ከደቡብ አፍሪቃ ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹ፤ ከደቡብ አፍሪቃ ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹ፤  

የደቡብ አፍሪቃ ወጣቶች አመጽን በጽኑ እንዲቃወሙት አደራ ተሰጣቸው።

በደቡብ አፍሪቃ፣ ሰኔ 9/2012 ዓ. ም. ብሔራዊ የወጣቶች ቀን ተከብሮ መዋሉ ተነገረ። ዕለቱ እንዳለፉት ዓመታት ወጣቶች በአካል ተገናኝተው ያከበሩት ባይሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በፌስ ቡክ አማካይነት እንዲከበር የተደረገ መሆኑ ታውቋል። በደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የፍትህ እና ሰላም ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪክቶር ፋላና ለወጣቶቹ በፌስ ቡክ አማካይነት ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ወጣቶቹ እምነታቸውን በሚገባ አውቀው እንዲኖሩበት በማለት የማበረታቻ መልዕክታቸውን አስተላልፈው፣ በሕይወታቸው ውስጥ ለሚያጋጣቸው በርካታ ችግሮች እና ፈተናዎች ሳይበገሩ፣ ተስፋቸውን አጥብቀው በመያዝ በእምነት ወደ ፊት መጓዝ ያስፈልጋ ብለዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ሰኔ 16/1976 ዓ. ም. በስዌቶ ከተማ ለነጻነት እና እኩልነት ሲታገሉ ሕይወታቸውን ያጡ ወጣቶችን መርሳት እንደሌለባቸው ገልጸው፣ ከ44 ዓመታት በፊት የተከፈለው መስዋዕትነት ከንቱ ሆኖ ሆኖ እንዳልቀረ፣ ፍሬን ያፈራ እና ታሪክን የቀየረ የደቡብ አፍሪቃ ሕዝቦች ኩራት መሆኑን አስረድተዋል። በዮሐ. 15፡13 ላይ “ሰው ሕይወቱን ስለወዳጆቹ አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር የለውም” የሚለውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ቪክቶር ፋላና፣ ይህ የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ፣ ወጣቶች በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለማሸነፍ ብርታት እንዲሆናችሁ ያስፈልጋል ብለዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የወጣቱ ትውልድ ተግዳሮቶች፣

በደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ዕድሜአቸው ከ16-24 በሆኑ ልጆች (30%) እና ከ25-34 (46%) በሆኑ ወጣቶች ላይ የደረሰው የሥራ ዕድል ማጣት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ቢሆንም “ተስፋ መቁረጥ የለባችሁም” በማለት አጽናንተዋቸዋል። በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ እንዲያስቡበት የመከሩት ብጹዕ አቡነ ቪክቶር ፋላና፣ ወጣቶቹ ከአማካሪዎቻቸው እና መንፈሳዊ አባቶች ጋር በመነጋገር ከሥራ ፈላጊነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት መሸጋገር የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ቪክቶር ፋላና መንግሥታቸው ለወጣቶች ልዩ ትኩርትን በመስጠት ለሥራ እንዲያዘጋጃቸው በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።

ችግርን ለመቋቋም መበርታት ያስፈልጋል፣

በትምህርት ዓለም የሚገኙትን ወጣቶች ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ቪክቶር ፋላና፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት፣ ታቅደው የነበሩ ፕሮጀክቶች መሰረዛቸውን ገልጸው፣ ወጣቶቹ በዚህ ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ ወረርሽኙም ቢሆን ጊዜያዊ መሆኑን አስረድተዋል። በሰባዎቹ ዓመታት ተማሪዎችን ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው መሆኑን አስታውሰው፣ ሁሉም የደረሰባቸውን ችግር ተቋቋመው ለመልካም ውጤት መብቃታቸውን ገልጸዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በትጋት መመከት ያስፈልጋል ያሉት ብጹዕ አቡነ ቪክቶር፣ ከዚህ ወረርሽኝ ራስን ለመከላከል በጤና ባለሞያዎች በኩል የሚወጡ መመሪያዎችን እና ደንቦችን ማክበር እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በስጋት ውስጥ ለሚገኙት እና ወላጆቻቸውን ላጡት ተስፋን መስጠት ያስፈልጋል ብለው፣ በእግዚአብሔር ላይ እምነትን በመጣል ወረርሽኙን ማስወገድ ይቻላል ብለዋል።

የአመጾች መከሰት፣

በደቡብ አፍሪቃ ማኅበረሰብ እና ቤተሰብ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን አስደንጋጭ የአምጽ ተግባራትን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ቪክቶር፣ ይህን አመጽ ወጣቶች በጽኑ እንዲቃወሙት አሳስበው፣ የሴቶች ሰብዓዊ መብት እና ክብር እስኪረጋገጥ ድረስ ድምጽ ማሰማት እና ለተግባራዊነቱ በርትቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ወጣቶቹ በደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የለውጥ አራማጆች እንዲሆኑ ያስፈልጋል ብለው፣ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥን ለማምጣት መስዋዕትን መክፈል ያስፈልጋል ብለዋል።

17 June 2020, 17:13