አለም አቀፍ የምድር ቀን አለም አቀፍ የምድር ቀን  

ምድራችንን የምንከባከብበት ክርስቲያናዊ የሆኑ ምክንያቶች

በሚያዝያ 14/2012 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ ለሃምሳኛ ጊዜ አለም አቀፍ የምድር ቀን ተከብሮ ማለፉ ያታወቃል። ይህ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የምድር ቀን በአሁኑ ወቅት የጋራ መኖሪያ ቤታችን በሆነችው በምድራችን ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ውድመት እና በደል ለአለም ሕዝብ ለማሳወቅ ታስቦ የሚከበር ቀን ሲሆን በምድራችን ላይ የሰው ልጆች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሚያደርሱት ጥፋት የምድራችን የአየር ንብረት አስገራሚ በሆነ መልኩ እየተለወጠ የሰው ልጆችን ለተለያዩ አደጋዎች እየዳረገ እንደ ሚገኝ ይታወቃል፣ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ይህንን በምድራችን ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ውድመት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የተለያየ ዓይነት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደ ምትገኝ ይታወቃል።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ፍጥረታትን የምንከባከብበት ክርስቲያናዊ የሆኑ ምክንያቶች

ከመስከረም 25 እስከ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም ድረስ “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር” በሚል መሪ ቃል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዐን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቫቲካን ተካሂዶ ማለፉ ይታወቃል። ይህ ሲኖዶስ “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቀውና 7.8 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የአማዞን ደን ክልል አዋሳኝ አገሮች ማለትም በብራዚል፣ በቦሊቪያ፣ በፔሩ፣ በኤኳዶር፣ በኮሎንቢያ፣ በቬንዙዌላ፣ በጉያና እና በሱሪናም አከባቢ የሚኖሩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ትኩረት ባደረገ መልኩ እና የቤተክርስቲያኗን ዓለማቀፋዊነት በሚያንጸባርቅ መልኩ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተውጣጡ የካቶሊክ ቤተክርቲያን ብጹዐን ጳጳሳትን ባካተተ መልኩ ቅዱስ ሲኖዶስ ተካሂዶ ማለፉ ይታወሳል።

“እናታችን የሆነችው ምድራችን። ምድራችንን እየገጠማት ያለውን ተግዳሮት በተመለከተ ክርስቲያናዊ የሆነ እይታ” በሚል አርዕስት በጥቅምት 13/2012 ዓ.ም ይፋ የሆነው መጽሐፍ  በአሁኑ ወቅት በአከባቢያችን ላይ እየደርሰ የሚገኘውን ከፍተኛ ውድመት በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና እንዲሁም የቁስጢንጢንያው የኦርቶዶክስ የዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትሪያርክ የሆኑት ፓትሪያርክ በርተሌሜዎስ በአሁኑ ወቅት አከባቢያችንን ወይም ምድራችን እየገጠማት የሚገኘውን ፈታኝ የሆነ ሁኔታ በተመለከተ ክርስትያኖች ሁኔታውን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር በማሰብ በጋራ እና በትብብር መሥራት እንደ ሚኖርባቸው የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። በተለይም ደግሞ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ምድራችንን በተመለከተ “የወደፊቱ ምድራችን እና በምድራችን ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን” በተመለከተ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ ለመፍታት እና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በጋር ተቀራርበው የሚሰሩበት እና ለምድራችን አስፈላጊ የሆነ እንክብካቤ ማደረግ እንደ ሚገባ የሚያሳስብ መጸሐፍ መሆኑም ይታወሳል።

የሰው ልጅ አንድነት

“ዘላቂ እና የተዋሃደ ልማት ለማምጣት ይችላ ዘንድ መላውን የሰው ልጅ አንድነት ባካተተ መልኩ እና በእዚህ  አማካኝነት የጋራ ቤታችንን የመጠበቅን አስፈላጊነት” የሚያጎሉ ሐሳቦች የተካተቱበትና የመጀመርያው ምዕራፍ “የተቀናጀ ራእይ” የሚል አርእስት ተሰጥቶታል። ይህ ጽንሰ-ሐሳብ የብክለት ፣ የአለም ሙቀት መጨመር ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ሕይወት በመጥፋት ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት ላይ እየተደረጉ የሚገኙትን አንዳንድ ስነ-ምዕዳርን የተመለከቱ ትንታኔዎችን በማጥናት “ዓለማቀፋዊ ከሆኑ ተግዳሮቶች አንስቶ ዓለም አቀፍዊ እስከሆኑ ዕድሎች ድረስ” ያለውን በመጥቀስ ማብራሪያ የሚሰጥ ምዕራፍ ነው። በአጭሩ ይህ አሁን ዓለማችን እየገጠማት የሚገኘው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ካላገኘ እና የመፍትሄ ሐሳቦች ካልተቀመጡ፣ ይህ ሐሳሳቢ የሆነ ሁኔታ እንዲቀየር የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ካልተቀመጡ ዓለማችን አሳሳቢ ወደ ሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለምትገባ ይህን ሐሳሳቢ ሁኔታ እና መፍትሄውን በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የሁኔታውን አሳሳቢነት፣ በተለይም ወጣቶች ግንዛቤ የሚያገኙበትን መድረክ እና ሁኔታ በመፍጠር ከህሊና የመነጨ እውነተኛ ሥነ-ምህዳራዊ የሆኑ ትምህርቶችን  በማስፋፋት ሁኔታውን መቀየር እንደ ሚገባ የሚገልጽ ሐሳቦች የተካተቱበት ምዕራፍ ነው።

የፍጥረታትን እና የሕይወትን መብት መጠበቅ

ንግግሮችን፣ ከታዳሚዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶችን እና ግንኙነቶችን በተጨማሪም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጓቸውን በርካታ ስብከቶች በተካተቱበት የመጽሐፉ ክፍል ውስጥ እርሳቸው ስመተ ርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ከተቀበሉበት እለት አንስቶ የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ያደረጓቸውን ንግግሮች እና የሰጧቸውን አስተያየቶች አጠቃሎ በያዘው የመጽሐፉ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ለሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት የሰጠውን ትልቁን ስጦታ ጠብቆ ለማቆየት ነው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ “በእግዚአብሔር እስትንፋስ” የተፈጠረው የሰው ልጅ አሁን በዓለማችን ላይ ለተቃጣው አሳሳቢ አደጋ በምድራችን ላይ የተቃጣባትን አደጋ ለመታደግ በሚደርገው ጥረት የሰው ልጅ በግንባር ቀደምትነት ተሳታፊ ይሆን ዘንድ ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብ የመጽሐፉ ክፍል ነው። በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ፈጣሪ የሆነው እግዚኣብሔር ፍጥረታት እና የሰው ልጅ የማይነጣጠል እና ጠንካራ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው መግለጻቸውን የሚያመለክቱ ሐሳቦች የተጠቀሱበት መጽሐፍ ሲሆን ፍጥረታት እና የሰው ልጅ ሕይወትን የተመለከቱ ጥያቄዎች መሰረታዊ እና ቀጣይነት ያላቸው ፍትሃዊ የሆኑ ጥያቄዎች በመሆናቸው የተነሳ ለእነዚህ የሕልውናችን ጥያቄዎች በሙሉ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን ከጥፋት መታደግ ይገባል የሚል እንድምታ የያዘ የመጽሐፉ ክፍል ነው። 

ስነ-ምዕዳርን የተመለከተ መንፈሳዊ ንባብ

“እናታችን የሆነችው ምድራችን” የተሰኘውን መጽሐፍ በማጠቃለያው ጽሑፍ ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትኩረታቸው አሁን ያለው የምድራችን ሁኔታ ለአካባቢያችን ደህንነት በጣሚ አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ መደረሱን ለማመልከት የተጠቀሙበትን ልዩ ልዩ ሐሳቦች አቅፎ በመያዝ ትንታኔ የሚያቀርብ የመጽሐፉ ክፍል ሲሆን ስነ-ምዕዳርን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሳያንሳዊ ትንታኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ የፈጣሪ ድንቅ ሥራ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ የተነሳ ነገረ-መለኮታዊ በሆነ መልኩ ጭምር ትንታኔ በመስጠት ምድራችን ሐሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መገኘቷ በራሱ መንፈሳዊ የሆነ መፍትሄ የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደ ሆነ ጨምሮ ይገልጻል።

የእግዚኣብሔር ፍቅር የሁሉም መዕክል ነው!

ፍጥረት የእግዚአብሔር ፍቅር ፍሬ ነው፣ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ እና ከሁሉም በላይ ለፍጥረታቱ ጠባቂ አድርጎ የሰየመው የሰው ልጅ ለምድራችን ተገቢውን ጥበቃ በማደረግ ምድራችን የሰው ልጆች በተስፋ የሚኖሩባት ሥፍራ ትሆን ዘንድ የማደረግ ኃላፊነት በሰው ልጆች ላይ የተጣለ ኃላፊነት መሆኑን የሚያትቱ ጽሑፎች ተካተውበታል። በእዚህም ምክንያት ትርጉም ባለው መልኩ አከባቢያችንን እና በአጠቃላይ ምድራችን እየደረሰባት ካለው ውድመት ለመከላከል የሰው ልጆች አንድነት በመፍጠር እና በተቀናጀ መልኩ ተግባራቸውን ማከናወን እንደ ሚገባቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተደጋጋሚ ማውሳታቸውን የሚገልጸው ይህ መጽሐፍ በሰው እና በፍጥረት መካከል ያለው በፍቅር ላይ የተገነባው ግንኙነት ከተቋረጠ የሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠውን ጸጋ ትርጉም ባለመረዳቱ የተነሳ ከፈጣሪው ጋር ያለው ግንኙነት ይናጋል የሚሉ የቅዱስነታቸው ሐሳቦች የተጠቀሱበት ጹሑፎች ይገኙበታል። የተፈጥሮ ሐብትን በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ ለማስገባት በሚደረገው ኃላፊነት የጎደለው ሐብት ለማጋበስ የሚደረገው ሩጫ ብዙዎቹ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሚከናወኑ በመሆናቸው የተነሳ ዓለማችንን እና የሰውን ልጅ ራሱ ሊያጠፉ የሚችሉ ክስተቶች በመሆናቸው የተነሳ ከአሁኑ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ እና መፍትሄ እንዲበጅላቸው ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ ያቅረቡትን ሐሳብ አቅፎ የያዙ ክፍሎችም በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሰዋል።

የኃጢያት አወቃቀር

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህ የአከባቢያችን እና በምድራችን ላይ በአሁኑ ወቅት እየተቃጣ የሚገኘው አደጋ አሰቸኳይ የሆነ መፍትሄ የሚያስፈልገው በመሆኑ የተነሳ ሁኔታው የበለጠ ከመስፋፋቱ በፊት ሕይወት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በእዚህም መሰረት ሕይወትን ለማቆየት የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ የሆኑ መርሆችን በመጠቀም የሰው ልጆች ሁሉ እኩል የሆነ መብት እና ክብር ያላቸው መሆናቸውን በሚገልጽ ሁኔታ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማርቀቅ አከባቢያችንን ከጥፋት መታደግ ይገባል የሚሉ ሐሳቦች የተካተቱበት መጽሐፍ ነው።

የምድራችን እና የድሆች ጩኸት

የቅድመ ሰነዱ ሁለተኛ ክፍል ውስጥ ደግሞ በምድራችን ላይ በተቃጣው ከፍተኛ አደጋ የተነሳ ምድራችን እና ሕዝቦቿ በመጮኽ ላይ ይገኛሉ የሚል እንድምታን ያዘለ ሰነድ ሲሆን ይህንን ችግር ከተቻለ ለማስወገድ ካልሆነ ለመቀነስ ይችላ ዘንድ የሚረዱ አንዳንድ አስተያየቶችን አቅፎ የያዘ የሰነዱ ክፍል ነው። በእዚህም መሰረት የምድራችንን እና የሕዝቦቿን በተለይም የድሆን ጩኸት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የተቀናጀ የስነ-ምዕዳር አሰራሮችን መከተል እንደ ሚገባ የሚያትት የሰነዱ ክፍል የሚገኝበት ነው።

“የአማዞን መሬት የያዘውን በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ወርቅ እና ዛፎችም ላይ ብዙዎች እጃቸውን አስገብተዋል። የቦታውን ሕዝቦች ሕይወት ያላገናዘበ የመንግሥት የተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲዎች በነዋሪው ላይ ችግር እያስከተለ ይገኛል በእዚህም የተነሳ መንግሥት ለእዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይገባዋል” የሚል አንቀጾች የተካተቱበት የሰነዱ ክፍል ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ “Earth Overshoot Day” (የምድርን የተፈጥሮ ሐብት ከመጠን በላይ በመጠቀማችን የሚደርሰውን ጉዳት) በተመለከተ ታስቦ የሚውለው ቀን በሐምሌ 22/2011 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። “Earth Overshoot Day” (የምድርን የተፈጥሮ ሐብት ከመጠን በላይ መጠቀም የሚያደርሰው ጉዳት) የሚታሰብበት ቀን መሬትን ከመጠን በላይ መጠቀም በተመለከተ የሰው ልጅ ሥነ ምህዳራዊ ሀብቶች እና አገልግሎቶችን ምድራችን በአንድ አመት ውስጥ መልሳ ማምረት ከምትችለው መጠን በላይ የምድራችንን ሐብት መጠቀም የሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ አስመልክቶ ታስቦ የሚውል ቀን ሲሆን በእዚህ ቀን ምድራችን በአንድ አመት ውስጥ ልትሰጠን ከምትችለው የተፈጥሮ ሐብት እጅግ በላቀ መልኩ በምድራችን ላይ ጫና በማደረግ ምድራችንን ለከፍተኛ አደጋ እና የአየር ንብረት ለውጥ እንደ ሚዳርጋት የሚያሳስብ ቀን ነው።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተለያዩ የማኅበራዊ አስተምሮዎቿ አማካይነት የአለም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ የሚገኘውን አደጋ በተመለከተ እና በተለይም ከኢንዱስትሪ አብዮት ማበብ እና መስፋፋትን ተከትሎ በከፍተኛ ደረጃ በከባቢ አየር ላይ በሚለቀቁ ጋዞች የተነሳ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በአለም ላይ እየተከሰተ የሚገኘው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ በቀዳሚነት ለዚህ ችግር እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጾ ያላበረከቱትን የአለማችን በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ከፍተኛ የሆነ ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ የተነሳ፣ የእነዚህን የድሃ አገራት ሕዝቦች ለስደት እና ለመከራ እየዳረገ የሚገኝ አደገኛ ክስተት በመሆኑ የተነሳ ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን እርምጃ እንዲወስዱ እና ታጋሽ የኃይል ምንጮችን እንዲጠቀሙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በማሳሰብ ላይ ትገኛለች።

ለእዚህም እርምጃ በዋቢነት የሚጠቀሰው ደግሞ አምስት አመት ገደማ በላቲን ቋንቋ “Laudato Si” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም ውዳሴ ለአንተ ይሁን በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይፋ ያደርጉት ሐዋርያዊ መልእክት በአብነት የሚጠቀስ ሲሆን “የጋራ የመኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን እንከባከብ” የሚል ጭብት የያዘ ሐዋርያዊ መልእክት ይፋ ማደረጋቸው ይታወሳል። ይህ ሐዋርያዊ መልእክት ስድስት ምዕራፎችን በውስጥ አቅፎ የያዘ ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን የእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት መሪ ሐሳብ የመነጨው ደግሞ እ.አ.አ. በ11ኛው ክፍለ ዘመን በኖረው እና ለተፈጥሮ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ከነበረው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ዘአሲሲ ጥሎት ካለፈው አሻራ ሲሆን እርሱም ምድራችንን በተመለከተ ሲናገር “የጋራ ቤታችን፣ ሕይወታችንን የምናጋራት እህታችንና እጆቹዋን ዘርግታ የምታቅፈን ውድ እናታችን” በማለት ምድራችንን ውበት ይገልጽ የነበረ ሲሆን በተጨማሪምጌታዬ ሆይ በምትንከባከበን እና በምታስተዳድረን በቀለማት ባሸበረቁ አበቦች እና ዕጽዋት በተሞላችውና ልዩ ልዩ ፍሬዎችን በምታፈራልን እህታችን እና እናታችን ምድር አማካይነት ተወደስ” በማለት የተፈጥሮን ሥጦታዎን በመመልከት ብቻ የእዚህ ስጦታ ፈጣሪ የሆነውን አምላክን ማወደስ እንደ ሚቻል ይገልጽ ነበር። ምድራችንን መንከባከብ ማለት የአምላክ ስጦታን መንከባከብ ማለት እንደ ሆነ አበክሮ ይገልጻል።

22 April 2020, 18:58