ ጥበብ በዚህ ምድር ይህን መንፈሳዊ ሀብት የሚመስል እንደማይገኝ ብርሃኑ ከፀሐይና ከጨርቃ ይልቅ እንደሚደምቅ ጥበበ ሰሎሞን ያሳውቀናል (ጥበ. ሰሎ. 7፣29) ይህ ጥበብ ኃጢአት የማያሰከትለውን ጉዳት ያስረዳናል፡፡ ለዚህ ጉዳት መደኃኒቱን ይጠቁመናል፡፡ ምድራዊ ነገር ከንቱ እንደሆነና የዚህ ሐሳባችን እዚያው መቅረት እንደሚያስፈልገው ይነግረናል፡፡ ሥጋዊ ፍላጐታችንና ዓለምን እንዳንከተል አእምሮአችንን ያበራልናል፡፡

2ኛ/ ልቦና ጥበብ ፍጡር ምን መሆኑን ሲገልጽልን ልቦና ደግሞ ፈጣሪ ማን መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ የፈጣሪ ትልቅነት፣ ችሎታ፣ ፍጽምና … ብዙ ነገሮችን ይገልጽልናል፡፡ በአምላክ የሚገኝ መንፈሳዊ ሰላም፣ ደስት፣ ብፅዕና ያሳየናል፡፡ ልቦና እግዚአብሔርን አሳውቆ እርሱን እንድንወድ፣ ወደ እርሱ አቅርቦ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ያደርገናል፡፡ «ጌታ ሆይ እዚህ ካንተ ጋር መሆን ጥሩ ነው´ ማለትን (ማቴ. 17፣4) ያሳስበናል፡፡ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ስናውቅ፣ ፍቅሩን ስንቀምስ ዓለም ያስጠላናል፡፡ የአምላክ ፍቅር ጣፋጭነት ይስበናል፡፡ ፍጡሮችን ትተን ፈጣሪን ራሱን እንፈልጋለን፡፡ 

3ኛ/ እግዚአብሔርን መፍራት፣ መጽሐፈ ምሳሌ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ያስተምረናል (ምሳ. 1፣7)፡፡ «እግዚብሔርን የሚፈራ ብፁዕ ነው´ (መዝ. 112) ይላል ዳዊት፡፡ ይህ ፍርሃት «እግዚአብሔርን በድየዋለሁና እንዳይቀጣኝ´ የሚል ማንኛውም ባሕርያዊ ፍርሃት አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ፍርሃት ነው እንጂ፡፡ «እግዚአብሔር ፈጣሪያችንን፣ አባታችንን፣ ወዳጃችንን እንዳናሳዝነው´ የሚል ቅዱስ ጭንቀትና ጥንቃቄ ነው፡፡ ይህ ፍርሃት ኃጢአት ከመሥራት ይገታናል፡፡ ጸጋ ይመጣልናል፡፡ እግዚአብሔርም የሚፈሩትን ይባርካቸዋል፡፡

4ኛ/ ምክር ይህ አንድ ሰማያዊ ብርሃን ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ቅዱስ በውሳኔ በምርጫ ጊዜ አእምሮአችንን ያበራልናል፡፡ ለደኀንነታችን የሚሆነውን መንገድ እንድንመርጥ ይረዳናል፡፡ ደግሞ በፈተና ጊዜ ይመክረናል፡፡ ከክፉ ጥሩ፣ ከሥጋዊ ጥቅም የነፍስን ጥቅም፣ ከዓለም እግዚአብሔርን እንድንመርጥ ይገፋፋናል፡፡

5ኛ/ ብርታት በዚህ መንፈሳዊ ኃይል መንፈስ ቅዱስ በችግራችን ጊዜ ይረዳናል፡፡ ይህ ብርታት ሕይወታችንን አስተካክለንና አርመን ለመጓዝ ይጠቅመናል፡፡ የሚገባ ትጋት ጽናት ይሰጠናል፡፡ ሁሉን ረጋ ብለን ሳንቸኩል እንድናደርግ ይረዳናል፡፡ በጭንቀት ጊዜ መታወክን ትተን እርጋታን ትዕግሥትን እንድንላበስ ያደርገናል፡፡

6ኛ/ አአምሮ መንፈስ ቅዱስ በአእምሮ ፍጡር እንዳለ ያሳየናል፡፡ ሁሉ ነገር አላፊ እንደሆነ አሳውቆ ከፍጡሮች ኋላ እንዳንሄድ የዓለም ሀብት፣ ክብር፣ ስንል ፈጣሪን እንዳንረሳ ያስጠነቅቀናል፡፡ የዓለም ስጦታ በስስት እንዳንፈልገው ሲመጣልን ደግሞ መጥነንና አይተን እንድንጠቀምበት ያስታውሰናል፡፡

7ኛ/ ቸርነት እግዚአብሔርን ስናውቅ እንደ ፈጣሪያችን፣ አምላካችን፣ ወዳጃችን እንድናከብረውና እንድንወደው ይገባናል፡፡ ልክ ወላጆቻችን ሕይወት ስለሰጡን ባደረጉልን መልካም ነገር ሁሉ እንደምናመሰግናቸውና እንደመናከብራቸው እንዲሁ ደግሞ ይህንን ሰማያዊ ወዳጃችንን ሁሉን የሚሰጠንና የሚያስብልንን ማመስገንና ማክበር አለብን፡፡ ለእግዚአብሔር ስግደትና ውዳሴ እንድናቀርብለት ፍላጐታችንን ትተን ፍላጐቱን እንድንፈጽም ይገፋፋናል፡፡ ሕይወታችንን በአገልግሎት እንድናሳልፈው ያሳስበናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በነዚህ በሰባቱ ሀብቶች ከእኛ ጋር አለ ወይ; ከሌለ እንደገና እንዲመጣልን በሀብቶቹ እንዲሞላን መንፈሳችንን እንዲያድሰው እንማጠነው፡፡

07 June 2020, 17:54