የቡዳ እምነት ተከታይ ከካህናት ጋር በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ የቡዳ እምነት ተከታይ ከካህናት ጋር በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

የቡዳ እምነት መሪ ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ መርሃ ግብር የገንዘብ ዕርዳታ ማድረጋቸው ተነገረ።

በንያንማር የቡዳ እምነት መሪ፣ ክቡር አሺን ኒያኒሳራ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር የገንዘብ እርዳታን ማድረጋቸው ታውቋል። መነኩሴው አሺን ኒያኒሳራ በኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ለተጠቁት ወገኖች እንዲውል ብለው ያዋጡት የአሥር ሺህ ዶላር እርዳታ በኒያንማር የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለምታበረክታቸውን የጤና እና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚውል መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 28/2012 ዓ. ም. በኮሮና ቫይረስ ወረርሽ የተጎዱ አካባቢዎችን በገንዘብ እና በሕክምና መገልገያ መሣሪዎች ለማገዝ የሚያስችል የአስቸኳይ እርዳታ የማሰባሰብ መርሃ ግብር ማዋቀራቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

በንያንማር ውስጥ ሲታጉ ሳያዳው በሚል ስማቸው በስፋት የሚታወቁ የቡዳ እምነት መሪ ክቡር አሺን ኒያኒሳራ በአገሪቱ ከሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መከከል በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላቋቋሙት የኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የለገሱት የአሥር ሺህ ዶላር እርዳታ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጎዱት አገሮች ውስጥ ቤተክርስቲያን ለምታቀርበው አገልግሎት ድጋፍ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። ኡካ ኒውስ የተባለ የዜና ምንጭ እንዳስታወቀው መነኩሴው የአሥር ሺህ ዶላር እርዳታቸውን ያበረከቱት በንያንማር የማንዳላይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለሆኑት ለብጹዕ ማርቆስ ቲን ዊን መሆኑ ታውቋል። መነኩሴው ከዚህም በተጨማሪ ለኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እንዲሆን በማለት የሩዝ፣ የአዴንጓሬ እና የሌሎች ምግቦች እርዳታን መስጠታቸው ታውቋል። የቡዳ እምነት መንኩሴ ለሀገረ ስብከቱ ያደረጉት እርዳታ ከዚህ በፊት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ቤተክርስቲያናትን ለማገዝ ብለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባዋጡት የ750 ሺህ ዶላር እርዳታ ላይ ተጨማሪ  መሆኑ ታውቋል።

ለእምነት ተቋማት የሚደረግ የጋራ ርህራሄ፣

ለሀገረ ስብከቱ ያደረጉት የአሥር ሺህ ዶላር እገዛ በእምነት ተቋማት መካከል ላለውን የጋራ ርህራሄ መንፈስ ጥሩ ምልክት ሊሆን ይችላል ያሉት፣ በንያንማር የቡዳ እምነት መሪ የሆኑት ክቡር አሺን ኒያኒሳራ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያሰቃየ በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለው፣ የቸርነት ተግባራችንን በአንድነት ወደፊት ማራመድ ያስፈልጋል ብለዋል። በንያንማር የማንዳላይ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ቲን ዊን፣ መነኩሴው ባደረጉት በጎ ተግባር ልባቸው የተነካ መሆኑን አስገንዝበው፣ ሕዝባቸው በከፍተኛ ማህበራዊ እና የጤና ቀውስ ውስጥ በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ ለድሆች የተደረገው ድጋፍ ያስደሰታቸው መሆኑን ከገለጹ በኋላ የተደረገላቸው እርዳታ በአገራቸው ውስጥ በሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት መካከል መልካም ወዳጅነት ስለመኖሩ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

በንያንማር የቡዳ እምነት መሪው ክቡር ሲታጉ ሳያዳው፣ ከንያንማር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የያንጎን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከካርዲናል ቻርል ቦ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ሲታወቅ፣ ከፍተኛ የቡዳ እምነት ተከታዮች ባሉባት ንያንማር ውስጥ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች የጋራ ውይይቶችን በማሳደግ ትልቅ አስተዋጽዖን ያበረከቱ እና በማበርከት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።  በንያንማር የቡዳ እምነት መሪው የሆኑት ክቡር ሲታጉ ሳያዳው፣ በንያንማር የ“ሲታጉ ቡዳ እምነት አካዳሚ” ፕሬዚደንት እና በአገራቸው ውስጥ በቡዳ እምነት ስር የሚገኙ ልዩ ልዩ ማኅበራትን በአማካሪነት በማገልገል የሐይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ የሚሳተፉ መሆናቸው ታውቋል። መነኩሴው ክቡር ሲታጉ ሳያዳው፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ንያንማር ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ያገኟቸው መሆኑ ሲታወስ ቀጥሎም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2011 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸው ይታወቃል።

መነኩሴው ክቡር ሲታጉ ሳያዳው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ የዕርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ያደረጉት የገንዘብ እርዳታ ይፋ የሆነው በንያንማር የአዲስ ዓመት መለወጫ ዕለት መሆኑ ሲነገር፣ በዕለቱ መከበር የነበረበት ብሔራዊ በዓል በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መሰረዙ ታውቋል። የእስያ አገር በሆነች ንያንማር የወረርሽኙ ምልክት ከታየበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሚያዚያ 9/2012 ዓ. ም. ድረስ 85 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህ ውስጥም ሁለቱ መሞታቸው ታውቋል።

21 April 2020, 19:50