የኢየሱስ መልክ በታቦር ተራራ ላይ በቅጽበት ተቀየረ የኢየሱስ መልክ በታቦር ተራራ ላይ በቅጽበት ተቀየረ  

የመጋቢት 06/2012 ዓ.ም የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ከአሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ውስጥ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መርጦ ወደ ተራራ የወጣበት አጋጣሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የእለቱ ምንባባት

1.      ኦሪት ዘፍጥረት 12፡1-4

2.    መዝሙረ ዳዊት 32

3.    2ኛ ጦሞቲዎስ 1፡8-10

4.    ማቴዎስ 17፡1-9

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የኢየሱስ መልክ በቅጽበት መቀየር

ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ። በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። ወዲያውም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፤ በዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ቃድህ ከሆነ፣ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው። እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።

ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲሰሙ ደንግጠው በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ። ኢየሱስም ቀርቦ ነካቸውና፣ “ተነሡ፤ አትፍሩ” አላቸው። ቀና ብለው ሲመለከቱም ከኢየሱስ በስተቀር ሌላ ማንንም አላዩም። ከተራራው በመውረድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም እንዳትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ (እሁድ መጋቢት 06/2012 ዓ.ም) በጀመርነው የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት እለተ ሰንበት ስርዓተ አምልኮ የኢየሱስ መልክ ተዐምራዊ በሆነ መልኩ መለወጡን በማሰብ እንድናሰላስል የሚጋብዘን ሲሆን ይህም የተከሰተው ኢየሱስ ደቀ-መዛሙርቱ ለሆኑት ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ የትንሳኤው ክብር ተምሳሌት የሆነውን ወደ ሰማይ በክብር የወጣበትን አጋጣሚ ገና እዚህ ምድር ላይ እያለ ቀድመው እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል። ከአሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ውስጥ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መርጦ ወደ ተራራ የወጣበት አጋጣሚ  ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ስለ ኢየሱስ ተአምራዊ የሆነው መልክ መለወጥ የመመሥከር ልዩ መብት ሰጣቸው። ነገር ግን ለምንድነው እነዚህን ሦስቱን ደቀመዛሙርት ብቻ የመረጠው? ለምንድነው እጅግ ቅዱስ ስለሆኑ ነው? በፍጹም! ጴጥሮስ ኢየሱስ ሞት በተፈረደበት ወቅት ይክደዋል፣ ሁለቱ ወንድማማቾች ያዕቆብ እና ዮሐንስ በመንግሥቱ የመጀመሪያ ስፍራ እንዲሰጣቸው ተጠይቁዋል (ማቴ 20፡ 20-23)።  ሆኖም ኢየሱስ  እንደኛ መስፈርት አይደለም ምርጫውን የሚያካሂደው፣ ነገር ግን በእርሱ የፍቅር እቅድ መሰረት ነው። የኢየሱስ ፍቅር ምንም ልኬት የለውም ፣ ፍቅር ነው ፣ እናም በእዚያ ፍቅር እቅድ ይመርጣል። ነፃ ፣ ቅድመ-ሁኔታ የሌለው፣ በነፃ ተነሳሽነት፣ በምላሹ ምንም ነገር የማይጠይቅ መለኮታዊ ፍቅር ነው። እናም እነዚያን ሦስቱን ደቀመዛሙርት እንደጠራ ፣ በተመሳሳይም ዛሬ ስለእርሱ እንዲመሰክሩ የተወሰኑ ሰዎችን ወደ እርሱ ይጠራል። የኢየሱስ ምስክር መሆን የማይገባን ስጦታ ነው፣ እኛ ብቁ እንዳልሆንን ይሰማናል፣ ነገር ግን በእዚህ ስሜት ተገፋፍተን አቅም የለንም በሚል ሰበብ ወደ ኋላ መመለስ አይገባንም።

ወንጌላዊው ሉቃስ (9፡28-36) እንደሚያሳየን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የብርሃን ሥፍራ በሆነው በተራራ ላይ መልኩ መቀየሩን የገለጸልን ሲሆን ይህም ግልጸት ለየት ባለ ሁኔታ ለሦስቱ ደቀ-መዛሙርት ብቻ ለየት ባለ ሁኔታ የተሰጣቸው ልምድ ነው። እነርሱም ከኢየሱስ ጋር ወደ ተራራው ላይ ይወጣሉ እርሱም ለብቻው ለመጸለይ መሄዱን ይመለከታሉ፣ ከእዚያም በኋላ “የፊቱ መልክ መለወጡን ይመለከታሉ” (ሉቃ. 9፡29)። እነርሱ እርሱን በየቀኑ ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ እንደ ማነኛውም ሰው አብሮዋቸው ሲኖር ይመለከቱት የነበረ ሲሆን አሁን ግን ሰብዓዊነቱን ባካተተ መልኩ ባሳየው አዲስ ክብር ፊት ለፊት ቆመው ይደነቃሉ። እነሆም ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤  በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ፋሲካ ማለትም ስለ መከራው፣ ሞቱ እና ትንሳኤው ይናገሩ ነበር።  ከፋሲካ በፊት የተደርገ ግልጸት ነበር።  ጴጥሮስ ኢየሱስን “አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” (ሉቃ 9:33) በማለት ይናገራል። እርሱ ያ በብርሃን የተሞላ የጸጋ ዘመን ፈጽሞ እንዳያበቃ ፈልጎ ነበር!

ኢየሱስ መልክ ተአምራዊ በሆነ መልኩ መለውጥ በክርስቶስ ተልዕኮ እጅግ በጣም ትክክለኛ እና ወሳኝ በሆነ ጊዜ ውስጥ የተከናወነ ክስተት ሲሆን ይህም ማለት ደቀ መዛሙርቱ እርሱ "ብዙ መከራ እንደ ሚደርስበት [...] እንደ ሚሞት እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደ ሚነሣ” ቀድመው እንዲገነዘቡት አድርጉዋል። ኢየሱስ ይህን እውነታ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት እንደማይወዱት ያውቃል - የመስቀል እውነታ፣ የኢየሱስ ሞት እውነታ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት እንደ ማይፈልጉት ይገነዘባል- በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሰማይ አባቱ አንዲያ እና ምርጥ የሆነውን ልጁን ወደ ዘለዓለማዊ ክብር እንዲገባ የሚያደርግበት መንገድ ልጁን ከሙታን በማስነሳት መሆኑን ደቀ-መዛሙርቱ በሚገባ ይገነዘቡ ዘንድ፣ በዚህም ምክንያት በመስቀል ላይ የሚደርሰበትን መከራ እና ሞት መቋቋም ይችሉ ዘንድ ሊያዘጋጃቸው በመፈለጉ የተነሳ የፈጸመው ተግባር ነው። ይህም ደግሞ አንድ ደቀ-መዝሙር ሊከተለው የሚገባው መነገድ ነው፣ ማንም ሰው ወደ ዘለዓለም ሕይወት ሊደርስ የሚችለው በምድራዊ ሕይወቱ የኢየሱስን መስቀል ተሸክሞ ሲጓዝ ብቻ መሆኑን ያሳያል። እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ መስቀል አለን። የራሳችንን መስቀል ተሸክመን በምንጓዝበት ወቅት ጌታ የዚህ ጉዞ ጫፍ የሆነውን የትንሳኤውን ውበት የምንመለከትበትን አቅጣጫ ያሳየናል።

ስለዚህ የክርስቶስ መልክ መለወጥ የክርስቲያን ሕይወት የስቃይ ሁኔታ ያሳየናል። መከራ ማለት ሐዘን ውስጥ መግባት ማለት አይደለም: አስፈላጊ የሆነ ሂደት ነው፣ ጊዜያዊም ነው። እኛ እንድንደርስበት የተጠራንበት ስፍራ የክርስቶስ መልክ እንደ ተለወጠበት ሥፍራ እኛም የምንደርስበት ሥፋር በብርሃን የተሞላ ነው፣ በእሱ ውስጥ ደህንነት፣ ደስታ፣ ብርሀን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ ያለ ገደብ እናገኛለን። በዚህ መንገድ የእርሱን ክብሩን ማሳየት መስቀል፣ ፈተናዎች፣ ትግል የምንገጥማቸው ችግሮቻችን ሁሉ  መፍትሄ የሚያገኙት እና ድል የሚሆኑት በእርሱ ፋሲካ  ወቅት መሆኑን ያረጋግጥልናል። በዚህም የተነሳ በዚህ አሁን ባለንበት የዐብይ ጾም ወቅት እኛም ወደ ተራራ እንውጣ! ነገር ግን በምን ዓይነት ሁኔታ ነው መውጣት የሚኖርብን! በጸሎት። በጸሎት መንፈስ ወደ ተራራ እንውጣ፣ በጽሞና መንፈስ በሚደረግ ጸሎት፣ በልባችን ውስጥ ብቻ በሚሰማ ጸሎት፣ ኢየሱስን ብቻ እንድንፈልግ በሚያበረታታን ጸሎት። ለተወሰነ ጊዜ በአስተንትኖ መንፈስ ውስጥ እንግባ፡ በእየለቱ ትንሽዬ ጊዜ ወስደን አስተንትኖ እናድርግ፣ ውስጣዊ ስሜቶቻችን በእርሱ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ የእርሱ ብርሃን በሕይወታችን ውስጥ እንዲያንጸባርቅ እንፍቀድለት።

በእርግጥም ወንጌላዊው ሉቃስ "እርሱ በሚጸልይበት ጊዜ" መልኩ እንደ ተለወጠ ይተርክልናል። ከአብ ጋር በጥልቀት መወያየቱ፣ በዚያም የሕግ እና የነቢያት መገለጫዎች የሆኑት የሙሴና የኤልያስ -ቃላትን በማስተጋባት በመስቀሉ ላይ ያለውን ሞት ጨምሮ፣ በሙሉ ነፍሱን ለአብ የማዳን ፈቃድ ራሱን በማስገዛት የእግዚአብሄር የብርሃን ክብር ራሱ ተቀብሎ ለእኛም እንዲያንጸባርቅ አድርጉዋል።

ስለዚህ ወንድሞች እና እህቶች፡ በክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚደረግ ጸሎት ሰው ውስጣዊ የሆነ መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጣ ያስችለዋል፣ ከእዚያም በዙሪያው ያለውን ዓለም ያበራል። ብርሃንን የሚያበሩ ሰዎች፣ ከዓይናቸው ደማቅ ብርሃን የሚወጣ ሰዎችን ስንት ጊዜ አግኝተናል! እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጸሎተኛ የሆኑ ሰዎች ናቸው፣ ጸሎት ደግሞ ይህንን የማድረግ ብቃት አለው፡ ጸሎት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ብርሃን መስጠት እንድንችል ያደርገናል።

ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት መንገድ መራመድ በደስታ እንቀጥል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ የአምልኮ ሥነ-ስርዓቶች በተደጋጋሚ በመካፈል ለጸሎት እና ለእግዚአብሄር ቃል ቦታ መስጠት ይኖርብናል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከኢየሱስ ጋር እንድንቆይ ታስተምረን ዘንድ እና በእርሱ መንገድ ላይ ለመጓዝ እንችል ዘንድ እርሷ ትርዳን። ምክንያቱ የእርሱን ክብር ማየት የምንችለው ከእርሱ ጋር ሆነን ስንኖር ብቻ በመሆኑ የተነሳ ነው።

ምንጭ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 29/2012 ዓ.ም ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ!

አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

13 March 2020, 14:23