ስደተኞች ወደ ደቡብ ጣሊያን ግዛት ሲደርሱ፣ ስደተኞች ወደ ደቡብ ጣሊያን ግዛት ሲደርሱ፣ 

ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ የአውሮፓ አገሮች ሊተባበሩ ይገባል።

የኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ስደተኞች ወደ ደቡብ ጣሊያን ግዛት ወደ ሆነው ሲሲሊያ እየገቡ መሆኑን የአርጄንቶ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ፍራንችስኮስ ሞንተነግሮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል። ከጥቂት ቀናት በፊት የወደብ ከተማ ወደ ሆነው ፖርቶፓሎ ከተማ 77 ስደተኞች መድረሳቸውን እና በብዙ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከተሳፈሩበት መርከብ ወርደው ወደ ጣሊያን ግዛት ለመግባት የመንግሥት ይሁንታን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን “ሲ ዎች” የተባለ የባሕር ላይ ነፍስ አድን የዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

በግል ጀልባ የተሳፈሩት በርካታ ስደተኞች በደቡብ ጣሊያን ግዛት በሆነው ሲሲሊያ በኩል እየገቡ መሆኑ ሲነገር በአውሮፓዊያኑ የብርሃነ ትንሳኤ በኦኣል ዕለት ብቻ 150 የሚሆኑ ከሊቢያ የተነሱ ስደተኞች ፖዛላኖ ወደ ተባለ የጣሊያን ግዛት መድረሳቸው ታውቋል። በግል ጀልባ ተሳፍረው የሜደቴራኒያን ባሕር በማቁረጥ ወደ ጣሊያን የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር መጨመሩ የተነገረ ሲሆን ከእነዚህ ስደተኞች መካከል የሕክምና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው፣ ከእነዚህም መካከል አንድ ነፍሰ ጡር እናት መኖሯ ታውቋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለስደተኞች የሚደረገውን የመስተንግዶ አገልግሎት አስቸጋሪ እንዲሆን ማድረጉ ሲታወቅ በዚህ መሠረት የጣሊያን መንግሥት የወደብ በሮቹ እንዲዘጉ በማለት ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል።

ስደተኛን የማስተናገድ ባሕል ሊስተካከል ይገባል፣

የተሻለ ሕይወት ለመኖር ሲሉ ሰዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ አሳልፈው መስጠታቸው የሚያሳዝን ቢሆንም የምንገኝበት ጊዜ ለሁላችንም አስቸጋሪ ነው ያሉት የአርጄንቶ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ፍራንችስኮስ ሞንተነግሮ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ራስን መከላከል አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው ይህም ለስደተኞች የሚደረገውን አቀባበል እና መስተንግዶ ለመቀነስ አለመሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፍራንችስኮስ በማከልም ስደተኞች ወደ ጣሊያን የሚያደርጉት ጉዞ ከዚህ በፊት የነበረ ወደ ፊትም የሚቀጥል በመሆኑ የአካባቢው ሕዝብ ስደተኛን በክብር ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕሉን ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።      

ችግር እንዳለ የማውቅ ከሆነ መፍትሄ ማግኘት ይኖርብኛል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፍራንችስኮስ አብዛኛው ሕዝብ ዕድሜው እየገፋ መሆኑን የአውሮፓ አገሮች በመዘንጋት ተጨማሪ የሰው ኃይል አያስፈልገኝም ከማለት ይልቅ ስደተኛን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅሙን በማስተባበር እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለይቶ ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፍራንችስኮስ በማከልም የወደፊት ዕድላችንን ማስተካከል ማለት ከዚህ በፊት ምን እንደተከናወነ ማሰላሰል ሳይሆን ወደፊት እንዴት ልንገለገልባቸው እንችላለን ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል።

በሀገረ ስብከታቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አዝጋሚ በመሆኑ ዕድለኞች ነን ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፍራንችስኮስ በአካባቢው የሚገኙ የሕክምና መስጫ ማዕከላት ወረርሽኙን ለመከላከል ብቁ ባይሆኑም በቫይረሱ የተጠቁ ሕሙማንን ተቀብሎ አስፈላጊውን እርዳት ማድረግ በምንችልበት ደርጃ ላይ እንገኛለን ብለዋል።        

16 April 2020, 18:43