ልዑላን ከፍተኛ መሪ፣ ግርማዊ ጃኮሞ ዳላ ቶሬ (በመሃከል) ልዑላን ከፍተኛ መሪ፣ ግርማዊ ጃኮሞ ዳላ ቶሬ (በመሃከል) 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በማልታ ልዑላን ከፍተኛ መሪ ዕረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጹ።

በቅድስት መንበር የማልታ ልዑላን ማህበር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ሚያዝያ 22/2012 ዓ. ም. ባወጣው ዘገባ፣ የማኅበሩ 80ኛው ልዑላን ከፍተኛ መሪ፣ ግርማዊ ጃኮሞ ዳላ ቶሬ ማረፋቸውን አስታወቀ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በልዑል ጃኮሞ ዳላ ቶሬ ዕረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።  በሕመም ላይ የቆዩት ልዑል ጃኮሞ ዳላ ቶሬ በ75 ዓመት ዕድሜ ያረፉት ረቡዕ ሚያዝያ 21/2012 ዓ. ም. በሮም መሆኑ ታውቋል። ከፍተኛ ትምህርታቸውን በሮም ከተማ በሚገኝ ላ ሳፒዬንሳ እና ቀጥለውም ሮም በሚገኝ ኡርባኒያና ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ መከታተላቸው ታውቋል። በመካከለኛው ዘመን የኪነ-ጥበባት ታሪክ ላይ ያተኮሩ በርካታ ትምህርታዊ ጽሑፎችን ማበርከታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1985 ዓ. ም. የማልታን ልዑላን ማህበር የተቀላቀሉት ልዑል ጃኮሞ ዳላ ቶሬ፣ ለማሕበሩ ባላቸው አክብሮት እና ጽኑ ፍቅር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1993 ዓ. ም. መሓላ በመፈጸም በ2004 ዓ. ም. በተካሄደው የማኅበራቸው ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ማኅበሩን በበላይነት እንዲመሩ መመረጣቸው ታውቋል።

ሚያዝያ 21/2012 ዓ. ም. ማኅበራቸው የልዑል ጃኮሞ ዳላ ቶሬ የሕይወት ታሪካቸውን በማስታወስ እንደገለጸው በድህነት ሕይወት፣ በችግር ውስጥ የሚገኙትን በመርዳት፣ የፍቅር እና የቸርነት አገልግሎቶችን ሲያበረከቱ የቆዩ መሆናቸውን አስታውሷል። ከልዑል ጃኮሞ ዳላ ቶሬ ዕረፍት በኋላ ማኅበሩን በበላይነት እንዲመሩ በማለት ከፍተኛ አዛዥ ጎንዛሎ ዶ ቫሌ ፒሶቶ ዴ ቪላስ ቦአስን በጊዜያዊነት የተመረጡ መሆኑ ታውቋል።  

በቅድስት መንበር የማልታ መንግሥት ልኡላን ማኅበር አምባሳደር ክቡር አንቶኒዮ ዛናርዲ ላንዲ እንዳስታወቁት፣ በልዑላዊ ከፍተኛ መሪ ጃኮሞ ዳላ ቶሬ እረፍት ማኅበራቸው ከፍተኛ ሐዘን የተሰማው መሆኑን ገልጸው፣ ግርማዊ ጃኮሞ ዳላ ቶሬ በሕዝቦች መካከል ኅብረትን ለመፍጠር የጋራ ውይይቶች እንዲደረጉ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውንም አስታውሰዋል። የተጣለባቸውን ሃላፊነት በታማኝነት እና በትህትና የተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ድሆችን እና በማኅበረሰብ መካከል ተረስተው ለቀሩት እርዳታን በማድረግ በተለይም ሮም ከተማን በመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞች የጎዳና ተዳዳሪ እና መጠለያ አልባ ለሆኑ ሰዎች እርዳታን በማዳረስ ከፍተኛ አገልግሎት የፈጸሙ መሆናቸውን አስረድተዋል

የማልታ ልዑላን ማህበር ዋና ዓላማ፣ ኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ከፍተኛ ወታደራዊ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በጤና ዘርፍ የሕክምና አገልግሎቶችን እና በድህነት ሕይወት ውስጥ ለሚገኙት የገንዘብ እና የማቴሪያል እገዛን ለማድረግ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1048 ዓ. ም. በኢየሩሳሌም የተቋቋመ ማህበር መሆኑ ታውቋል። የማልታ ልዑላዊ ማኅበር ይበልጥ በጤና እና በማኅበራዊ ዘርፎች ተሰማርቶ ከ120 በላይ አገሮች ውስጥ ሰብዓዊ እርዳታዎችን በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። “ማልቴሴር ኢንተርናሽናል” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የማልታ ልዑላዊ ማህበር የዕርዳታ ማዕከል በተፈጥሮ አደጋ እና በጦርነት ለተጎዱት እርዳታን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። ባሁኑ ጊዜ በሶርያ እና ኢራቅ የሚካሄዱ ጦርነቶችን እና አመጾችን ሸሽተው ወደ ድንበር አካባቢዎች ለተሰደዱት ተፈናቃዮች ዕርዳታን በማቅረብ ላይ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። ማኅበሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቋሚ ታዛቢ ያለው መሆኑ ሲታወቅ፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ተወካዮች ያሉት መሆኑ ታውቋል። የማልታ መንግሥት ልዑላዊ ማህበር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ከ1834 ዓ. ም. ጀምሮ ዋና ጽሕፈት ቤቱን በሮም ከተማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ታውቋል።

30 April 2020, 19:55