“እግዚአብሔርም ቁጣውን ይገልጻል” መጽሐፍ የፊት ገጽ፣ “እግዚአብሔርም ቁጣውን ይገልጻል” መጽሐፍ የፊት ገጽ፣  

"እግዚአብሔር ቁጣውን የሚገልጸው ለህዝቡ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ነው"።

የእግዚአብሔርን ቁጣ እና ፍርድ አስመልክቶ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው ምን ያህል እውነተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቁጣ በምን መንገድ እንደገለጸው እና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ የሚስጥ መጽሐፍ በቅርቡ ታትሞ የወጣ መሆኑ ታውቋል። የመጽሐፉ ደራሲ የሆኑት ክቡር አባ አልዶ ማርቲን፣ እግዚአብሔር የሚቆጣው ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ መሆኑን አብራርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክቡር አባ አልዶ ማርቲን በጣሊያን የቪቼንሳ ከተማ ካህን ሲሆኑ በሀገረ ስብከታቸው በሚገኝ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኃይማኖት መምህር መሆናቸው ታውቋል። በአሲሲ ከተማ የሚገኝ የሥነ መለኮት ተቋም ዳይሬክተርም መሆናቸው ታውቋል። ለተለያዩ መንፈሳዊ መጽሄቶች ጽሑፎችን በማበርከት የሚታወቁት አባ አልዶ ከፍተኛ ፍላጎት አድሮባቸው በቅርብ የሚከታተሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔርን ቁጣ በሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተለይም በብላይ ኪዳን መጽሐፍ ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በሌላ ወገንም በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተገለጸውን የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ ከብሉይ ኪዳን ጋር በማወዳደር፣ እግዚአብሔርን ሁለት ዓይነት ገጽታዎች እንዳሉት የሚያስመስለውን ክፍል ለመመልከት ጥረት አድርገዋል። አባ አልዶ ማርቲን አሁን ላሳተሙት መጽሐፍ የመረጡት ርዕስ “እግዚአብሔርም ይቆጣል፤ የእግዚአብሔር ቁጣ እና መለኮታዊ ፍርድ ፍቅሩን የሚገልጽበት መንገድ ነው” በማለት ያብራራሉ። በመጨረሻም የመጽሐፋቸውን ጭብጥ ሲያጠቃልሉ፣ በእርግጥ እግዚአብሔር በሚቆጣበት ጊዜ እና ፍርዱን በሚሰጥበት ጊዜ ቁጣው ለጉዳት ጉዳትን ለማስከተል ሳይሆን ለሕዝቡ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽበት መንገድ መሆኑን አባ አልዶ ማርቲን ከቫቲካን ዜን አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

“የእግዚአብሔር ቁጣ” በሚለው መጽሐፋቸው እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያጸናውን ግንኙነት ምን እንደሚመስል ማስረዳት ቀዳሚ ዓላማቸው እና ፍላጎታቸው መሆኑን የገለጹት አባ አልዶ ማርቲን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር እና መልካም ፈቃድ የሚገልጹ እንጂ ከዚህ የተለየ አለመሆኑን አስረድተዋል። አንዳንድ ጊዜ ብሉይ ኪዳንን ከአዲስ ኪዳን ጋር በማወዳደር በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ቁጣውን የሚገልጽ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር ምሕረቱን እና ፍቅሩን የገለጠበት ሁኔታን በመመልከት እግዚአብሔር ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት የሚያስቡ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ያስታወሱት አባ አልዶ ይህ አስተሳሰብ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን አስረድተው እግዚአብሔር ሁለት አቋም እንደሌሉት፣ ሕዝቡን የሚያፈቅር፣ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር በቁጣ የሚገልጽ እግዚአብሔር መሆኑን አስረድተዋል። እርሱ ለራሱ የመረጠው የእስራኤል ሕዝብ በኃይለኞች በኩል ጥቃት ሲፈጸምባቸው ደስ እንደማይሰኝ የገለጹት አባ አልዶ፣ ደስ የማይሰኘውም በአመጸኞች፣ ህዝቡን በሚገድሉ የፖለቲካ መሪዎች ፣ በተለይም በአቅመ ደካሞች እና በድሆች ላይ ግፍን በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ቁጣውን የሚገልጽ መሆኑን እና ለሕዝቡ ያለውን ጥልቅ ፍቅር በዚህ መልክ የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል።

የሕዝብን ስቃይ በተመለከተ በብሉይ ኪዳን፣ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ በርካታ ንጹሃን ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር እኩል እንዲሰቃዩ እግዚአብሔር ያደረገበት ወቅት መኖሩን ያስታወሱት አባ አልዶ ይህ ታሪክ በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው ሁሉ ከዚህ በፊት፣ ዛሬ እና ወደ ፊት ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜም የሚያነሳው ታሪክ ነው ብለው ይህን ታሪክ መርምሮ ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀ ሰው አለመኖሩን ገልጸዋል። በማቴ. 27:46 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውኸኝ?” ማለቱንም አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስን “አምላኬ” ማለቱ ከአባቱ ያልራቀ፣ በስቃይ ጊዜ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ያስገነዝበናል ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም መምህር ነው ብለን ስንመሰክር ምስክርነታችን እውነት ያሉት አባ አልዶ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካምነት፣ መሐሪነት እና አዳኝነት ምን ጊዜም ቢሆን አይካድም ብለው በሌላ ወገን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን መዘንጋት የለብንም ብለዋል። ስለ ሆነም አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስም ቁጣውን የሚገልጽባቸው አጋጣሚዎች አሉ ብለዋል። የሰው ልጅ በበሽታ እና በክፋት ሲጠቃ ኢየሱስም አይደሰትም ያሉት አባ አልዶ በዚህ ባሕሪው በብሉይ ኪዳን ውስጥ በአንዳንድ መጽሐፍት ላይ ከተጠቀሱት ታሪኮች ጋር የኢየሱስ ክርስቶስ አቋም ተመሳሳይነት አለው ብለዋል። በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ግብዝነት እና ኃጢአት በመቃወሙ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ተመሳሳይነት አለው ብለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፋቸውን አንዳንድ መልዕክቶን እና የዮሐንስ ራዕይን የተመለከትን እንደሆነ የእግዚአብሔር ቁጣ የታየባቸውን አጋጣሚዎችን መኖራቸውን አስረድተው ይህም የእግዚአብሔ ፍቅር የተገለጠበት ሆኖ እናገኛለን ብለዋል።

በመጀመሪያው የመጽሐፋቸው ክፍል ስለ እግዚአብሔር ቁጣ ከተናገሩ በኋላ በሁለተኛው ክፍል ስለ እግዚአብሔር ፍርድ የተናገሩበት ምክንያት ለምን እንደሆነ ያስረዱት አባ አልዶ በሁለቱም መጽሐፍት ማለትም በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን መካከል የጠበቀ ግንኙነት መኖሩን ለማሳየት ነው ብለው፣ ፍርድ የዘመናችን ሰዎች ነጻ ሕሊናቸውን በመጠቀም የሚውስዱት ውሳኔ መኖሩን፣ ይህን ተጠቅመው ወደ እውነት ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት በራሳቸው ተግባር ወደ ትክክለኛው ፍርድ መድረስ የሚችሉ መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰው ልጅ በመጨረሻው ዘመን ለፍርድ እንደሚቀርብ መናገሩ በሰው ላጅ ላይ ቅጣትን ለመጣል ሳይሆን በሕይወት ዘመናችን ያከናወናቸው ተግባራት ወደ ብርሃን በመውጣት እውነቱን ለማሳየት መሆኑን አባ አልዶ አስረድተዋል። በማቴ. 25 ላይ በዓለም መጨረሻ የሰው ልጅ በመላእክቱ ሁሉ ታጅቦ በክብር ዙፋኑ በሚቀመጥበት ጊዜ ሕዝቦችም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ ይላል። በሁለት ተከፍለው በግራ እና በቀኝ እንደሚቆሙ ይናገራል። “ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ታርዤ አልብሳችኋኛል ወዘተ። በዚያን ጊዜ ጻድቃን እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል፥ ጌታ ሆይ! መቼ የርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ ወሰትረፈ። ንጉሡም በእውነት እላችኋለሁ፣ ከእናአዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው።” በዚህ መልኩ እግዚአብሔር በዓለም መጨረሻ ፍርድን በሚሰጥበት ጊዜ በፍቅር ተነሳስተን ለደረግናቸውን መልካም ሥራዎች ዋጋን በመስጠት አስፈላጊ እንደነበሩ ሊያሳውቀን ይፈልጋል በማለት አስረድተዋል።

መጽሐፋቸው ዓለማችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚሰቃይበት ወቅት ለንባብ መብቃቱን የገለጹት አባ አልዶ ማርቲን፣ በሉቃ. 13 ላይ “የገሊላ ሰዎች ለእግዚአብሔር መስዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ ጲላጦስ ገደላቸው፣ ደማቸውም ከመስዋዕታቸው ጋር ተደባለቀ” የሚለውን ጥቅስ ያስታወሱት አባ አልዶ፣ ኢየሱስም ሲመልስ ታዲያ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ሁሉ ጥፋት የሰረሰባቸው፣ ከሌሎች የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ኃጢአተኞች ስለነበሩ ይመስላችኋልን? አይድደለም! በኃጢአታችሁ ተጸጽታችሁ ንስሓ ባትገቡ፣ እናንተም እንደእነስርሱ ትጠፋላችሁ” ማለቱን አስታውሰዋል። ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ ፍርድ አለመስጠቱን የትናገሩት አባ አልዶ የወንጌሉ ጥቅስ በሚገባ ያነበብን እንደሆነ በስተጀርባው የእግዚአብሔር ቁጣ እንደሌለበት ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስም በግልጽ እንደተናገረው በገሊላ ሰዎች ላይ የደረሰው ቅጣት በእግዚአብሔር ፍርድ ወይማ ቁጣ አለመሆኑን፣ ነገር ግን ሰዎች በሰሩት ኃጢአት ተጸጽተ ንስሓ የማይገቡ እና የማይለወጡ ከሆን ተመሳሳይ ቅጣት የሚደርስባቸው መሆኑን ተናግሯል ብለዋል። አሁን የምንገኝበት የስቃይ ጊዜ ሰዎች በሙሉ ሃላፊነትን በመውሰድ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን፣ በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑት እና በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙት የሚፈወሱበት መንገድ ማመቻቸት ከእግዚ አብሔር የተላከ አደራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2016 ዓ. ም. ያወጁትን የምሕረት ዓመት ያስታወሱር ክቡር አባ አልዶ፣ በእርግጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ምሕረት ብዙ ተናግረዋል ብለው በዓለማችን በተለያየ ደረጃ የሚፈጸሙ ኢፍትሃዊነት መኖሩን በማስታወስ፣ ለዚህም ሰዎች ለኃጢአታቸው ምህረትን እንዲለምኑ ለማድርግ ነው ብለው እግዚአብሔር የሚቆጣው ለሚራራለት ሕዝቡ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ እንጂ ሕዝቡን ለመጉዳት አለመሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣

                                          

15 April 2020, 21:03